1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ የውጭ ብድር የመክፈል አቅም ምዘና

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 19 2015

ፊች ሬቲንግስ የተባለ ተቋም ለኢትዮጵያ የውጭ ብድር የመክፈል አቅም ከዚህ ቀደም የሰጠውን ምዘና ባለፈው ሣምንት ዝቅ አድርጓል። በተቋሙ ስሌት መሠረት እስከ መጪው ሰኔ ድረስ አገሪቱ 1.6 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ብድር ወለድ መክፈል ይጠበቅባታል። አገሪቱ በጎርጎሮሳዊው 2024 ደግሞ ሌላ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ክፍያ አለባት።

https://p.dw.com/p/4LVKn
USA Wirtschaft Ratingagentur Fitch Ratings in New York Gebäude
ምስል picture-alliance/dpa

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ የኢትዮጵያ የውጭ ብድር የመክፈል አቅም ምዘና

መቀመጫውን በኒው ዮርክ ያደረገው ፊች ሬቲንግስ የተባለ ተቋም ለኢትዮጵያ የውጭ ብድር የመክፈል አቅም ከዚህ ቀደም የሰጠውን ምዘና ባለፈው ሣምንት ዝቅ አድርጓል። ዓለም አቀፍ የብድር ምዘና ኤጀንሲ የሆነው ተቋም ባለፈው ሣምንት ይፋ ባደረገው ሰነድ የኢትዮጵያ የውጭ ዕዳ አከፋፈል ምን ሊመስል እንደሚችል ትንበያ የሰጠ ነው። ከዚህ ቀደም በዚሁ ተቋም ምዘና ሲሲሲ (CCC) የሚል ደረጃ ተሰጥቶት የነበረው የኢትዮጵያ የውጭ ዕዳ የመክፈል አቅም ባለፈው ሣምንት ወደ ሲሲሲ ኔጌቲቭ (CCC-) ዝቅ ብሏል። 

በጀርመኑ ሔለባ ባንክ የኤኮኖሚ ትንተና ባለሙያው ፓትሪክ ሐይኒሽ ተቋሙ ለኢትዮጵያ ብድር የመክፈል አቅም የሰጠው ምዘና ከሲሲሲ (CCC) ወደ ሲሲሲ ኔጌቲቭ (CCC-) ቢቀየርም ሁለቱም "ዕዳ የመክፈል አቅም ዝቅተኛ መሆኑን የሚያሳዩ" በመሆናቸው "መሠረታዊ ለውጥ" እንደሌላቸው ይናገራሉ።

"በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት የብድር ሰነድ ለዓለም አቀፉ የካፒታል ገበያ የማቅረብ ዕቅድ የለውም" የሚሉት ፒተር ሐይኒሽ ምዘናው በቀጥታ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የሚያሳድረው ጫና "የተወሰነ" ቢሆንም "ለውጭ ባለወረቶች እና ለውጭ ባንኮች አንዳች ምልክት የሚሰጥ በመሆኑ ጫና ሊኖረው ይችላል" ሲሉ አስረድተዋል።

ይኸ ለኢትዮጵያ ብድር የመክፈል አቅም የተሰጠ ምዘና በፕሪቶሪያ የተፈረመው በቋሚነት ግጭት የማቆም ሥምምነት ሊፈጥር ይችላል ተብሎ የሚጠበቀውን የመካከለኛ ጊዜ የማክሮ ኤኮኖሚ እና የፋይናንስ ሁኔታ መሻሻል ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው። ዓለም አቀፉ የአቅርቦት ሰንሰለት የገጠሙት ተግዳሮቶች ያሳያሉ ተብሎ የሚጠበቀው መቃለል እንዲሁም የመንግሥት የዕዳ ሁኔታ መሻሻል ለትንበያው ከግምት ውስጥ የገቡ ጉዳዮች ናቸው።

አዲስ አበባ ስታዲየም
በፊች ግምት መሠረት ኢትዮጵያ 1.6 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ዕዳ ወለድ ክፍያ እስከ መጪው ሰኔ ይጠብቃታል። ምስል DW

በፊች ግምት መሠረት ኢትዮጵያ 1.6 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ዕዳ ወለድ ክፍያ እስከ መጪው ሰኔ ይጠብቃታል። በጎርጎሮሳዊው 2024 ደግሞ ሌላ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ክፍያ አለባት። በጎርጎሮሳዊው 2023 የውጭ ንግድ ሚዛን ጉድለት (Current Account Balance) እና የተጣራ የውጭ ቀጥተኛ መዋዕለ ንዋይ 1.7 ቢሊዮን ዶላር ደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ የፊች ትንበያ ያሳያል። በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ያላት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ከአንድ ወር በታች ለሚሆን ጊዜ የሚበቃ ሸቀጦች እና አገልግሎቶችን ለመሸመት የሚችል ነው።  

"አሁን ባላት 1.5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የሚገመት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ የሚጠበቅባትን ለመክፈል በጣም አስቸጋሪ ነው" የሚሉት የኤኮኖሚ ተንታኙ ፓትሪክ ሐይኒሽ "ይኸን ምዘና ዝቅ እንዲል ያደረገውም ይኸው ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ (G20's Common Framework) በኩል የዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ ለማድረግ የጀመረችው ሒደት በዋናነት በፊች ምዘና ላይ ተጽዕኖ ያሳደረ ጉዳይ ነው። በማዕቀፉ ኢትዮጵያ የውጭ ዕዳ ለመክፈል የተፈጠረባትን ጫና የሚያቃልል ማሻሻያ ካልተበጀ እና ተጨማሪ የውጭ የፋይናንስ ድጋፍ ካላገኘች የውጭ ብድር የመክፈል ጫናው እንደሚባባስ ፊች አስታውቋል።

የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ ከተጀመረ ዓመት ከዘጠኝ ወራት ገደማ ያስቆጠረው የዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ ድርድር ተጠናቆ ተግባራዊ ቢሆን ኖሮ ለኢትዮጵያ የውጭ ዕዳ ጫና ፋታ ሊሰጥ ይችል እንደነበር ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። የዕዳ አከፋፈል ማሻሻያው ቢጠናቀቅ ኖሮ "ወደፊት መግፋት" ይቻል እንደነበር የገለጹት ዶክተር አብዱልመናን የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ክምችት አነስተኛ መሆን ጭምር አገሪቱ ዕዳዋን ለመክፈል ለገጠማት ተግዳሮት አስተዋጽዖ እንዳለው አስረድተዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከጥቅም ውጪ የሆነ ታንክ
ለኢትዮጵያ ብድር የመክፈል አቅም በፊች ሬቲንግስ የተሰጠ ምዘና በፕሪቶሪያ የተፈረመው በቋሚነት ግጭት የማቆም ሥምምነት ሊፈጥር ይችላል ተብሎ የሚጠበቀውን የመካከለኛ ጊዜ የማክሮ ኤኮኖሚ እና የፋይናንስ ሁኔታ መሻሻል ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው። ምስል Baz Ratner/REUTERS

ከኢትዮጵያ አበዳሪዎች የሚጠበቀው የዕዳ ማሻሻያ ግን እስካሁን ድረስ ይኸ ነው የሚባል እርምጃ አላሳየም። በቻይና እና በፈረንሳይ ተባባሪ ሊቀ-መንበርነት የሚመራው የኢትዮጵያ አበዳሪዎች ኮሚቴ እስካለፈው ኅዳር ድረስ ለአራት ጊዜያት ቢሰበሰብም ለአገሪቱ ሊደረግ ከሚችል የዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ ላይ የተደረሰ ሥምምነት ስለመኖሩ በግልጽ የተባለ ነገር የለም። በፕሪቶሪያ በተፈረመው በቋሚነት ግጭት የማቆም ሥምምነት ጋብ ያለው የትግራይ ጦርነት እና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የሚጠበቀው የዕዳ ዘላቂነት ትንተና አለመከናወን ለዕዳ አከፋፈል ማሻሻያው መዘግየት አስተዋጽዖ አበርክተዋል።

የኢትዮጵያ ዕዳ ከአጠቃላይ አገራዊ የምርት መጠን 56 በመቶ ገደማ እንደሚሆን የሚናገሩት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን የውጭ ብድር እስከ 28 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ገልጸዋል። ይኸን ለመክፈል ፈታኝ የሚያደርገው የብድር መጠኑ ብቻ ሳይሆን የአከፋፈል ውሉ ጭምር እንደሆነ የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ይጠቅሳሉ።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አስተዳደር ቦርድ
ኢትዮጵያ የምትጠብቀው የብድር ጫና ትንተና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ውሳኔን ይፈልጋል።ምስል IMF/Cliff Owen

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ካለፈው ሰኔ ጀምሮ በኢትዮጵያ የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ ግብር ፕሮግራሞች ላይ ከባለሥልጣናቱ ጋር ግንኙነት መጀመሩን አስታውቋል። አገሪቱ ከተቋሙ የምትጠብቀው የብድር ጫና ትንተና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ውሳኔን ይፈልጋል። የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት የተፈራረሙት ሥምምነት በጦርነቱ ምክንያት አገሪቱ ከልዕለ ኃያላኑ እና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ያላትን ግንኙነት ሊያሻሽል እንደሚችል በርካታ የኤኮኖሚ ባለሙያዎች ተስፋ አድርገዋል። እንዲያም ሆኖ አሁንም ተጽዕኖ የሚኖራቸው ጉዳዮች እንዳሉ የሚናገሩት ፓትሪክ ሐይኒሽ  የተጠያቂነት ጉዳይ አንዱ መሆኑን አንስተዋል።

የአውሮፓ ኅብረት እና አሜሪካ ካስቀመጧቸው ቅድመ ሁኔታዎች አንዱ የተጠያቂነት ጉዳይ መሆኑን የተናገሩት የኤኮኖሚ ትንተና ባለሙያው "ኢትዮጵያ እንዴት እንደምታስተናግደው ግን የምናውቀው ነገር የለም። በተዋጊዎቹ መካከል ባለፉት ሁለት ዓመታት ኃይለኛ ጥላቻ ስለነበር ጉዳዩ ውስብስብ ነው። ቢያንስ ይፋ በተደረገው ሥምምነትም ቢሆን ጉዳዩ በግልጽ ምላሽ አላገኘም። ይኸ የተጠያቂነት ጉዳይ ቁልፍ ሚና ይኖረዋል" ሲሉ ተናግረዋል። ባለሙያው እንደሚሉት "በቤኒሻንጉል ጉምዝ እና ኦሮሚያ ክልሎች ያለው የሰላም ሁኔታ ኢትዮጵያ ከለጋሾች ጋር በሚኖራት ግንኙነት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር የዕዳ አከፋፈል ማሻሻያውንም ለተወሰኑ ወራት ሊያዘገይ ይችላል።"

የአውሮፓ ኅብረት ባለፈው ሣምንት ባወጣው መግለጫ የፕሪቶሪያው ሥምምነት በዘላቂነት ተግባራዊ መሆን ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማደስ እንደሚያስችል አስታውቋል። ኅብረቱ የተኩስ አቁም፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እና ለዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግ እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና በደሎች ተጠያቂነትን ማረጋገጥ የልማት ትብብር እና የኤኮኖሚ ድጋፍን በሒደት መልሶ ለማስጀመር እንደሚፈቅድ ገልጾ ነበር።

እሸቴ በቀለ