1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኤርትራ ወታደሮች አሁንም ትግራይ ክልል ውስጥ ይገኛሉ?

ሰኞ፣ የካቲት 25 2016

የኤርትራ ጦር በኃይል ከያዘው የኢትዮጵያ ግዛት እንዲወጣ፥ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት «ኃላፊነቱ ሊወጣ ይገባል» ሲል የትግራይ ክልል ግዚያዊ አስተዳደር ጥሪ አቀረበ። የኤርትራ መንግሥት በበኩሉ፥ የያዘው የኢትዮጵያ ሉአላዊ ግዛት እንደሌለ ይገልፃል።

https://p.dw.com/p/4d9Ay
የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ድንበር ጋር አንድ ወታደር ቆሞ
እጎአ ህዳር 22 ቀን 2020 ዓ ም ሁመራ ምስል Eduardo Soteras/AFP/Getty Images

የኤርትራ ወታደሮች አሁንም ትግራይ ክልል ውስጥ ይገኛሉ?

በትግራዩ ጦርነት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ወግነው በትግራይ ሲዋጉ የነበሩ የኤርትራ ኃይሎች፥ ጦርነቱ በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ከተቋጨ በኋላ ጭምር ከተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች አለመውጣታቸው በክልሉ አስተዳደር ብቻ ሳይሆን በአውሮፓ ሕብረት እና አሜሪካ ጨምሮ በተለያዩ አካላት ሲገለፅ ቆይቷል። 

በቅርቡ ለዚህ ተደጋጋሚ ክስ ምላሽ የሰጠው በእንግሊዝ የሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲ፥ የኤርትራ ጦር በትግራይ ግዛት ውስጥ እንደሌለ ገልጿል። ባድመን ጨምሮ ሌሎች አሁን ላይ በኤርትራ ጦር የተያዙ አካባቢዎች ህወሓት በሕገወጥ መንገድ ለሁለት አስርት ዓመታት ይዟቸው የቆዩ የኤርትራ ሉአላዊ ግዛቶች ናቸውም ሲል ገልጿል።

የኤርትራ ጦር በምስራቅዊ እና ሰሜን ምዕራብ የትግራይ ዞኖች ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች መኖራቸው በተደጋጋሚ የሚገልፀው የትግራይ ክልል ግዚያዊ አስተዳደር፥ እነዚህ በኢትዮጵያ ሉኣላዊ ግዛት ያሉ የውጭ ሐይሎች በኃይል ከያዙት ግዛት የማስወጣት እና የተፈናቀሉ ዜጎች የመመለስ ኃላፊነት የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት መሆኑን ይገልፃል። ለዶቼቬለ የተናገሩት የትግራይ ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ፅሕፈት ቤት ሐላፊ አቶ ረዳኢ ሓለፎም የኤርትራው ኤምባሲ መግለጫ፥ የኤርትራ ጦር የተለያዩ የትግራይ ክልል አካባቢዎች በሐይል ተቆጣጥሮ እንዳለ አመላካች ብለውታል። 

Äthiopien I Konfliktregion Tigray
የኢትዮጵያ መንግሥት ወታደሮች እጎአ መጋቢት 7 ቀን 2021 ዓ ም በመቀሌ ከተማምስል Minasse Wondimu Hailu/AA/picture alliance

የኮምኒኬሽን ፅሕፈት ቤት ሐላፊው አቶ ረዳኢ ሓለፎም፥ ከአልጀርስ ውል አፈፃፀም ጋር የተያያዘ ጉዳይም፥ በሐይል የተወረረው መሬት ከተመለሰ በኃላ በሕጋዊ እና ዓለምአቀፋዊ መንገድ ሊፈፀም የሚችል ብለውታል። 

ከዚህ በተጨማሪ አቶ ረዳኢ በዚህ ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግሥት "ማለት ያለበትን ማለት አለበት። ኃላፊነቱ መወጣት አለበት" ብለዋል። 

በትግራይ የኤርትራ ጦር ብቻ ሳይሆን የአማራ ክልል ታጣቂዎች ጭምር መኖራቸው ጨምረው የገለፁት ሐላፊው ይህ የፕሪቶርያው የሰላም ውል የሚፃረረ፣ በትግራይ ያለው አሳሳቢ የተፈናቃዮች ችግር እንዳይፈታ እንቅፋት የሆነ ብለውታል።

ሚሊዮን ኃይለስላሴ
ልደት አበበ
ነጋሽ መሀመድ