1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮ-ሶማሊያ ዲፕሎማሲያዊ ትኩሳት ወዴት ?

ቅዳሜ፣ መጋቢት 28 2016

ራስ ገዟ ሶማሌ ላንድ እና ከፊል ራስ ገዟ ፑንትላንድ ፤ የሶማሊያ ፌዴራል ሪፐብሊክ ኢትዮጵያ በሁለቱም ግዛቶች የሚገኙ የቆንስላ ጽህፈት ቤቶቿ እንዲዘጉ ያስተላለፈችውን ዉሳኔ አንቀበልም ብለዋል። የኢትዮጵያውን አምባሳደር በ72 ሰዓታት ጊዜ ውስጥ ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ተነግሯቸዋል።

https://p.dw.com/p/4eUnW
Äthiopien Addis Abeba | Treffen AU | Somalia Präsident  Hassan Sheikh Mohamud
ምስል REUTERS

የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት እየተካረረ ሄዷል

ራስ ገዟ ሶማሌ ላንድ እና ከፊል ራስ ገዟ ፑንትላንድ ፤ የሶማሊያ ፌዴራል ሪፐብሊክ ኢትዮጵያ በሁለቱም ግዛቶች የሚገኙ የቆንስላ ጽህፈት ቤቶቿ እንዲዘጉ ያስተላለፈችውን ዉሳኔ አንቀበልም ብለዋል።  

የኢትዮጵያውን አምባሳደር በ72 ሰዓታት ጊዜ ውስጥ ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ እንደተነገራቸው የሶማሊያ ጠቅላይ ሚንስቴር ጽህፈት ቤት ባለፈው ሐሙስ ዐስታውቋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በበኩሉ ሶማሊያ ስለወሰደችው እርምጃ መረጃ የለኝም ብሏል። ለመሆኑ የሶማሊያ ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወዴት እያመራ ይሆን ? የሶማሊያ እርምጃስ በእርግጥ መሻቷን ይሞላላት ይሆን ወይስ ሌላ መዘዝ ይዞባት ይመጣ ይሆን ቀጣዩ ዘገባችን ከብዙ በጥቂቱ ይመለከተዋል። 
ሶማሊያ የኢትዮጵያውን አምባሳደር ሙክታር ሞሀመድ  በ72 ሰዓታት ውስጥ ሀገር ለቀው እንዲወጡ ስታዝ በአንጻሩ አዲስ አበባ የሚገኙ አምባሳደሯን «ለምክክር» ወደ ሞቃዲሾ ጠርታለች። 


የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው ሐሙስ ይፋ ባደረገው መግለጫው « ኢትዮጵያ በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባትን ጨምሮ የሶማሊያን ሉአላዊነት በሚገዳደሩ ተግባራት በመሰማራቷ» እርምጃው ተወስዷል ፤ ብሏል። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ ነብዩ ተድላ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው መረጃ የለንም የሚል አጭር መልስ መስጠታቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል። 
ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሌላንድ ጋር ከወራት በፊት የጦር ሰፈር ምስረታ እና የወደብ ኪራይ ስምምነት መፈጸሟ ከሶማሊያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ መሻከር ውስጥ አስገብቷታል።

የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሐመድ ከልዑካናቸው ጋር
ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሌላንድ ጋር ከወራት በፊት የጦር ሰፈር ምስረታ እና የወደብ ኪራይ ስምምነት መፈጸሟ ከሶማሊያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ መሻከር ውስጥ አስገብቷታል። ምስል MICHELE SPATARI/AFP

በቅርቡ ደግሞ ለሶማሊያ ፌዴራል ሪፐብሊክ እውቅና እንደማትሰጥ ያስታወቀችው ፑንትላንድ የውጭ ግንኙነቱን በራሴ እወጣዋለሁ ማለቷ እና የገንዘብ ሚንስትሯ ከሶማሊያ ፌዴራል መንግስት እውቅና ውጭ በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጋቸው የሃገራቱን ዲፕሎማሲያዊ መሻከር ቀውስ ውስጥ ከቶታል።

ዶ/ር አደም ካሴ ባለሞያ እና የምስራቅ አፍሪቃ እና የአፍሪቃ ቀንድ አካባቢዎች ቀጣናዊ ጉዳዮችን በቅርበት ይከታተላሉ ። የኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ ስምምነት ፣ የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ


ሶማሊያ የኢትዮጵያውን አምባሳደር አባራ በምትኩ የራሷን ወደ ሀገር ቤት መጥራቷ በሃገራቱ መካከል የተፈጠረው ዲፕሎማሲያዊ መሻከር ለመባባሱ ማሳያ ነው ይላሉ ።
«ሁኔታው ከዚህ በፊት በተለይ የኢትዮጵያ መንግስት እና የሶማሌ ላንድ አስተዳዳሪዎች የተፈራረሙትን ውል ተከትሎ ሁኔታው ትንሽ ውጥረት የነገሰበት ነበር። አሁን የምናየውም ከዚያ ቀጥሎ ነገሮች እየተጠናከሩ እና እየተካረሩ መሄዳቸውን ነው የሚያሳየው ። » 


ሶማልያ ለሉአላዊነቷ እና የግዛት አንድነቷ አለመከበር በዋናነት ኢትዮጵያን ተጠያቂ ታድርግ እንጂ ከሶስት አስርት አመታት በላይ የሀገር ያህል ራሷን በማስተዳደር ላይ በምትገኘው እና በቅርቡ ደግሞ ለፌዴራሉ መንግስት ዕውቅና በነፈገችው ፑንትላንድ ላይ የሚኖራት ተጽዕኖ ያን ያህል አይደለም።

ለዚያም ይመስላል ሶማሊያ  በሁለቱ ግዛቶች የሚገኙ የቆንስላ ጽህፈት ቤቶች እንዲዘጉ ትዕዛዝ ብታስተላልፍም ሰሚ አጥታ ቆንስላዎቹ በነበሩበት ስራቸውን ስለመቀጠላቸው የተሰማው ።

የሶማሊላንድ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ርሆዳ ኤልሚሴይድ እና የፑንትላንዱ የኢንፎርሜሽን ሚንስትር አይዲድ ዲሪር በየግዛቶቹ የሚገኙ የቆንስላ ጽህፈት ቤቶች ስራቸውን ስለመቀጠላቸው ለሮይተርስ የዜና ወኪል ማረጋገጫ ሰጥተዋል። 

የኢትዮጵያ ፣ ኤርትራ እና የቀድሞ ሶማሊያ መሪዎች
የኢትዮጵያ መንግስት አሁን ሶማሊያ ውስጥ ያለው ወታደር ለሶማሊያ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያም የሚጠቅም ነገር ነው ። በተለይ አልሸባብ እየጠነከረ የሚሄድ ከሆነ አደጋው ለሶማሊያ ብቻ ሳይሆን በተለይ ለኢትዮጵያ እና በአጠቃላይ ለአካባቢውም ጭምር ነው።ምስል Eduardo Soteras/AFP/Getty Images

ግዛቶቹ ከፌዴራሏ ሶማሊያ በተቃርኖ ምንም እንኳ ዓለማቀፉ ማህበረሰብ ሶማልያን ሳይከፋፍል ዕውቅና ቢሰጥም ሶማሊያ ሳትከፋፈል እንደ ሀገር አብራ መቀጠል አለመቻሏ የፈጠረው ችግር ለዚህ እንዳጋለጣት  ዶ/ር አደም ይናገራሉ ።


« የሶማሊያ ከ90ዎቹ በፊት በነበረችበት አቋም እንደ ሀገር አብራ አለመቀጠሏ ፤ በዚያ ውስጥ የሶማሌ ላንድ ራsሷን የቻለች ፣ ዓላማዋም ሀገር የመሆን ነው ፤ ፑንትላንድ ሀገር የመሆን ዓላማ ባይኖራትም በተቻለ መጠን ከፍተኛ የሆነ የስልጣን ወደ ክልሎች ወደ እርሷ እንዲዞር የምትፈልግበት ሂደት ፣ ከ90ዎቹ በኋላ የመጡ የፖለቲካ እና የኤኮኖሚ ስረዓት የፈጠረው ነው።»

የሶማሊያ እና የቱርክ ስምምነት አንድምታዎች

ኢትዮጵያ በሶማሊያ ከ10 ዓመታት ለተሻገረ ጊዜ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ሰራዊቷን በማስፈር ከእስላማዊ ታጣቂ ቡድን አልሸባብ ጋር ስትዋጋ ኖራለች፤ በርካታ ወታደሮቿም ተገድለውባታል። የኢትዮጵያ ወታደሮች ወደ ሶማሊያ መዝመት አልሸባብን ከመዲናዪቱ ከማባረርም ባሻገር ለኢትዮጵያ የስጋት ምንጭ እንዳይሆን እስከ መከላከልም አድርሶታል። 


የሰሞንኛው የሀገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ቀውስ ሶማሊያ የኢትዮጵያ ወታደሮች ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ አልያም ኢትዮጵያ በራሷ ተነሳሽነት ወታደሮቿን ታስወጣ ይሆን ? የአፍሪቃ ቀንድ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በቅርበት የሚከታተሉት አደም ካሴ የራሳቸው ምልከታ አላቸው።


« የዓለም አቀፍ ግንኙነቶች በተለይ በሀገራት መካከል ያሉት ውስብስብ ናቸው ። በአንዳንድ ነገሮች ላይ እየተጣላክ እየተጋፈጥክ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ደግሞ እየተከባበርክ የምትሄድበት ነው ። የኢትዮጵያ መንግስት አሁን ሶማሊያ ውስጥ ያለው ወታደር ለሶማሊያ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያም የሚጠቅም ነገር ነው ።

በተለይ አልሸባብ እየጠነከረ የሚሄድ ከሆነ አደጋው ለሶማሊያ ብቻ ሳይሆን በተለይ ለኢትዮጵያ እና በአጠቃላይ ለአካባቢውም ጭምር ነው።

ከዚህ አንጻር ግንኙነቱ በቀላሉ የሚሻክር አይሆንም ። ነገር ግን ይህ እሰጣገባው የሚቀጥል ከሆነ የኢትዮጵያ መንግስት በራሱ ፈቃድ የማስወጣት ፍላጎት እንኳ ባይኖረው ሶማሊያ በሌላ ሀገር ወታደሮች የመተካት  አዝማሚያ ሊኖር ይችላል።»
ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የደረሰችው የጦር ሰፈር እና የወደብ ኪራይ ስምምነት ወራት ቢያስቆጥርም የስምምነቱ ተግባራዊነት አንድ እርምጃ ፈቀቅ አላለም ፤ አልያም አልታጠፈም ።

የኢትዮጵያ ወታደሮች
የሰሞንኛው የሀገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ቀውስ ሶማሊያ የኢትዮጵያ ወታደሮች ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ አልያም ኢትዮጵያ በራሷ ተነሳሽነት ወታደሮቿን ታስወጣ ይሆን ? የሚሉ ጥያቄዎች ሲነሱ ይሰማሉምስል Million Hailessilasie/DW

ስምምነቱን ተከትሎ የኢትዮጵያን ድርጊት አምርራ ያወገዘችው ሶማሊያ በፕሬዚዳንቷ አማካኝነት ተገቢ ነው የምትለውን ዕርምጃ እንደምትወስድ በተደጋጋሚ ስታሳውቅ ቆይታለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ሶማሊያ በራሷ የህገ መንግስት ማሻሻያ ለማድረግ መወሰኗን ተከትሎ ከከፊል ራስ ገዟ የአላውቅሽም እንዲያውም የውጭ ግንኙነት ስራዎቼን በራሴ እወጣለሁ ምላሽ ማግኘቷ ለፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ ሙሐመድ አስተዳደር ሌላ ራስ ምታት ሆኗል።

የሆነ ሆኖ የአፍሪቃ ቀንድ ዲፕሎማሲው አብጧል። የአፍሪቃ ህብረት እና የመንግስታቱ ድርጅትን ጨምሮ ጣልቃ ገብተው ነገሮችን ያረጋጉ ይሆን ወይስ   ቀጣዮቹ ቀናት ሌላ ቀውስ ይዘው ይመጡ ይሆን ለጊዜው አይታወቅም ። 

ታምራት ዲንሳ