1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«የኦነግ ሸኔ» ጥቃት በተፈናቃዮች ላይ፦ ኢሰመኮ

ሐሙስ፣ የካቲት 9 2015

የኢሰመኮ መግለጫ፦ «ታጣቂዎቹ ጥቃቱን ባደረሱበት ከተማ ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው የሚኖሩ ተፈናቃዮችን ቤትለቤት እየዞሩ በተለይ የአማራ ብሔር ተወላጆችን ለይተው ገድለዋል» በማለት የምርመራ ግኝቱ ጠቁሟል። ጥር 25 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በተሰነዘረው ጥቃት ቢያንስ 50 ሰዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ ኮሚሽን አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/4Na9H
Äthiopien l Gebäude Ethiopian Human Rights Commission( EHRC)
ምስል Solomon Muchie/DW

ቢያንስ 50 ሰዎች ተገድለዋል

የኢትዮጵያ መንግስት «ኦነግ-ሸኔ» በሚል ስም በአሸባሪነት የፈረጀዉና ራሱን «የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት» በማለት የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ጥር 25 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በሰነዘረው ጥቃት ቢያንስ 50 ሰዎች መግደሉን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ ኮሚሽን አስታወቀ። ከሟቾቹ መካከል አራቱ ሴቶች እና ሦስቱ ሕፃናት ናቸው ተብሏል። 42ቱ በተፈናቃዮች የመጠለያ ጣቢያ ውስጥ እና ከተቀባይ ማኅበረሰብ ጋር ተቀላቅለው ይኖሩ የነበሩ ተፈናቃዮች እንዲሁም መንግሥትን ይደግፋሉ የተባሉ ነዋሪዎች መሆናቸውንም ኢሰመኮ ገልጧል።  አንድ የክልል የሥራ ኃላፊ ከነ አሽከርካሪያቸው፤ የከተማ ፖሊስ እና የቀበሌ ሚሊሻ አባላትም በታጣቂዎቹ መገደላቸውን ኢሰመኮ አክሏል። 

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ወለጋ ዞን ጎቡ ሰዮ ወረዳ አኖ ከተማ ጥር 25 ቀን 2015 ዓ.ም በዋናነት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ኢላማ በማድረግ ተፈጽሟል ባለው ጥቃት በሰው ሕይወት፣ አካል እና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን በተመለከተ ምስክሮችን፣ የመንግሥት አካላትን እና የተጎጂ ቤተሰቦችን በማነጋገር ምርመራ ማድረጉን ገልጿል። በዚሁ እለት በርካታ ቁጥር ያላቸው የወታደር ልብስ የለበሱ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ ኦነግ ሸኔ) መሆናቸው በነዋሪዎች የተገለጹ ታጣቂዎች በሦስት አቅጣጫ ወደ አኖ ከተማ መግባታቸውን፤ በመቀጠል በከተማዋ የተለያዩ አቅጣጫዎች ተከታታይ የሆነ የተኩስ ድምፅ መሰማት መጀመሩን እና የሲቪል ሰዎች ግድያና የአካል ጉዳት፣ የንብረት ዘረፋ እና ውድመት መድረሱንም አስታውቋል።

ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ በአካባቢው በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት ከጎቡ ሰዮ ወረዳ 11 ቀበሌዎች እና ከሁለት የአዋሳኝ ወረዳ ቀበሌዎች ተፈናቅለው በአኖ ከተማ በመጠለያ ውስጥ እንዲሁም ከመጠለያ ውጭ ከተቀባይ ማኅበረሰብ ጋር ተቀላቅለው የሚኖሩ ቁጥራቸው 10,800 የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚገኙ መሆኑንም በተቋሙ የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ክፍል የሪጅን ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ኢማድ አብዱልፈታህ ለዶቼ ቬለ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ ጠቅሰዋል።

Äthiopien l Gebäude Ethiopian Human Rights Commission( EHRC)
የኢሰመኮ ዓርማ በመሥሪያ ቤቱ ግድግዳ ላይ ይታያልምስል Solomon Muchie/DW

«በታጣቂ ቡድኑ በተፈጸመ ጥቃት አንድ የክልል የሥራ ኃላፊ ከነሾፌሩ፣ የከተማ ፖሊስ እና የቀበሌ ሚሊሻ አባላትን ጨምሮ ቢያንስ 50 ሰዎች ተገድለዋል። ከእነዚም መካከል 42 ተጎጂዎች በተፈናቃዮች የመጠለያ ጣቢያ ውስጥ እና ከተቀባይ ማኅበረሰብ ጋር ተቀላቅለው ይኖሩ የነበሩ ተፈናቃዮች እንዲሁም መንግሥትን ይደግፋሉ የተባሉ ነዋሪዎች ነበሩ፡፡ ከሟቾች መካከል አራት ሴቶች እና ሦስት ሕፃናት ናቸው፡፡»

«ታጣቂዎቹ ጥቃቱን ባደረሱበት ከተማ ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው የሚኖሩ ተፈናቃዮችን ቤትለቤት እየዞሩ በተለይ የአማራ ብሔር ተወላጆችን ለይተው ገድለዋል» በማለት የምርመራ ግኝቱ ጠቁሟል። 
የሟቾችን አስከሬን ጥቃቱ በተፈጸመበት ዕለት እና በማግስቱ የአካባቢው ማኅበረሰብ መቅበ ታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ 8 ሰዎች ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል፡፡ በተፈጸመው ጥቃት በከተማዋ የሚገኙ የግለሰቦች የንግድ መደብሮች፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ሌሎች ተቋማት መጠነ ሰፊ ዘረፋ እና ውድመት እንደተፈፀመባቸውም ተገልጿል። ኢሰመኮ ጥቃቱ በዕቅድና ዝግጅት የተፈጸመ ነው ብሏል።

በሌላ በኩል የመከላከያ ሰራዊት ከተማዋን መልሶ ከተቆጣጠረ በኋላ “ከሸኔ ጋር ተባብራችኋል” በሚል ጥርጣሬ ስምንት ወጣቶችን በቁጥጥር ስር ካዋሉ በኋላ በጸጥታ ኃይሎች መገደላቸውን ኢሰመኮ አረጋግጫለሁ ብሏል። «የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ኢላማ በማድረግ የተፈጸመው ጥቃት በክልሉ በቀጠለው ግጭት ምክንያት የሲቪል ሰዎች ደኅንነት የከፋ ደረጃ ላይ መድረሱን ያሳያል» ያለው ኢሰመኮ መንግሥት የሲቪል ሰዎችን ደኅንነት ከማስጠበቅ በተጨማሪ ለግጭቱ ዘላቂ እና ሰላማዊ መፍትሔ ለማበጀት ተጨባጭ እርምጃ መውሰድ አለበት ሲል ገልጿል።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ