1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ገበያ ለውጭ ባለወረቶች ሲፈቀድ ባለሙያዎች ተስፋ እና ሥጋት ተሰምቷቸዋል

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 9 2016

የኢትዮጵያ መንግሥት የችርቻሮ ንግድ ለውጭ ባለወረቶች ሲፈቅድ ከ2 ሺሕ-10 ሺሕ ስኩዌር ሜትር የሚሰፉ ሱፐርማርኬቶች እንዲገነቡ ይፈልጋል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ መመሪያ በወጪ፣ ገቢ እና ጅምላ ንግድ ዘርፎች የውጭ ባለወረቶች እንዲሳተፉ የሚፈቅድ ነው። የመንግሥት ጉልህ ፖሊሲ ለውጥ ለአንዳንድ ባለሙያዎች ተስፋ ለሌሎች ሥጋት ያጫረ ሆኗል።

https://p.dw.com/p/4etWA
ለኢትዮጵያ ሸቀጥ የጫነ ኮንቴይነር
የኢትዮጵያ መንግሥት ጉልህ የፖሊሲ ለውጥ ሲያደርግ ለሀገር ውስጥ ነጋዴዎች ብቻ ተከልለው በቆዩ የወጪ እና ገቢ ንግድ ዘርፎች የውጭ ባለወረቶች እንዲሰማሩ ፈቅዷልምስል Everyonephoto/Pond5 Images/IMAGO

የኢትዮጵያ ገበያ ለውጭ ባለወረቶች ሲፈቀድ ባለሙያዎች ተስፋ እና ሥጋት ተሰምቷቸዋል

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ለኢትዮጵያውያን ነጋዴዎች ተከልለው በቆዩ ዘርፎች የውጭ ባለወረቶች እንዲሰማሩ ሲፈቅድ እርምጃውን በሚከታተሉ ባለሙያዎች ዘንድ ተስፋም ሥጋትም ይታያል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት የኢንቨስትመንት ቦርድ ይፋ ያደረገው መመሪያ የኢትዮጵያ መንግሥት በገቢ፣ ወጪ፣ የጅምላ እና ችርቻሮ ንግድ ዘርፎች ለበርካታ ዓመታት ሲከተል የቆየውን ፖሊሲ ሙሉ በሙሉ የቀየረ ነው።

የፖሊሲው ለውጥ መንግሥት ተግባራዊ የሚያደርገው ሀገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር አካል ነው። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት እስካሁን ተግባራዊ ባደረጋቸው ማሻሻያዎች ለነዳጅ ይደረግ የነበረውን ድጎማ ቀስ በቀስ እያነሳ ነው።

ለውድድር ተዘግቶ የቆየው የቴሌኮም ገበያ ተከፍቶ ሳፋሪኮም አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን በቅርቡ የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ ገበያ እንዲሠማሩ የሚፈቅደው ፖሊሲ ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

ለውጭ ባለወረቶች የተፈቀዱ የንግድ ሥራ ዘርፎች በሀገር ውስጥ አቅም “ዘላቂ ብሔራዊ ኤኮኖሚ ለመገንባት” ተከልለው የቆዩ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ ይፋ ያደረገው መመሪያ ይጠቁማል።

የሀገር ውስጥ ነጋዴዎችን ዕድገት በጥራት እና በመጠን ለማመቻቸት፣ ወደ ዓለም አቀፉ የእሴት ሰንሰለት እንዲዋሀዱ ለማድረግ እና በሒደት እሴት ወደ ተጨመረባቸው ኢንቨስትመንቶች ለማሸጋገር የንግድ ዘርፎቹ በሕግ ለውጭ ባለወረቶች ቢከለከሉም የመመሪያው መግቢያ እንደሚለው የታቀደው አልተሳካም።

የደብረ ማርቆስ ገበያ
የወጪ፣ ገቢ፣ የችርቻሮ እና ጅምላ ንግድ ዘርፎች ለኢትዮጵያውያን ብቻ የተፈቀዱ ሆነው ቢቆዩም መንግሥት በተከተለው ፖሊሲ እንደተጠበቀው ለውጥ አልመጣም። ምስል DW/E. Bekele

መመሪያውን የተመለከቱት ቲ ቤስት ሎው የተባለው የሕግ ተቋም ሸሪክ ዶክተር ታደሰ ሌንጮ “ከወጪ ንግድ የሚፈለገው የውጭ ምንዛሪ አልተገኘም። የሚፈለገው የቴክኖሎጂ ሽግግር አልተገኘም። የሚፈለገው ከፍተኛ የሆነ ተወዳዳሪነት አልተገኘም” የሚለው አመክንዮ በመመሪያው መግቢያ ዘርፎቹ ለመከፈታቸው በገፊ ምክንያትነት እንደተጠቀሰ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ መመሪያ ለሀገር ውስጥ ነጋዴዎች ተጠብቀው የቆዩት የሥራ ዘርፎች “በአገልግሎት ተደራሽነት፣ በጥራት እና በቅልጥፍና” ቅሬታ የሚቀርብባቸው እንደሆኑ ያትታል። በዘርፎቹ “ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሔድ ሕገ-ወጥ ድርጊቶች” መኖራቸውንም ይገልጻል።

በመመሪያ መሠረት ከዚህ በኋላ ፈቃደኛ የሆኑ የውጭ ባለወረቶች ጥሬ ቡና፣ ጫት፣ የዘይት እህሎች፣ ጥራጥሬ፣ ቆዳ፣ ሌጦ፣ የደን ምርቶች፣ ዶሮ እና የቀንድ ከብቶች ከገበያ ገዝተው ወደ ውጪ መላክ ይችላሉ። በዚህ ዘርፍ ለመሠማራት የሚፈልጉ የውጭ ባለወረቶች በውጭ ንግድ ልምድ፣ አቅም እና የገበያ ትሥሥር ሊኖራቸው ይገባል።

የውጭዎቹ ነጋዴዎች በመመሪያው የተፈቀዱ ሸቀጦችን ወደ ውጪ ሀገር ለመላክ ለእያንዳንዳቸው ግዴታ ተቀምጦባቸዋል። ለምሳሌ ያክል ጥሬ ቡና በዓለም አቀፍ ገበያ መሸጥ የሚፈልግ ነጋዴ ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት በአማካይ የ10 ሚሊዮን ዶላር ቡና ከኢትዮጵያ የገዛ መሆን እንዳለበት መመሪያው ያዛል። ከዚህ በተጨማሪ ኩባንያው ፈቃድ በተሰጠበት ዓመት 10 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ቡና ከኢትዮጵያ ገዝቶ በውጭ ገበያ ለመሸጥ ውል መግባት ይጠበቅበታል።

“ሊመጡ የሚችሉት አሁን እየገዙ ያሉ ችግር ያለባቸው ኩባንያዎች ናቸው። ትላልቅ ኮርፖሬት ኩባንያዎች የራሳቸውን ሱቅ እዚህ አቋቁመው የራሳቸውን ግዢ ሊፈጽሙ ይችላሉ” የሚሉት ዋይኤችኤም የተባለው የቢዝነስ እና የመዋዕለ-ንዋይ አማካሪ ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃይለመስቀል “ግዢ ሲፈጽሙ ቀጥታ ከገበሬው ጋር የመደራደር ዕድል ይፈጥርላቸዋል። ገበሬውንም በሚፈልጉት አይነት እንዲያመርት የማገዝ ዕድል ሊፈጥሩ ይችላሉ” ሲሉ ተስፋቸውን ገልጸዋል።

ቦንጋ ቡና ሲደርቅ
በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ መመሪያ መሠረት የውጭ ባለወረቶች ጥሬ ቡና፣ ጫት፣ የዘይት እህሎች፣ ጥራጥሬ፣ ቆዳ፣ ሌጦ፣ የደን ምርቶች፣ ዶሮ እና የቀንድ ከብቶች ከገበያ ገዝተው ወደ ውጪ መላክ ይችላሉ።ምስል DW/J. Jeffrey

ከቡና በተጨማሪ ለውጭ ባለወረቶች በተፈቀዱት ሸቀጦች የገንዘብ መጠኑ ቢለያይም ተመሳሳይ ቅድመ ሁኔታዎች ማሟላት እንደሚጠበቅባቸው መመሪያው ያዛል። የወጪ ንግድ ለውጭ ባለወረቶች ሲፈቀድ “ገበሬው ይጠቀማል” የሚሉት አቶ ያሬድ ኢትዮጵያ በዓለም ገበያ የምትሸጠው ሸቀጥ መጠን ሊጨምር እንደሚችል ተስፋ አድርገዋል። ይሁንና አቶ ያሬድ እንደሚሉት ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ አኳያ የሚኖረው ፋይዳ ከአንድ በመቶ በታች እንደሚሆን ተናግረዋል።

የውጭ ባለወረቶች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ሲገቡ የገበያ ትሥሥር አበጅተው እንደሆነ የሚጠቅሱት ዶክተር ታደሰ የሚፈጠረው ውድድር በገበያው ብቸኛ በነበሩ ተዋናዮች ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ገልጸዋል። “ከውድድር ሊወጡ የሚችሉ የኢትዮጵያ የበፊቱ የሀገሬው ተዋናዮች ጥቂት ናቸው። ሊጎዱ ይችላሉ፤ ምን አልባት ሊጎዱ ይችላሉ። ተወዳዳሪ ካልሆኑ ምን አልባት ከገበያውም ሊወጡ ይችላሉ” ሲሉ ዶክተር ታደሰ ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያን ገበያ በተለይ የንግድ ሥርዓቱን ለውጭ ባለወረቶች ወለል አድርጎ የሚከፍተው የፖሊሲ ለውጥ ተስፋ የመጫሩን ያክል ሥጋት የሚሰማቸው ባለሙያዎች አሉ። “ከውጪ የሚመጡት ሰዎች በፍጥነት ትርፋቸውን ማግኘት ስለሚፈልጉ በፍጥነት ጥሬ ዕቃውን ማውጣት ላይ ያተኩራሉ” የሚሉት በዩናይትድ ኪንግደም ብሪስቶል ዩኒቨርሲቲ ሥር በሚገኘው ፔሪቮሊ አፍሪካ ጥናት ማዕከል ተመራማሪው ዶክተር ኢዮብ ባልቻ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚፈልገውን የውጭ ምንዛሪ ቢያገኝም ሀገሪቱ ግን “አብዛኛውን ሕብረተሰብ የሚጠቅም የኤኮኖሚ ሥርዓት አትገነባም” ሲሉ ይሞግታሉ።

አብዛኛውን የኢትዮጵያ ወጣት፤ አብዛኛው ገጠር ውስጥ የሚኖረውን ሕዝብ ጉልበት የሚጠቀም፤ የግብርና፣ የማምረቻ እና የአገልግሎት ዘርፉን እርስ በርስ የሚያስተሳስር ዕድል አይፈጥርም የሚሉት ዶክተር ኢዮብ “በቀላሉ ጥሬ ዕቃ ቶሎ ቶሎ ወደ ውጪ እንዲወጣ የሚያመቻች ይሆንና ሀገሪቱ የበለጠ ውድቀት ውስጥ እንድትገባ ነው የሚያደርጋት” ሲሉ የተሰማቸውን ሥጋት ገልጸዋል።

የአሜሪካ ሱፐር ማርኬት
በሀገሪቱ ሕግ መሠረት ፈቃድ የሚያገኙ የውጭ ኩባንያዎች እና ነጋዴዎች በችርቻሮ ንግድ ሥራ እንዲሰማሩ የተፈቀደላቸው ሲሆን ከ2 ሺሕ እስከ 10 ሺሕ ሜትር ስኩዌር ስፋት ያላቸው ሱፐር ማርኬቶች እንዲገነቡ ይጠበቃል። ምስል Lucy Nicholson/REUTERS

መመሪያው የውጭ ባለወረቶች ከአፈር ማዳበሪያ እና ከነዳጅ ውጪ ያሉ ሸቀጦች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ማስገባት ይፈቅዳል። የውጭ ነጋዴዎች ከአፈር ማዳበሪያ በቀር የማናቸውንም ሸቀጦች የጅምላ ንግድ ሥራ ማከናወንም ይችላሉ። በሀገሪቱ ሕግ መሠረት ፈቃድ የሚያገኙ የውጭ ኩባንያዎች እና ነጋዴዎች በችርቻሮ ንግድ ሥራ እንዲሰማሩም ተፈቅዶላቸዋል። በመመሪያው መሠረት በችርቻሮ ንግድ የሚሠማሩ የውጭ ባለወረቶች ከ2000 እስከ 10, 000 ሜትር ስኩየር ሜትር ስፋት የሚኖራቸው መደብሮች መገንባት አለባቸው።

የኢትዮጵያ ውስብስብ ቢሮክራሲ የሀገሬውን ሰዎች በኃይል የሚፈታተን ለውጭ ኩባንያዎችም “የማያመች” የሚባል ነው። የውጭ ምንዛሪ እጥረት እና የሀገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ ተጽዕኖ ማሳደራቸው አይቀርም።

“እነ ዎልማርት ወይም እነ ቴስኮ [ወደ ኢትዮጵያ] ገብተው ገበያውን ይቆጣጠሩታል ብዬ አላስብም” የሚሉት አቶ ያሬድ እንደ ኬንያ ባሉ ገበያዎች የተሰማሩ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ብቅ ቢሉ “ምርጫ ይፈጥራል” የሚል ተስፋ አላቸው።

ይኸ የፖሊሲ ለውጥ የውጭ ባለወረቶች እና ኩባንያዎችን ቀልብ ከገዛ የሀገሪቱን የችርቻሮ ንግድ ከሥር መሠረቱ የሚቀይር ይሆናል። “የመንግሥት ዋናው ሥራ የጥቂቶችን ጥቅም ማስጠበቅ አይደለም። የመንግሥት ሥራ የአብዛኛውን ጥቅም ማስጠበቅ ነው” የሚሉት የሕግ ባለሙያው ዶክተር ታደሰ “በጅምላ እና በችርቻሮ ንግድ የሚሰማሩ ድርጅቶች ቢመጡ የሚጠቀመው የኢትዮጵያ ሸማች ይመስለኛል።ምክንያቱም በዋጋ ቅናሽ ያገኛል። ብዙ አማራጮች የሚያገኝበት አጋጣሚ ይፈጠርለታል” ሲሉ ተስፋቸውን አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመሩት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ መመሪያ በወጪ፣ ገቢ፣ ጅምላ እና ችርቻሮ የንግድ ዘርፎች የውጭ ባለወረቶች እንዲሳተፉ ፈቅዷል። ምስል United Nations FAO 2024

ዶክተር ኢዮብ ግን የውጭ ባለወረቶች በገቢ ንግድ እንዲሰማሩ ሲፈቀድ ገበያው “ከውጪ በርካሽ” ወደ ኢትዮጵያ በሚገባ ሸቀጥ ተጥለቅልቆ የሀገር ውስጥ ምርት ችግር ውስጥ እንዳይወድቅ ይሰጋሉ። “አብዛኞቹ የአፍሪካ እና የካሪቢያን ሀገሮች በእንደዚህ አይነት መልኩ ነው ኤኮኖሚያቸው በ1980ዎቹ እና 90ዎቹ ድቅቅ ያለው” የሚሉት ዶክተር ኢዮብ የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ ቀደም ሲከተል የነበረው አቋም “ውስንነቶች” እንደነበሩበት ይስማማሉ።

“የኢትዮጵያ መንግሥት የራሴን ሀገራዊ ከበርቴ እያገዝኩኝ አሳድጌ በጊዜ ሒደት አቅም እንዲኖረው አደርጋለሁ ብሎ ነው እስከዛሬ ድረስ ይኸንን [አቋም] ይዞ የነበረው። ውስንነት አለው። አዎ ውስንነት አለው። በተለያዩ ዓይነት አካሔዶች ሊስተካከሉ የሚገቡ ውስንነቶች አሉ” የሚሉት ተመራማሪው “ይኸንን ግን ብትንትን አድርገህ ስትከፍተው የተመዘገበ ኮርፖሬሽን መጥቶ ሀብት እና ጥሪት እንዲዘርፍ ነው የምታደርገው” ሲሉ ብርቱ ትችት ይሰነዝራሉ።

አቶ ያሬድ ኃይለማርያም በወጪ እና ገቢ ንግድ የተሠማሩ የኢትዮጵያ ኩባንያዎች ራሳቸውን በማጠናከር ተፎካካሪ ሆኖ መገኘት ግፋ ሲልም በሽርክና ከውጪዎቹ ጋር አብሮ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ይመክራሉ።

መንግሥት የውጭ ምንዛሪ የበለጠ ሊያስገኝ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ሊያሳልጥ፣ የችርቻሮ እና ጅምላ ንግድን ሊያዘምን የሚችለውን ሊመርጥ እንደሚገባ የሚመክሩት ዶክተር ታደሰ “ኢትዮጵያዊ ስለሆንክ መንግሥት ጥላ ሊሆንልህ ይገባል የሚለው ነገር እስካሁን የሔድንበት የተሳሳተ መንገድ ስለሆነ አሁን መቀየሩ በጣም ደስ ብሎኛል” ሲሉ ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ