የኢትዮጵያ ደኅንነት፣የፖለቲካ አለመረጋጋትና የምጣኔ ኃብት ማሻሻያ
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 25 2016የኢትዮጵያ ደኅንነት፣የፖለቲካ አለመረጋጋትና የምጣኔ ኃብት ማሻሻያ
በኢትዮጵያ የሚታየው የፀጥታ ችግር እና የፖለቲካ አለመረጋጋት አገሪቱን ወደ አደገኛ ሁኔታ ያስገባታል የሚል ስጋት እንዳሳደረባቸው፣ ምሁራንና ባለሙያዎች ገለጹ።
ታዋቂ ምሁራንና ባለሙያዎች፣የኢትዮጵጵያ ወቅታዊ ፈተናዎች ናቸው ባሏቸው የአገሪቱ ደህንነት፣ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እና የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ላይ ውይይት አካሄደዋል።
ተሳታፊዎቹ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ሁኔታ በገመገሙበት የሰሞኑ የበይነ መረብ የውይይታቸው ክፍል፣ እየተባባሰ መጥቷል ባሉት የደህንነት ስጋቶች፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት እንዲሁም የዓለም አቀፍ ጣልቃ ገብነት ፍላጎቶችን ተመልክተዋል።
የኢትዮ-ሶማሊያ ዉዝግብ፣ የምስራቅ አፍሪቃ ቀውስ ሌላው ስጋት
በመንኮታኮት አፋፍ ላይ ያለች ሃገር
የመንግስት አንዳንድ ባለስልጣናት በሃገሪቱ ያለው የሰላም ሁኔታ እየተሻሻለ ነው ሲሉ ቢደመጡም፣የምሁራንና ባለሙያዎቹ ምልከታ ግን ተስፋን የሚያጭር አይደለም።
ዶይቸ ቨለ ያናገራቸውና የዚህ ውይይት አስተባባሪዎች ከሆኑት መኻከል አንዱ፣ ፕሮፌሰር ግርማ ብርሃኑ፣ከስዊዲን ባቀረቡት የውይይት ጽሑፍ፣የኢትዮጵያ አገረ መንግስት እየወደቀ ሃገሪቱም ወደመበታተን እያመራች ነው ሲሉ ስጋታቸውን ከፍ አድርገው አሰምተዋል።
" ከመንግስት መውደቅ ወደ መንግስት መንኮታኮት የምለው ፣ስቴት ኮላፕስ የሚባሉቱን ያሟላል የኢትዮጵያ መንግስት።በእውነት ኔጌቲቭ ገጽታ ለማቅረብ ሳይሆን እነዚህ ሶስት ነገሮች፣መፍረክረክ መውደቅና እንዳለ መንኮታኮት የሚባሉትን ነገሮች የመንኮታኮቱ ጫፍ ላይ ነው ያለነው፤እንዴት እንመልሰዋለን ነው።"
በኦሮሚያ ህዝቡን ያንገሸገሸው የጸጥታ ችግር፡ የፖለቲከኞች አስተያየት
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም
የኢትዮጵያ መንግስት ካለፈው ወር አንስቶ፣አጠቃላይ የማክሮ ኤኮኖሚ ማሻሻያ በማድረግ፣ሃገሪቱን ተወዳዳሪ ወደሆነ ባለው በገበያ ላይ ወደተመሰረተ የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት ማሸጋገሩን አስታውቋል።
መንግሥት ይህ ፕሮግራም፣ በኢኮኖሚው ውስጥ ለረጅም ጊዜ ትንሰራፍቶ የቆየውን፣የማክሮ ኢኮኖሚ አለመረጋጋትና መዛባት እንደሚያሻሽለው እምነት ይዟል።
ይሁንና የውይይቱ ተሳታፊዎች፣ይህ የኢኮኖሚ ማሻሻያው የደህንነት ስጋት የተደቀነባትን አገር፣ ሌላ ተግዳሮት ያስከተልባታል የሚል ግምገማ አላቸው። ዶይቸ ቨለ ስለዚሁ ጉዳይ በኒውዮርክ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑትንና የውይይቱ ተሳታፊ የሆኑትን ፕሮፌሰር ቢኒያም አዋሽ ጠይቋቸው ነበር።
የኢትዮጵያ መንግሥት ታክስ ሳይጨምር ከዘርፉ የሚሰበስበውን ገቢ 4 በመቶ ማሳደግ ይችላል?
"ይህ የገንዘብ መበደር ብቻ ጥያቄ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አቀራረጽ ምን ይመስላል? ለሚቀጥለው ዐሥር 15 ዓመታት የሚል ጥያቄ ነው።እና የዚህ ብድር ዋናው ዓላማው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የመቆጣጠርና የመቅረጽ ስለሆነ ያ በጣም ትልቅ አዲስ ነገር ነው።"
ፕሮፌሰር ቢንያም፣ የኢትዮጵያ መንግስት የምጣኔ ኃብት ዕቅድ በአስቸኳይ ማውጣት እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል።
"መንግስት አንደኛ ሀላፊነቱ፣ጸጥታ ከማስከበር ሌላ፣ በተለይ በተለይ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ስለሆነ የኢኮኖሚ ፕላን ያስፈልጋል።የአይኤምኤፍ ብድርና የዋሽንግተን ኮንሰንሰስ የሚባለው የመዋቅር ማሻሻያ ፕሮግራም፣ እነዚህ የአይኤም ኤፍ ብድር ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት ጠቅላላ የልማት ፕላን የሚባል የላቸውም።ስለዚህ የግዴታ ያስፈልጋታል ባይ ነን።"
ምን መደረግ አለበት?
አሳሳቢነቱ እየጎላ መጥቷል ባሉት የሀገሪቱ መረጋጋትንና ደኅንነት ላይ አትኩሮ መፍትሔዎችን የሚፈነጥቅ ስብሰባ በቀጣይ እንደሚካሄድ ፕሮፌሰር ግርማ ጠቁመዋል።
"በደኅንነት ደረጃ ሊያመጣ የሚችለው ነገር በጣም አደገኛ ነው።አንድ አገር ከፈነዳ፣ከቁጥጥር ውጭ ከሆነ የከፋው ሁኔታ ነውና ከእዛ በፊት ምን መደረግ አለበት የሚል መንደርደሪያ ዐሳቦችን ይዘን በሚቀጥለው በወር ውስጥ እንመለስበታለን።"
ፕሮፌሰር ቢኒያም፣በኢትዮጵያ በግጭት የሚታሳፉ ኃይሎች ልዩነታቸውን በጠመንጃ ሳይሆን በሰላማዊ መንግስት መንገድ መፍታታቸው በሃገሪቱ ላይ ከተጋረጠው አደጋ መውጫ መንገድ ይሆናል ይላሉ።"
በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት በመንግስትም ውስጥ ከመንግስት ውጭ የሆኑ ኢመደበኛ የተሰለፉት ኀይሎች፣መወያየትና መግባባት መፍጠር አለባቸው የሚል ዐሳብ ነው። ምክንያቱም የፖለቲካ ቀውሱ ከኤኮኖሚ መድቀቁ ጋር ሁለቱም የተያያዙ ስለሆነ ማለት ነው።"ብለዋል።
ታሪኩ ኃይሉ
ታምራት ዲንሳ