የኦነግ አመራሮች መፈታት ለፖለቲካ ድርጅታቸው ብሎም ለአገር እፎይታ ነው ተባለ
ቅዳሜ፣ ጳጉሜን 2 2016የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የሰባት አመራሮቹን ከአራት ዓመታት የተራዘመ እስርመለቀቅን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ የፖለቲከኞቹ መፈታት ለቤተሰቦቻቸው፣ ለፖለቲካ ድርጅታቸው ብሎም ለአገር እፎይታ ነው ብሏል፡፡ ኦነግ ይህን ሲል ግን ፖለቲከኞቹ የታሰሩት ህጋዊውን የፖለቲካ ስራቸውን ከመስራት ውጪ ያጠፉት አንዳችም ጥፋት አልነበረም የሚለውን ሃሳብ በማስመር ነው፡፡
ኦነግ በመግለጫው እርምጃውን የፍትህ እና እርቅ አዎንታዊ ምልክት አድርጎ እንደሚወስድ ነው የገለጸው፡፡ ይሁንና በቀጣይ በየደረጃው ያሉ አባላቶቹና ደጋፊዎቹ እንዲፈቱም ተጨማሪ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ብሎም ተዘግተውብኛል ያለው ጽ/ቤቶቹ ተከፍተው በፖለቲካ ሂደቱ በነጻነት መንቀሳቀስ እንዲቻል ጠይቋል፡፡
የፖለቲከኞቹ መፈታት፤ አዎንታዊነት
የፓርቲው የፖለቲካ ኦፊሰር ያሶ ከበበው ሆርዶፋ ለዶቼ ቬለ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሮያ የፖለቲከኞቹ መፈታት ሁሉንም የፖለቲካ ችግሮች የሚቀይር ባይባልም ለሰላም መልካም ምልክት የሚሰጥ ጅማሮ ብለውታል፡፡ “ሰላም በአንድ አገር የፖለቲካ አውድ ውስጥ ያለው ሚና ስለሚታወቅ ‘የፖለቲካ ታሳሪዎችን’ መልቀቅ በየትኛውም ሚዛን ሲታይ ጠቃሚ ነው” ያሉት ፖለቲከኛው ሂደቱ ሜዳውን ለሰላምና እርቅ የሚያመቻች ከሆነ እሰየሁ የሚያስብል ነው ብለውታልም፡፡ ይህም ሂደት ምናልባትም “ፖለቲካን ከመሳሪያ አፈሙዝ ወደ ብዕርና ጠረጴዛ የሚመልስ ከሆነ ሊበረታታ የሚገባ ነው” ብለዋልም፡፡ አቶ ያሶ ሂደቱ ጥቂት አመራርን ብቻ በመፍታት ላይ እንደማቆም ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡
በሰላም ማምጣት ሂደት ውስጥ ጉልህ ድርሻ መወጣት ያለበት መንግስት ነው ያሉት ፖለቲከኛው ከክልሉም አልፎ መላው አገሪቱን ለሚያምስ ግጭት ፖለቲካዊ ውይይት እንደማድረግ ምንም መፍትሄ እንደሌሌም ነው ሃሳባቸውን ያስቀመጡት፡፡
ከኦነግ አመራሮች መፈታት ጋር ተያይዘው አስተያየታቸውን የሰጡን ሌላው የህግ ባለሙያና የፖለቲካ ተንታኝ ሄኖክ ገቢሳ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ዶ/ር ሄኖክ አስተያየታቸውን የጀመሩት ስለ የፖለቲካ አመራሮቹ መፈታት ስሜታቸውን በማጋራት ነው፡፡ “ለነሱ በጣም ነው የተደሰትኩት፤ ያለምንም ፍርድ ለአራት አመታት እስር ላይ ቢቆዩም አሁን ተለቀው እንደማንኛውም ሰው በነጻነት የመንቀሳቀስ መብታቸውን ገቢራዊ ማድረግ በመጀመራቸው ደስተኛ ነኝ፤ ነገር ግን መንግስት ሲፈልግ ሚያስር ሲፈልግ የሚፈታ መሆኑንም በዚህ አይቸበታለሁ” ብለዋል፡፡
የፖለቲከኞቹ መፈታት የሰላም መንገድ ጅማሮ ይሆን?
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎችን በማስተላለፍ የኦሮሚያ ግጭት እንዲያበቃ፤ ከተቻለም በቀጣዩ ወርሃ መስከረም ውስጥ የሚደረገውን የኢሬቻል በዓል አብሮ ማክበር እንዲቻል የሚሉ ጥሪዎችን አስተጋብተዋል፡፡ የኦነግ አመራሮቹ ከእስር የመፈታት ዜናም የተሰማው የርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ በተላለፈበት አንድ ሳምንት እንኳ ባልሞላበት ጊዜ ነው፡፡ ምናልባትም እነዚህ በቀጣይ የአገሪቱ የፖለቲካ አውድ ለመቀየር ለመወጠኑ ማሳያ ይሆን? የፖለቲካ ተንታኙ ሄኖክ ገቢሳ በዚህ የሚስማሙ አይመስልም፡፡ “የአዲስ ዓመትን መምጣት ተከትሎ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የሚለቃቸው እስረኞች አካል ካልሆነ በስተቀር የፖለቲካው መሰረታዊ ለውጥ ጥሪ አይመስለኝም” በማለት አስተያየታቸውን አጋርተዋል፡፡
ዶ/ር ሄኖክ በአስተያየታቸው አገሪቱን ከግጭት ወደ ሰላም ለማምራ መንገዱም ይህ ነው ይላሉ፡፡ “የትግራዩን ጦርነት ያቆመው የፕሪቶሪያው ተኩስ ማቆም ስምምነት ጥሩ ተሞክሮ ሊሆን ይችላል፡፡ መፍትሄው ድርድርና ውይይት ነው፡፡ ለዚ ደግሞ ቀዳሚው እርምጃ ጠመንጃ ማስቀመጥ ነው” ብለዋል፡፡ በአገሪቱ ሁሉም አከባቢ ያሉ ሃይሎች ለጊዜውም ቢሆን ተኩስ በማቆም ለድርድር እንዲቀመጡና አዲስ ራዕይ ያለው አገራዊ የፖለቲካ አቅጣጫ መቀየስም አገሪቱን ከግጭት አዙሪት የሚያወጣው ብቸኛው መንገድ ብለውታል፡፡
ስዩም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር