1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኤች አይ ቪ ኤድስ ትኩረት ማጣት

ቅዳሜ፣ ኅዳር 21 2017

በጥናቱ መሰረት የኤች አይ ቪ ተሃዋሲ ስርጭት ላይ ይበልጥ ተጋላጭ የማህበረሰብ አካል በአፍላ እድሜ ላይ የሚገኙ ወጣት ሴቶች ናቸው፡፡ የተሃዋሲው የስርጭት ምጣኔም ከክልል ክልል ልዩነቶች ያሉት ቢሆንም አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ3.25 በመቶ የስርጭት ምጣኔ ከፍተኛው ነው፡፡

https://p.dw.com/p/4nbQW
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ምስል Seyoum Getu/DW

የኤች አይቪ ሥርጭት


በየዓመቱ በጎርጎሳውያን ዲሰምበር 01 ወይም ህዳር 22 የሚከበረው የዓለም የኤድስ ቀን ነገ እሁድ ህዳር 22 ቀን 2017 ዓ.ም. ለ37ኛ ጊዜ ይከበራል፡፡
በኢትዮጵያ ደግሞ ለ36ኛ ጊዜ የሚከበረው ይህ ቀን “ሰብዓዊ መብትን ያከበረየኤች አይ ቪ አገልግሎት ለሁሉም!” የሚል መሪ ቃል ተሰጥቶታል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር ከማህበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር ያስጠናውና በቅርቡ ተጠናቋል ባለው ጥናት መሰረት በአዲስ መልክ በቫይረሱ ከሚያዙ ዜጎች መካከል 70 በመቶ ያህሉ በአፍላ እድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እየተገባደደ ባለው የጎርጎሳውያን 2024 ያካሄደው ጥናታዊ ትንበያ እንደሚያሳየው፤ በኢትዮጵያ እድሜያቸው ከ15 በላይ በሆኑ ሰዎች መካከል የኤች አይ ቪ ስርጭት ምጣኔ 0.87 በመቶ ነው፡፡ በስሌቱ መሰረት ከ600 ሺህ በላይ ዜጎች ኤች አይ ቪ በደማቸው እንደሚገኝ፤ ከ7 ሺህ 400 በላይ ሰዎች በየዓመቱ አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ እንዲሁም ከ10 ሺህ በላይ የቫይረሱ ተጠቂዎች ደግሞ በበሽታው ሰበብ ህይወታቸውን ያጣሉ፡፡
የወጣቶች ተጋላጭነት መባባስ
በጥናቱ መሰረት የኤች አይ ቪ ተሃዋሲ ስርጭት ላይ ይበልጥ ተጋላጭ የማህበረሰብ አካል በአፍላ እድሜ ላይ የሚገኙ ወጣት ሴቶች ናቸው፡፡ የተሃዋሲው የስርጭት ምጣኔም ከክልል ክልል ልዩነቶች ያሉት ቢሆንም አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ3.25 በመቶ የስርጭት ምጣኔ ከፍተኛው ነው፡፡ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ እንዳሉትም “ከአዲስ አበባ ቀጥሎ ከዚህ በፊት በከፍተኛ የስርጭት መጠን የሚታወቀው ጋምቤላ ክልል ዘንድሮ በ3.24 በመቶ ሁለተኛ ሲሆን በሐረር 2.76፣ ድሬዳዋ 2.35፣ ትግራይ 1.2 እና በአማራ ክልሎች ከአጠቃላይ አገራዊ አማካይየስርጭት መጠን 0.87 በመቶ ከፍ ያለ የቫይረሱ ስርጭት ይታያል” ብለዋል፡፡ በአንጻሩ በሶማሌ ክልል ዝቅተኛ የሆነ 0.17 የተሃዋሲው ስርጭት ምጣኔ መኖሩም ተነግሯል፡፡
የተሃዋሲው ስርጭት በከተሞች 2.9 እና በገጠር 0.4 በመቶ እንደሆነም የተነገረ ሲሆን በዓመቱ በአዲስ በቫይረሱ ከሚጠቁ ከሰባት ሺህ በላይ ዜጎች 70 በመቶ ያህሉ ወጣቶች ስለመሆናቸው ተመላክቷል፡፡ ዶ/ር ደረጀ እንደሚሉትም “አፍላ ወጣት ሴቶች ላይ ስርጭቱ አሁንም ከፍተኛ እንደሆነ ማየት ይቻላል፡፡ በርግጥ ስርጭቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ መቀነስ ቢያሳይም አዲስ በቫይረሱ ከሚያዙ 70 በመቶው እድሜያቸው ከ15-29 የሚሆኑ ወጣቶች ናቸው፡፡ በተለይም በአፍላ እድሜ ላይ የሚገኙ ወጣት ሴቶች ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው” ነው ያሉት፡፡

በጥናቱ መሰረት የኤች አይ ቪ ተሃዋሲ ስርጭት ላይ ይበልጥ ተጋላጭ የማህበረሰብ አካል በአፍላ እድሜ ላይ የሚገኙ ወጣት ሴቶች ናቸው፡፡
በጥናቱ መሰረት የኤች አይ ቪ ተሃዋሲ ስርጭት ላይ ይበልጥ ተጋላጭ የማህበረሰብ አካል በአፍላ እድሜ ላይ የሚገኙ ወጣት ሴቶች ናቸው፡፡ ምስል Seyoum Getu/DW


የተሃዋሲውን ስርጭት የመቆጣጠር ውጥንና ተግዳሮቱ 
አገራት በ2030 ኤድስ የማህበረሰቡ የጤና ችግር ወደማይሆንበት ደረጃ ማድረስ የሚለውን ራዕይ ይዘው ስምምነቱን ለመተግበር በጥረት ላይ መሆናቸው ይነገራል፡፡ ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ የኤች አይ ቪ ስርጭት ምጣኔ በጎርጎሳውያኑ 2010 ከነበረበት 1.26 በመቶ አሁን ላይ ወደ 0.87 ዝቅ ማለቱ ነው የሚነገረው፡፡ ተሃዋሲው ከሶስት ዓመታት በፊት እንኳ ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ ምጣኔው 14.9 በመቶ ግድም ከነበረበት አሁን ላይ ወደ 8.6 ዝቅ ማለቱ ነው የተገለጸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ባጋጠሙ የተፈጥሮና ሰውሰራሽ አደጋዎች ምክንያት የኤች አይ ቪ ኤድስ መድሃኒትን ያቋረጡ ወደ ህክምና ተመልሰው አገልግሎቱን እንዲያገኙ ጤና ሚኒስቴር በትኩረት መስራቱም ተጠቁሟል፡፡
ኤች አይ ቪ ለመከላከል ከፌዴራል እስከ ታችኛው መዋቅር ተዘርግቶ የነበረው አደረጃጀት መፍረስ፣ የሚዲያ በጉዳዩ ላይ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ማቀዝቀዝ እና በአፍላ እድሜ  ላይ የሚገኙ ወጣቶች ላይ በትኩረት አለመስራት ደግሞ ለተፈለገው ውጤት አለመምጣት በተግዳሮት ተነስቷል፡፡ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ እንደሚሉት፤ በተለይም እንደ ኢንደስትሪ ፓርኮች እና አበባ ልማት ባሉ ተጋላጭ ወጣቶች በሚበራከቱባቸው አከባቢዎች የሚገኙ የጥናት ውጤቶች ተጨማሪ ትኩረት እንዲሰጣቸው አመላካች ነው፡፡ “በዚህ በርካታ ወጣቶች በተለይም ተጋላጭ የሆኑ ወጣት ሴቶች የሚበራከቱበት በመሆኑ ትኩረቱ በሚፈለገው ደረጃ አንዳለመሆኑ ባለድርሻዎች በትብብር መስራት አለባቸው” ነው ያሉት፡፡

ኤች አይ ቪ ለመከላከል ከፌዴራል እስከ ታችኛው መዋቅር ተዘርግቶ የነበረው አደረጃጀት መፍረስ ለመከላከሉ ሂደት እንቅፋት መሆኑን ተነግሯል
ኤች አይ ቪ ለመከላከል ከፌዴራል እስከ ታችኛው መዋቅር ተዘርግቶ የነበረው አደረጃጀት መፍረስ ለመከላከሉ ሂደት እንቅፋት መሆኑን ተነግሯልምስል UNAIDS


ቀጣዩ የበሽታውን ስርጭት የመቆጣጠር የትኩረት አቅጣጫ
አቶ ፍቃዱ ያደታ ደግሞ በኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ስራ አስፈጻሚ ናቸው፡፡ እንደሳቸው ገለጻ በወጣቶች ላይ ከፍ ብሎ የታየው የተዋሲው የስርጭት ምጣኔ ቫይረሱ ወረርሽኝ ሆኖ ዳግም እንዳይነሳ ሰፊ ስራ እንዲሰራ ጥቆማን የሰጠ ነው ብለዋል፡፡ “በግልጽ የሚታይ የማይደበቅ መዘናጋት አለ” ያሉት ኃላፊው አሁን ስራ ላይ ያውን የኤች አይ ቪ ኤድስመከላክልና ቁጥጥር ስልት የሚያተኩረው በተጋላጭ ማህበረሰብ ላይ እንደመሆኑ በወጣቶች ላይ በትምህርት ቤትም ሆነ ከዚያ ውጪ ያለው ግንዛቤ መቀዝቀዙን በጥናት መረጋገጡን አንስተዋል፡፡ በነዚህ ወጣቶች ላይ የቫይረሱ ስርጭት የ1.7 በመቶ ምጣኔ እንደሆነም በማስታወስ ይህ የቀጣዩ የስራ ትኩረታቸው አካል እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡  
ላለፉት ዓመታት በከፍተኛ ግጭት ውስጥ በነበረው በተለይም በሰሜን ኢትዮጵያ አከባቢ የተሃዋሲው ስርጭት ይታወቃል ወይ በሚል ጥያቄም ቀርቦላቸው፤ “በወቅቱ የጤና መሰረተ ልማቶች ከፍተኛ ጉዳት” ማስተናገዱን ገልፀው፤ አሁን ላይ ከ94 በመቶ የላቀውን አገልግሎት ወደ ስፍራው መመለሱን አስረድተዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር