1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦሮሚያ እና የሶማሌ መስተዳድር ግጭት ብሷል

ሐሙስ፣ ጳጉሜን 2 2009

በኢትዮጵያ የኦሮሚያ እና የሶማሌ ክልሎች በሚያዋስኗቸው ወረዳዎች የተቀሰቀሰው ግጭት ወደ ባሌ እና ቦረና ዞኖች ተስፋፋ። ዛሬ በባሌ ዞን በተቀሰቀሰው ግጭት ብቻ አራት ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል። የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥም ግጭቶቹ መከሰታቸውን አረጋግጧል።

https://p.dw.com/p/2jXjc
Äthiopische Volksgruppe der Oromos
ምስል picture alliance/Yvan Travert/akg-images

ታጣቂዎች ድንበር ተሻግረው የሶማሌ ክልል ሰንደቅ ዓላማ አውለብልበዋል

የኦሮሚያ እና የሶማሌ ብሔራዊ ክልሎች በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች የተቀሰቀሱት ግጭቶች ወደ ቦረና እና ባሌ ዞኖች ተዛምተዋል። ዛሬ ሁለቱ ክልሎች ከሚዋሰኑበት ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው የቦረና ዞን ጫሙኪ የተባለ ቀበሌ በተቀሰቀሰ ግጭት የሰዎች ህይወት መጥፋቱን የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ጉዳዮች ኮምዩንኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። አቶ አዲሱ እንደሚሉት የሁለቱን ክልሎች የተሻገሩ ታጣቂዎች ከዚህ ቀደም የተደረሰ ሥምምነትን በመጣስ የሶማሌ ክልልን ሰንደቅ ዓላማ በአካባቢው አውለብልበዋል። በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ቦረና ዞን ሞያሌ ከተማ ጫሙኪ ቀበሌ "ከዚህ በፊት የሶማሌ ክልል መንግሥት ትክክል ባልሆነ መንገድ የመንግሥት ፕሮጀክት ለመገንባት ሥራ አስጀምሮ ነበር" የሚሉት አቶ አዲሱ ግንባታው በኦሮሚያ የአስተዳደር ወሰን ውስጥ የተጀመረ መሆኑ ውይይት ተደርጎበት ተቋርጦ እንደነበር ይናገራሉ። "ትናንትና የተደረገውን ሥምምነት በመተላለፍ ከሶማሌ ክልል የመጡ የታጠቁ ኃይሎች እዛ አካባቢ ላይ የሶማሌ ክልልን ሰንደቅ አላማ የማውለብለብ ነገር ነው ያደረጉት።" የሚሉት አቶ አዲሱ ዛሬ ጳጉሜ 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ከጠዋቱ 11 ሰዓት አካባቢ ግጭት መቀስቀሱን፤የተኩስ ልውውጥ እንደነበርም አክለዋል። "ሞያሌ ዛሬ የተከሰተው ግጭት በጣም ከፍተኛ ሊባል የሚችል ነው። በሰው ህይወት እና በአካል ላይም ጉዳት እንደደረሰ ነው ሪፖርት እየመጣ ያለው። ግችቱ ሙሉ በሙሉ ስላልበረደ ምን ያክል ሰው ላይ ጉዳት ደረሰ የሚለውን አላጣራንም" ሲሉ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የኮምዩንኬንሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ተናግረዋል።

Somalia Äthiopien Viehzucht-Nomaden
ምስል DW/J. Jeffrey

በባሌ ዞን ራይቱ ገልቢ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በተቀሰቀሰ ተመሳሳይ ግጭት አራት ሰዎች ሞተው ሶስት ሰዎች ሳይቆስሉ እንዳልቀረ ማንነታቸውን መግለጥ ያልፈለጉ የአይን እማኝ ይናገራሉ። "በሁለቱ የድንበር አዋሳኝ ህዝቦች መካከል ዛሬ ጠዋት የጀመረ ጦርነት ነው።" የሚሉት የአይን እማኝ "የሶማሌ ልዩ ፖሊሶች" ቡራ የተባለ ቦታን በመቆጣጠራቸው ግጭቱ መቀስቀሱን ተናግረዋል። "እዚህ አካባቢ ያለው ነዋሪው ቦታውን {መልሶ} ከተቆጣጠረ በኋላ እንደገና ቀለበት ውስጥ ከተዋቸው ብዙ ሰው እንደገደሉብን ነው የሚነገረው" ሲሉም አክለዋል። "እስካሁን ሶስት የቆሰለ ሰው እና አራት የቆሰለ እንዳለ ነው የሚወራው" የአይን እማኙ እንደሚሉት ግጭቱ ከተጋጋለ በኋላ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ከጊኒር ከተማ ወደ አካባቢው ሲንቀሳቀሱ ተስተውሏል።

አቶ አዲሱ አረጋ በባሌ ዞን ተመሳሳይ ግጭት ተቀስቅሶ እንደነበር ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል። አቶ አዲሱ የአካባቢው ማኅበረሰብ ግጭቱን ቶሎ እንዲቆም አድርጎታል ብለዋል። ሰሞኑን ሰላም አጥታ የሰነበተችው የምኤይሶ ከተማም መረጋጋት እንደራቃት ትገኛለች። "ትናንትና እና ዛሬ በምዕራብ ሐረርጌ በኩል ምዔይሶ ከተማ ላይ ተኩስ ተከፍቶ የጸጥታ ሁኔታ የደፈረሰበት ሁኔታ ነው ያለው" ብለዋል አቶ አዲሱ።

ከ1,000 በላይ ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ድንበር ያላቸው ሁለቱ ክልሎች ባለፈው ሚያዝያ 29 ቀን  2009 ዓ.ም. ድንበራቸውን ለማካለል ሥምምነት ተፈራርመው ነበር። በተፈረመው ሥምምነት መሰረት ከጥቂት ቀበሌዎች በቀር የማካለሉ ሥራ እየተጠናቀቀ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ አዲሱ "እኛ የአስተዳደር ወሰንን ማካለል ብቻ ሳይሆን ዘላቂ ሰላም የሚመጣበትን መንገድ ተጨማሪ ርቀት ሔደን እየሰራን ነው ያለንው። ሕዝቡ በአብሮነት የቆየ የኖረ ነው። ግጭቱ የሕዝብ ለሕዝብ አይደለም። በእንደዚህ አይነት ትንኮሳዎች የሕዝቦች ወንድማማችነት፤የሕዝቦች አብሮነትን ካሁን በኋላ ችግር ላይ እንዳይወድቅ ጠንክረን ነው የምንሰራው።"

በዚህ ዘገባ ላይ የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትንም ይሁን የፌዴራል መንግሥትን አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልሰመረም።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሰ