1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእሬቻ ሆራ-ፊንፊኔ አከባበር

ቅዳሜ፣ መስከረም 25 2017

“እሬቻ ሁለት ነው፡፡ አሁን የምናከብረው እሬቻ ቢራ የምንለው ከክረምት ወደ ቢራ ያጣታንን ፈጣሪ የሚመሰግንበት የምስጋና ኢሬቻ እና ከበጋ ወደ ክረምት ከመግባታችን በፊት ደግሞ የምናከብረው ለፈጣሪ ምህላ የምናቀርብበት ኢሬቻ አርፋሳ ናቸው” አባገዳ ገበየሁ አጀማ

https://p.dw.com/p/4lRIz
Oromo-Gemeinschaft feiert „Ericha“ - Erntedankfest in Äthiopien
ምስል Seyoum Getu/DW

ኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ በድምቀት ተከብሯል፡፡


የ2017 ዓ.ም. ኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ በድምቀት ተከብሯል፡፡
አባገዳዎች፤ ሃዳሲንቄዎች በህብረዜማ በበርካታም በኣሉ ታዳሚያን ህዝብ ታጅበው ዛሬ ጠዋት ማለዳውን አዲስ አበባ ውስጥ የዘንድሮ 2017 ዓ.ም. ኢሬቻ ሆራ-ፊንፊኔን አክብረዋል፡፡ አባገዳና አባመልካዎችም ለአእሬቻ ስነስርዓቱ በተሰናዳ ስፍራ ላይ ተገኝተው ስርዓቱን አከናውነው አባቶቹም የእሬቻ ስነስርዓቱን በምርቃት ከፍተዋል፡፡
 በየአቅጣጫው ወደ መስቀል አደባባይ እና ከእስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ጀርባ ባለውባለው ዶሎሎ ቡዴና ወደ ሚባለው የእሬቻ ስፍራ የሚተሙት የበዓሉ ታዳሚያን በተደጋጋሚ የሚደረጉትን ፍተሻ እና ጥብቅ የጸጥታ አካላቱ ክትትልም አልፈው ነው፡፡ በዚህም በዓሉ ሰላማዊ በሆነሁኔታ ተጠናቋል፡፡ አባገዳ ገበየሁ አጀማን በዚሁ በእሬቻ ስፍራ አግኝተን አነጋግረናቸዋል፡፡ “እሬቻ ሁለት ነው፡፡ አሁን የምናከብረው እሬቻ ቢራ የምንለው ከክረምት ወደ ቢራ ያጣታንን ፈጣሪ የሚመሰግንበት የምስጋና ኢሬቻ እና ከበጋ ወደ ክረምት ከመግባታችን በፊት ደግሞ የምናከብረው ለፈጣሪ ምህላ የምናቀርብበት ኢሬቻ አርፋሳ ናቸው” ብለዋል፡፡ በዓሉ የእርቅ የአንድነት እና የሰላም አምሳያ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

የ2017 ዓ.ም. ኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ በድምቀት ተከብሯል፡፡
የ2017 ዓ.ም. ኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ በድምቀት ተከብሯል፡፡ምስል Seyoum Getu/DW


እያደገ የመጣው ኢሬቻ..
አባገዳ ገበየሁ አክለውም ስለ በዓሉ አከባበር በሰጡትአስተያየታቸው፡ “በዓሉ ሲከበር ጎሳ እና ብሔር እንዲሁም ሃይማኖት አይለየም” በማለት ስፍራውንም ሆነ በዓሉን እንደ መገናኛ በመጠቀም ጉልህ የቱሪስት መስህብ ማድረግ እንደሚቻልም አመልክተዋል፡፡
አዩ ኮርሳ ደበላ ደግሞ ከዚሁ ከአዲስ አበባ በዓሉ ላይ ለመታደም ዘንድሮ ለስድስተኛ ጊዜ ስፍራው ላይ መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡ ዘንድሮ ለስድስተኛ ጊዜ እየተከበረ ያለውን ኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔን የተለየ በማለት ምልከታቸውን አጋርተዋል፡፡ “ድምቀቱና ስርዓቱ በጣም የተሸለ መሆኑን ተመልክቻለሁም” ብለዋል፡፡

“በዓሉ ሲከበር ጎሳ እና ብሔር እንዲሁም ሃይማኖት አይለየም” የበአሉ ታዳሚዎች
“በዓሉ ሲከበር ጎሳ እና ብሔር እንዲሁም ሃይማኖት አይለየም” የበአሉ ታዳሚዎችምስል Tiksa Negeri/REUTERS


የብሔር ብሔረሰቦች ተሳትፎ በእሬቻ
በርካታ ከተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች እንዲሁም ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎችም በእሬቻ ላይ ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡ ከሲዳማ ክልል መጥተው በዚህ በዓል ላይ የታደሙት የአገር ሽማግሌና አባገዳ አርገታ ዲቄ  “እሬቻ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በዓላቶቻቸውን በአንድነት የማክበር ባህላቸውን እያሳደጉ የመምጣታቸው ማሳያ ነው” በማለት ሃሳባቸውን አጋርተዋል፡፡
ከጌዴኦ ዞን በህብረት ከመጡት አንዱ ይስሃቅ ሎሎም አስተያየታቸውን ካጋሩን ናቸው፡፡ “በዓሉን ውብና ደማቅ በዛውም ከፍተኛ ማህበራዊ መስተጋብር የሚስተዋልበት ሆኖ ነው ያገኘሁት” ብለዋል፡፡
በዚህ በዓል ወጣቶች በጋራ በመሆን በባህል አልባሳት እሬቻን የማድመቁ ሁኔታ እየጎላ መጥቷል፡፡ ወደ 20 ግድም ጓደኛሞቹ ጋር በተመሳሳይ አልባሳት ከደመቁት መካከል ከቃሊቲ አከባቢ የመጣው ቦና አባድልቢ ሃሳቡን ያነሳል፡፡ “ተመሳሳይ ልብስ በያመቱ እየለበስን በዚህ ስፍራ እንገኛለን” ብሏል።
ሥዩም ጌቱ 
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር