1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮ ቴሌኮም አሥር በመቶ ድርሻ ለሽያጭ ቀረበ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 6 2017

እርምጃው የ130 ዓመቱን የመንግሥት የልማት ድርጅት ወደ አክሲዮን ማሕበር የቀየረ ነው ተብሎለታል።ኢትዮ ቴሌኮም ይህንኑ የድርሻ ሽያጩን ቴሌብር በተባለው የኩባንያውን የግብይት መተግበሪያ በመጠቀም እንደሚያከናውነው ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/4lssM
Äthiopien Addis Abeba 2024 | Ethio Telecom CEO Frehiwot Tamiru präsentiert Investitionsmöglichkeiten
ምስል Solomon Muche/DW

ኢትዮ ቴሌኮም ለኢትዮጵያዉያን ያቀረበው የድርሻ ሽያጭ ሲዳሰስ

የኢትዮ ቴሌኮም አሥር በመቶ ድርሻ ለሽያጭ ቀረበ

 

ኢትዮ ቴሌኮም ከዛሬ ጀምሮ አሥር በመቶ ድርሻውን ለኢትዮጵያውያን መሸጥ ጀመረ።

 

እርምጃው የ130 ዓመቱን የመንግሥት የልማት ድርጅት ወደ አክሲዮን ማሕበር የቀየረ ነው ተብሎለታል።ኢትዮ ቴሌኮም ይህንኑ የድርሻ ሽያጩን ቴሌብር በተባለው የኩባንያውን የግብይት መተግበሪያ በመጠቀም እንደሚያከናውነው ተገልጿል።

አካታች ሀብትን የመፍጠር እድል የፈጠረ ነው የተባለለት ይህ የአክሲዮን ሽያጭ የኩባንያውን 100 ሚሊየን ብር ድርሻ ለኢትዮጵያውያን ለሽያጭ ያቀረበ ሲሆን ሥራውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ማምሻውን አስጀምረውታል።

ኢትዮጵያን ዲጂታል የማድረግ ውጥን፡ ኢትዮ ቴሌኮም
 

ኢትዮ ቴሌኮም አጠቃላይ የሀብት ግምቱ 100 ቢሊዮን ብር መሆኑን የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ በዚሁ የሽያጭ ሥነ ሥርዓት ማስጀመርያ ላይ ተናግረዋል።

"ሁሉም ማህበረሰብ የልማት ተጋሪ እንዲሆን የሚያደርግ ነው" የተባለለት ይህ የኢትዮ ቴሌኮም የአክሲዮን ሽያጭ ላይ አንድ ሰው ዝቅተኛ ድርሻ መግዛት የሚችለው 33 ድርሻዎችን ሲሆን ይህም 9900 ብር ነው። ከፍተኛ የአክሲዮን ሽያጩ ደግሞ 3333 ድርሻ ሲሆን በብር 999, 900 ይሆናል ተብሏል።

የኩበንያው የአክሲዮን ሽያጭ ከዛሬ ረቡዕ ጥቅምት 6 ቀን 2017 ዓ.ም እስከ ታህሳስ 25 ይቆያል ተብሏል። ሆኖም ሽያጩ ከዚያ ቀድሞ የሚጠናቀቅ ክሆነ ግን ሽያጩ እንደሚዘጋ ተነግሯል።

ኢትዮ-ቴሌኮም ስኬታማ ነኝ ሲል፣ ደንበኞቹ ግን አጥጋቢ አገልግሎት አይሰጥም ብለዋል

ሁለተኛው ምዕራፍ የድርሻ ሽያጭ ወደፊት ይቀጥላል ተብሏል። በሁለተኛው ሽያጭ የተገዙ ድርሻዎችን ለግብይት ማቅረብ የሚያስችል፣ መልሶ ለመሸጥ እና ለማስትላለፍ ዕድል የሚሰጥበት ነው ተብሏል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይህን መሰሉ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል የማዞሩ ሥራ በሌሎች ኩባንያዎችም ይቀጥላል ብለዋል።

ይህን መሠሉ ሥራ "የፕራይቬታይዜሽን አንዱ ተቀጥላ ነው" ያሉት የፋይናንስና የኢኮኖሚ አማካሪና መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ዳዊት ታደሰ ሂደቱ መንግሥት ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዞር የያዘው ጥረት አካል መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ጋዜጣዊ መግለጫ

ይህንን ሥራ ወደ ተግባር ለማምጣት ከአንድ ዓመት ጊዜ በላይ ወስዷል ተብሏል። ኢትዮ ቴሌኮም በ2016 በጀት ዓመት 93 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ማስታወቁ ይታወሳል።

ሰለሞን ሙጬ

ታምራት ዲንሳ

ሸዋዬ ለገሰ