1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ፖለቲካ መዋቅራዊ መዛቦቶች እና መፍትሔያቸው

ሰኞ፣ ሚያዝያ 7 2016

ኢትዮጵያ እየሰፋ የመጣዉ "መዋቅራዊ መዛባቶች" እንዲቀረፉ ምን ይደረግ ? የሚለው ጉዳይ አሁንም አሳሳቢነቱ ቀጥሏል። አንዳንዶች ኢትዮጵያ ለገጠማት ውስብስብ ችግር እውነተኛና አካታች ውይይትና ድርድር ሲሉ ሌሎች ሀገሪቱ ከሌላው ዓለም እኩል እንድትራመድ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ማድረግን ጨምሮ የሽግግር መንግሥትን እንደ መፍትሔ አማራጭ ያቀርባሉ።

https://p.dw.com/p/4elvK
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ)
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ምስል Ethiopian Human Rights Council

የኢትዮጵያ ፖለቲካ መዋቅራዊ መዛቦቶች እና መፍትሔያቸው

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚያስከትሉት ጉዳት እየሰፋ የመጣ "መዋቅራዊ መዛባቶች" እንዲቀረፉ ምን ይደረግ ? የሚለው ጉዳይ አሁንም አሳሳቢነቱ ቀጥሏል። አንዳንዶች ኢትዮጵያ ለገጠማት ውስብስብ ችግር እውነተኛና አካታች ውይይትና ድርድር ከሁሉም ወገን ጋር ማድረግ የሚል ሀሳብ ያቀርባሉ።

በተመሳሳይ ሌሎች ሀገሪቱ ከሌላው ዓለም እኩል እንድትራመድ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ማድረግን ጨምሮ የሽግግር መንግሥትን እንደ መፍትሔ አማራጭ ያቀርባሉ።

ሀገሪቱ በሚገጥማት ፈታኝ የፀጥታ ችግሮች ምክንያት የአስቸኳይ ጌዜ አዋጅ ከመደንገግ እስከታጣቂ ቡድኖችን በሽብር ፈርጆ እርምጃ እስከመውሰድ ደርሳለች። ያም ሆኖ ችግሮች አልተቀረፉም።

መንግሥት ከዚህም ባሻገር ችግሮችን ለመፍታት የምክክር ኮሚሽን እና የሽግግር ፍትሕ አማራጮች ላይ አተኩሮ እየሠራ መሆኑን ገልጿል። ያነጋገርናቸው አንድ አስተያየት ሰጪ ለሁሉም ነገር መፍትሔው "በሕግ እና በሥርዓት ፣ በጊዜና በድርጊት የተገደበ" የመንግሥት አስተዳደር ማዋቀር ነው ይላሉ።

የኢትዮጵያ ነባራዊ ችግሮች

ኢትዮጵያ አንድም በጎሳ ማንነት “እኛና እናንተ”የሚል በጉልህ የሚንፀባረቅ ልዩነት የሚታይባት፣ አስከፊ ውጤት ያለው ድርጊትም የሚታይባት እየሆነች ነው። ሃይማኖትን የመሰል ችግር ምንጭ የሚያደርጉ አስተሳሰቦችም በግለሰቦች መራመዳቸው እየጎላ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንምስል Solomon Muche/DW

ልቅ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አጠቃቀም የሚፈጥረው ጥላቻ ፣ የበቀለኝነት ስሜት ለችግሮች መባባስ እያገዘ ነው። በየጊዜው የሚደመጡ የሰላም ጥሪዎች ወደ ጎን እየተባሉ ሕግን ያለመፍራት ፣ ተጠያቂነትን ማናናቅም እየተለመደ እንደ እገታ እና የደኅንነት ሥጋት የመሰሉ ክስተቶች እንዲጎሉ አድርጓል። ምልከታዎች ይህንን ያሳያሉ። ይህ ለምን ሆነ? ያነጋገርናቸው አንድ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ንቁ ተመልካች ስማቸውን ሳይጠቅሱ ሀሳባቸውን አጋርተውናል።

የመንግሥት የመፍትሔ ትልሞች

ኢትዮጵያ ውስጥ በልሂቃን አዋቆች መካከል በሀገራዊ ጉዳዮችመግባባት መራቁ ብቻ ሳይሆን አለመተማመናቸው እና በመካከላቸው ያለው ጥርጣሬ “ለዴሞክራሲያዊ የሽግግር ሂደት ፈታኝ” መሆኑ የምክክር ኮሚሽን ተዋቅሮ ዘላቂ መፍትሔ የሚሰጥ ጭምቅ ሀሳብ እንዲወልድ ሥራ ከጀመረ ሁለት ዐመታት ተቆጥረረዋል። መንግሥት ከዚህም ባለፈ የሽግግር ፍትሕን ለመተግበር በዝግጅት ላይ ነው።

ፎቶ ማህደር፤ መንግሥት በአማራ ክልል የሚካሄድ ጦርነት ያቁም ተቃዉሞ በጣልያን
ፎቶ ማህደር፤ መንግሥት በአማራ ክልል የሚካሄድ ጦርነት ያቁም ተቃዉሞ በጣልያን ምስል Marcello Valeri/ZUMA/picture alliance

ይህ እንዳለ ሆኖ በሀገሪቱ "በሕግ እና በሥርዓት ፣ በጊዜና በድርጊት የተገደበ" የመንግሥት አስተዳደር ማዋቀርን እንደ ሁነኛ መፍትሔ የሚያቀርቡት ያነጋገርናቸው ግለሰብ መንግሥት በተለይ ለፀጥታ እና የደኅንነት ጉዳዮች አናሳ ግምት መስጠቱን መታዘባቸውን ያብራራሉ።

ውይይት ለምን ጉልበት አጣ?

ውይይት መፍትሔ መሆኑ ከታመነበት ለምን አልተቻለም? ነባር ፖለቲከኛው ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እነደሚሉት “ፖለቲካው ጫካ ገብቷል”። በጦርነት ፣ በትጥቅ ግጭት ፣ በሃይማኖትና በጎሳ ማንነት እና ፍላጎት ከሚስተዋለው ጭካኔ የተሞላበት መገዳደል እስከ እገታ እና  መንቀሳቀስ ያለመቻል ችግር የተወጠረችው ኢትዮጵያ ምን ብታደርግ ይበጃል?

ሰለሞን ሙጬ

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ