1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኩፍኝ ወረርሽኝ መስፋፋት እና የቀጠፈው ሕይወት

ዓርብ፣ መጋቢት 13 2016

በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አከባቢዎች የኩፍን በሽታ መስፋፋት የሰዎችን ህይወት እያጠፋ ስለመሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ በክልሉ ሰሜን ሸዋ ዞን ዋራ ጃርሶ ወረዳ በስምንት ቀበሌዎች የተከሰተ ወረርሽኙ በአንድ ሳምንት ብቻ ከ50 ያላነሱ ህይወት መቅጠፉ ነው የተነገረው፡፡ በወረርሽኙ ከተጠቁት ደግሞ አብዛኛዎቹ ህጻናት ናቸው ተብሏል፡፡

https://p.dw.com/p/4e1HR
የክትባት ምልክት
የክትባት ምልክት ምስል Weber/Eibner-Pressefoto/picture alliance

የኩፍኝ ወረርሽኝ በኦሮሞያ ክልል የብዙ ሰዎችን ህይወት ቀጠፈ

የኩፍኝ ወረርሽኝ መስፋፋት እና የቀጠፈው ህይወት

በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አከባቢዎች የኩፍን በሽታ መስፋፋት የሰዎችን ህይወት እያጠፋ ስለመሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ በክልሉ ሰሜን ሸዋ ዞን ዋራ ጃርሶ ወረዳ በስምንት ቀበሌዎች የተከሰተ ወረርሽኙ በአንድ ሳምንት ብቻ ከ50 ያላነሱ ህይወት መቅጠፉ ነው የተነገረው፡፡ በወረርሽኙ ከተጠቁት ደግሞ አብዛኛዎቹ ህጻናት ናቸው ተብሏል፡፡

በክልሉ የሰሜን ሸዋ ዞን ወራ-ጃርሶ ወረዳ ፋጂ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አስተያየት ሰጪ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአከባቢያቸው በፍጥነት የተዛመተው የወረርሽኙ መስፋፋት ለብዙዎች ህይወት መቀጠፍ ምክኒያት ነው ይላሉ፡፡ ይህ ስፍራ ሰሜን ሸዋ ዞንን ከምዕራብ ሸዋ ዞን የሚያዋስነው ከአባይ በረሃ እና ሙገር ወንዝ ቆላማ አከባቢዎች መካከል የሚገኝ ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡ “ፋጂ ኤጀርሳ የምባለው መንገዱ እሩቅ ነው፡፡ በረሃማ ነው፡፡ መኪና በተሻለ ወደ ውስጥ ከገባ እንኳ ከ2 ሰኣት በላይ የእግር ጉዞ ያለው ስፍራ ነው፡፡ በወረርሽኙ በብዛት እየተጠቁ ያሉት ህጻናት እና እርጉዝ እናቶች ናቸው” ብለዋል፡፡ አስተያየት ሰጪው አንድ ሳምንት ውሳጥ 50 ገደማ ህጻናት እና አዛውንቶች በዚሁ በወረርሽኙ ማለፋቸውን አስረድተዋል፡፡

የወረርሽኙ በአንድ ሳምንት ውስጥ መስፋፋት

ሌላም አስተያየት ሰጪ የአከባቢው ነዋሪ አስተያየታቸውን ቀጠሉ፡፡ “ወረርሽኙ በብዛት ያጠቃው ከአስር ዓመት በታች ያሉ ህጻናትን ነው፡፡ ባለፈው አንድ ሳምንት በተለይም በአንድ ቀበሌ ብቻ ከ20 በላይ ህጻናት ማለቃቸውን አውቃለሁ፡፡ ይህ የሆነው ፋጂ ኤጄርሳ ከምባል ቀበሌ አንድ ሰፈር ውስጥ ነው፡፡ በሽታው እንደዛሬ ከያዛቸው በማንቀጥቀት በማግስቱ ይገድላቸዋል” ነው ያሉት፡፡

በአከባቢው ቤተሰብ ያላቸው እና አከባቢው ላይ ያደጉት፤ አሁን ላይ ግን በአዲስ አበባ የሚገኙ አንድ አስተያየት ሰጪም ሃሳባቸውን እንዳከሉልን፤ “አከባቢው እንደ ቆላ ነገር ነው፡፡ ኩፍኝ አንድ ጊዜ የሚይዝና በዋናነት ህጻናትን የሚያጠቃ በሽታ ነው፡፡ አሁንም አንድ ህይወታቸው ካለፈ የ45 ዓመት ጎልማሳ ውጪ በብዛት የተጠቁት ህጻናት ናቸው” ብለዋል፡፡

የኩፍኝ የወረርሽኙ በአንድ ሳምንት ውስጥ መስፋፋት
የኩፍኝ የወረርሽኙ በአንድ ሳምንት ውስጥ መስፋፋትምስል Imago/Science Photo Library

የፀጥታው ችግር ያሰፋው የጤና አሰጣጥ ክፍተት

እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ በነዚህ አከባቢዎች ለዓመታት በኢትዮጵያ መንግስት እና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ባለው የታጠቀ ቡድን መካከል የሚደረግ ጦርነት በአከባቢው የጤና መሰረተ ልማትን ጨምሮ በርካታ የማህበራዊ መገልገያ መሰረተ ልማቶችን አውድሟል፡፡ “እነ ከዚህ በፊት የማውቀው ሆሴህ ጤና ጣቢያ የሚባል ነበር በአከባቢው፡፡ አሁን ወድሟል፡፡ ትምህርት ቤትም እንዲሁ የለም፡፡ በተለይም የዛሬ

ሶስት ዓመት አከባቢ በዚህ ዙሪያ በከፋው ጦርነት በርካታ ጤና ጣቢዎች እና ትምህርት ቤቶች እንዳልነበሩ ሆነዋል” ነው ያሉት፡፡ በወረዳው ከጎሃ ፅዮን እና ቱሉ ሚልኪ በስተቀር ትምህርት ቤቶች እና ጤና ጣቢዎቹ የጦርነቱ ሰለባ ሆነው መውደማቸውንም አስረድተዋል፡፡ ሌላም አስተያየት ሰጪ አስተያየታቸው አከሉ፤ “በአከባቢው ባለው የጸጥታ መደፍረስ ክትባት የለም፡፡ በዚህ አከባቢ የሰላም ሁኔታ አስቸጋሪ ስለሆነ ከታች ቆላ ወደላይ መውጣትም ሆነ ከላይ ደጋ ያለው ወደ ቆላው ወርዶ አገልግሎት መስጠቱ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ በዚህም ለዓመታት ክትባት በዚህ አከባቢ አይዳረስም፡፡ ሰው የመታከም እድል በማጣቱ ብቻ በሚታከም በሽታ በቀላሉ ያልፋል፡፡ ይህ ወረርሽኝ ድሮ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ተረስቷል፡፡ ተከስቶም አያውቅም ነበር፡፡ በፖለቲከኞች ፍልሚያ ምክኒያት ሰው በቀላል በሽታ እያለቀ ነው” ሲሉ ይናገራሉ፡፡

እንደ ክልል የወረርሽ መስፋፋት እና የበጎ ፈቃደኞች ርብርብ

የኩፍኝ ወረርሽኝ መስፋፋት እና የቀጠፈው ሕይወት
የኩፍኝ ወረርሽኝ መስፋፋት እና የቀጠፈው ሕይወትምስል Imago/Xinhua

በአካባቢው ተከስቷል ስለተባለው ወረርሽኝ እና ስለሚሰጠው ግብረመልስ ለመጠየቅ ለኦሮሚያ ጤና ቢሮ የተለያዩ ኃላፊዎች ብንደውልም ስብሰባ ላይ በመሆናቸው አስተያየት መስጠት እንደማይችሉ ገልጸውልናል፡፡ ያም ሆኖ ግን በኦሮሚያ ክልል በርካታ ወረዳዎች ውስጥ የተከሰተው የኩፍኝ በሽታ ወረርሽኝ በ16 ሺህ ሰዎች ላይ መገኘቱን የክልሉ ጤና ቢሮ መረጃ ያሳያል፡፡

አስተያየታቸውን የሰጡን የወረ-ጃርሶ ወረዳ ነዋሪው በአከባቢው በሚገኙ ስምንት ቀበሌያት የተከሰተውን ወረርሽኙን ለመግታት ትናንት እና ዛሬ የተወሰኑ በጎ ፈቃደኛ ሃኪሞች ከአዲስ አበባ ወደ ስፍራው ተጉዘው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡ ያም ሆኖ ግን የችግሩ ግዝፈት ሰፊ እንደመሆኑ ሰፊ ርብርብ እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል፡፡ “ከአዲስ አበባም 10 የሚሆኑ በጎ ፈቃደኛ ሃኪሞች መጥተዋል፡፡ ወደ ስድስት የሚደርሱ ነፍሰጡሮች ወደ ገብረጉራቻ ሪፌር ተብለው ተልከዋል፡፡ ወረርሽኑ የተከሰተባቸው ወደ 8 ቀበሌዎች ስለሚሆኑና ጤና ጣቢያዎች አስቀድሞም ስለወደሙ ሰፊ ርብርብ ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ባለፉት አምስት ዓመታት ገደማ ተስፋፍቶ የቆየው ግጭት በርካታ ቦታዎች ላይ የጤናን ጨምሮ ሌሎች ማህበራዊ መገልገያዎችን በማውደሙ ህብረተሰቡን ለሰፋፊ ቀውሶች መዳረጉ ተደጋግሞ ይነገራል፡፡

ሥዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ታምራት ዲንሳ