1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሕግ እና ፍትሕኢትዮጵያ

የእነ ቀሲስ በላይ መኮንን የክስ መቃወሚያ ብይን

ሰኞ፣ ግንቦት 19 2016

ፍርድ ቤቱ በአዋጅ 882 መሰረት የቀረበው ክስ ከባድና ከ10 ኣመት በላይ እስር ፍርድ ስለሚያስከትል የዋስትና መብት ጥያቄውን በዛሬው ችሎት ውድቅ አድርጓል።ፍርድ ቤቱ ጠበቆች አቃቤ ህግ ሆን ብሎ በዚህ አዋጅ የከሰሰው የዋስትና መብት ለማስከልከል ነው ብለው ያቀረቡትንም መቃወሚያ በክስ ሂደት የሚጠራ መሆኑን ጠቅሶ ዋስትናውን ሳይፈቅድ አልፎታል፡፡

https://p.dw.com/p/4gLW0
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎትምስል Seyoum Hailu/DW

የእነ ቀሲስ በላይ መኮንን የክስ መቃወሚያ ብይን

 

ዛሬ ያስቻለው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሶስተኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ቀሲስ በላይ መኮንን በተጠረጠሩበት «ከባድ አታላይነት የሙስና ወንጀል እና ሰነዶችን አስመስሎ የማዘጋጀት» የክስ ሂደት ላይ የተከሳሾች ጠበቆች መቃወሚያ ብይን ለመስማት ቀርበዋል። በችሎቱ አንደኛ ተከሳሽ ቀሲስ በላይ ከሁለተኛ ተከሳሽ ጋር ቀርበው የክስ መቃወሚያ ብይናቸውን ስሰሙ የሶስተኛ ተከሳሽ የክስ መቃወሚያም ዛሬ በጠበቃቸው በኩል ቀርቧል፡፡ አራተኛ እና አምስተኛ ተከሳሾች ግን ዛሬም ስላልቀረቡ ፖሊስ በቀጣይ ችሎት እንዲያቀርባቸው አሁንም ትእዛዝ ተላልፏል፡፡

የዋስትና ጥያቄ ክርክር

ሶስቱ ተከሳሾች በቀረቡበት ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም. በዋለው ችሎት በተለይም የአንደኛ እና ሁለተኛ ተከሳሾች ጠበቆች በደንበኞቻቸው ላይ በሀሰተኛ ሰነድ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል በሚል የቀረበው ክስ፤ የመንግስት ወይም እንደ ባንክ ያሉ ህዝባዊ ድርጅት ሰራተኞች ባልሆኑበት የማታለል ወንጀል ክሱ የሙስና ወንጀሎች ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 32 (2/3) መሰረት የሚሸፈን አይደለም ብለው ተከራክረው ነበር የአቃቤ ህግ ክስ ላይ መቃወሚያቸውን ያቀረቡት፡፡ የቀሲስ በላይ መኮንን የችሎት ውሎጠበቆች አክለውም ተጎጂ ሊሆን ነበር በተባለው በህዝባዊ ድርጅቱ ላይ የደረሰ ጉዳት ወይም በተከሳሾች የተገኘው ጥቅም በሌለበት አግባብ አቃቤህግ ክሱን አክብዶ ያቀረበበት ሂደቱ አግባብነት የሌለውና ተከሳሾች የዋስትና መብት እንዳያገኙ ሆን ብሎ ያደረገው ነው በማለትም ክሱን ተቃውመውታል፡፡ ጠበቆች አክለውም ተከሳሾች በተለይም አንደኛ ተከሳሽ የሀይማኖት አባትና ተሰሚነት ያላቸው ግለሰብ እንደመሆናቸው፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪና ቋሚ አድራሻ ያላቸው መሆኑን እንዲሁም ታማሚ መሆናቸው ግንዛቤ ውስጥ ገብቶ በወንጀል ህግ ተጠይቀው የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው በሚል ተከራክረዋል፡፡ 

ቀሲስ በላይ መኮንን
ቀሲስ በላይ መኮንን ምስል Seyoum Getu/DW

በዚሁ የጠበቆች መቃወሚያ ላይ ዝርዝር ምላሽ የሰጠው ከሳሽ አቃቤህግ በተከሳሾች ሊደርስ የነበረው ጉዳት ከፍተኛ ስለነበር፤ በጸረ-ሙስና ልዩ የስነስርዓትና የማስረጃ ህግ አዋጅ ቁጥር 434/2005 እንዲሁም በአዋጅ 882/2007 በተሻሻለው አንቀጽ 2/3 መሰረት ከ10 ዓመት በላይ በሚያስቀጣ የሙስና ወንጀል የተከሰሱ በመሆኑ የዋስትና መብት በግልጽ ያስከለክላል በማለት መቃወሚያውን ውድቅ ይደረግ ሲል ሞግቷል፡፡ አቃቤህግ አክሎም ተከሳሾች “በወንጀሉ ሊያገኙት ነበር” ካለው “ያልተገባ ጥቅም” በተጨማሪ ካላቸው የገንዘብ አቅምና እውቅና አንጻር ወደ ውጪ ሊያወጡ የሚችሉ መሆኑን እንዲሁም “አሁንም በእስር ላይ ከሚገኙ ተከሳሾች ጋር በግብራበርነት የተሳተፉ” ያሏቸው ሌሎች ሁለት ተከሳሾች በምርመራ ወቅት ተፈልገው ያልተገኙ ከመሆኑ አንጻር “በህግም ሆነ በሁኔታ ሊሰጥ የሚችለው የዋስትና መብት ውድቅ እንዲደረግ” በማለት ፍርድ ቤቱ ወደ ቀጣይ የክርክር ሂደት እንዲገባም ጠይቋል፡፡የእነ ቀሲስ በላይ መኮንን የችሎት ውሎ

የዋስትና መከልከል ብይን

ይህን የግራ ቀኝ ክርክሩን ያደመጠው ፍርድ ቤቱ በተለይም በአዋጅ 882 መሰረት የቀረበው ክስ ከባድና ከ10 ኣመት በላይ እስር ፍርድ ስለሚያስከትል የዋስትና መብት ጥያቄውን በዛሬው ችሎት ውድቅ አድርጓል፡፡ ፍርድ ቤቱ ጠበቆች አቃቤ ህግ ሆን ብሎ በዚህ አዋጅ የከሰሰው የዋስትና መብት ለማስከልከል ነው ብለው ያቀረቡትንም መቃወሚያ በክስ ሂደት የሚጠራ መሆኑን ጠቅሶ ዋስትናውን ሳይፈቅድ አልፎታል፡፡

ቀሲስ በላይ መኮንን
ቀሲስ በላይ መኮንንምስል Privat

ፍርድ ቤቱ የክሱ ትክክለኛነትን በተመለከተ በጠበቆች የቀረበውን መቃወሚያ እና በጠበቆች መቃወሚያ ላይ ዛሬ ከሳሽ አቃቤህግ በጽሁፍ ያቀረበውን ምላሽ ተመልክቶ ብይን ለመስጠት ለግንቦት 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም በተመሳሳይ ጭብጥ የክስ መቃወሚያቸው ዛሬ በጠበቆች የቀረበው የሶስተኛ ተከሳሽ መቃወሚያ ላይም ከተለዋጭ ቀጠሮው አስቀድሞ የአቃቤ ህግ የጽሁፍ ምላሽ ተሰጥቶ አንድ ላይ ብይን እንዲሰጥ እና እስካሁን ያልተያዙ 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾችም በፖሊስ ተይዘው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ተላልፏል፡፡

ሊቀአዕላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን እና ሌሎች ተከሳሾች ዛሬ የዋስትና መብትን በፍርድ ቤቱ መነፈጋቸውን ተከትሎ ፖሊስ ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ብጠይቅም፤ ቀሲስ በላይ ያቀረቡት የህክምና ክትትል ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ እስከ ቀጣይ ቀጠሮ ግንቦት 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ብቻ አሁን በሚገኙበት ፖሊስ ጣቢያ እንዲቆዩ ችሎቱ አዟል፡፡

ሊቀ ዐዕላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን በሚያዚያ ወር መጀመሪያ የአፍሪካ ኅብረት ግቢ ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ በአካል በመቅረብ "ከኅብረቱ የክፍያ ሰነድ ጋር ተመሳስለው የተዘጋጁ" በተባሉ ሀሰተኛ ሰነዶች በመጠቀ ከስድስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ከህብረቱ የባንክ ሒሳብ ወደ ሌላ ሒሳብ ለማዘዋወር ሲሞክሩ ተገኝተዋል በሚል በፖሊስ መያዛቸው የሚታወስ ነው።

ስዩም ጌቱ 

ኂሩት መለሰ    

እሸቴ በቀለ