1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ዕድልና ሥጋት 

ረቡዕ፣ መስከረም 28 2012

የአፍሪካ አገሮችን የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ምቹነት ከተጠቃሚነትና ከሥጋት አንፃር ገምግሞ ደረጃ የሚሰጠው «ኮንትሮል ሪስክ» የተባለ የጥናት ቡድን ሰሞኑን ባወጣዉ ዘገባ ኢትዮጵያ በመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ረገድ ከፍተኛ ዕድል ቢኖራትም በዚያዉ መጠን ስጋቱ ከፈተኛ መሆኑን ገልጿል።

https://p.dw.com/p/3QzlJ
Äthiopien Währung Birr
ምስል DW/Eshete Bekele Tekle

ከኢኮኖሚዉ ዓለም


መቀመጫዉን በእንግሊዝ ሀገር ያደረገዉ «ኮንትሮል ሪስክ» የተባለዉ የምጣኔ ሀብት አማካሪ ድርጅት  በጎርጎሮሳዊዉ መስከረም 23 ቀን 2019 የተወሰኑ የአፍሪቃ ሀገራትን  የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት በተመለከተ ዓመታዊ  ዘገባ አዉጥቷል።  
ድርጅቱ ባወጣዉ የ2019 የአፍሪካ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ስጋትና ዉጤታማነት ጠቋሚ መረጃ በኢትዮጵያ፣ በአንጎላና በደቡብ አፍሪቃ የተደረጉ የማሻሻያና የለዉጥ አጀንዳዎች  በሀገራቱ የምጣኔ ሀብትና የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ላይ ያሳደሩትን ተፅዕኖዎች መርምሯል።
ዘገባዉ በአፍሪቃ ሀገራት መካከል ያለዉን አፈፃጸም  ከአህጉሪቱ ነባራዊ ሁኔታ አንጻር በመለየትም  ለመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ተስፋ ሰጪ የሆኑ የገበያ ዕድሎችንና አደጋዎችን በንፅፅር አቅርቧል።
በዚህ መሰረት ባለሀብቶች መዋዕለ ንዋያቸዉን በኢትዮጵያ ቢያፈሱ በዋናነት ከህዝብ ብዛቷ አንጻር በከፍተኛ ደረጃ ዉጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ አመልክቷል። በዚያዉ ልክም በሀገሪቱ ዉጤታማ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰትን ሊገድቡ የሚችሉ ስጋቶች መኖራቸዉን ገልጿል።
ለሀገራት ከተሰጠዉ አስር ነጥብ ኢትዮጵያ በመዋዕለ ንዋይ ፍሰት አዋጭነቷ አንፃር ስምንት ነጥብ የተሰጣት ሲሆን የስጋት ደረጃዋም በዚያዉ መጠን ከፍተኛ መሆኑ ነዉ በዘገባው የተመለከተዉ።
ምንም እንኳ የስጋት መጠኑ ካለፈዉ 2018 ጋር ሲነፃጸር በዜሮ ነጥብ አራት መቀነስ ቢታይበትም ከፍተኛ ስጋት ይታይባቸዋል ከሚባሉ ሃገራት ማለትም፦ ዲሞክራቲክ ኮንጎን እና ደቡብ ሱዳንን  ከመሳሰሉ የአፍሪቃ ሀገራት ተርታ ነዉ ኢትዮጵያ የተመደበችዉ። የዉጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የገንዘብ ተቋማት የአሠራር ድክመት እንዲሁም የሀገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ለስጋቱ መጨመር በምክንያትነት ተቀምጧል። የምጣኔ ሀብት ባለሙያዉ አቶ ጌታቸዉ ተክለማርያም በሪፖርቱ የተጠቀሰዉ የስጋት መጠን መንግስት ከፍተኛ ሥራ መስራት እንዳለበት የሚያመላክት ነዉ ይላሉ።
ኢትዮጵያ በመዋዕለ ንዋይ ፍሰት በዉጤታማነት ረገድ ከፍተኛ ነጥብ እንዲሰጣት  ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ የህዝብ ብዛቷ ሲሆን፤ በዚህም ለባለሀብቶች ሰፊ የገበያ ዕድል ይፈጠራል የሚል ተስፋ አሳድሯል። ያም ሆኖ ግን የአብዛኛዉ ህዝብ ገቢ አነስተኛ በመሆኑ የመግዛት አቅሙም በዚያዉ መጠን ዝቅተኛ ነዉ በሚል የሚተቹ አሉ። ለዚህም አብዛኛዉን የኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ የሥራ ዕድልን የሚፈጥርና የመግዛት አቅምን የሚጨምር ኢኮኖሚያዊ የሽግግር መዋቅር መፍጠር መፍትሄ መሆኑን ባለሙያዉ ይጠቁማሉ። «« አሁን ብዙ ህዝብ ነዉ ያለን።ብዙ ስራ በመፍጠር ረገድ የተሻለ የሚያዋጣዉ የኢንደስትሪዉ ዘርፍ ነዉ።የሰርቪስ ዘርፉ አደገ በ«ጂዲፒዉ ሪፍሌክትድ» ሆነ ግን ደግሞ ስራ በመፍጠር ረገድ በቂ የሰዉ ሀይልን በዉስጡ ሊይዝልን አልቻለም።አሁን የምናየዉ ብዙ የስራ አጥ ቁጥር የሚታየዉ በሱ መዋቅራዊ ችግር ነዉ በዋናነት።ከዚህ አንፃር ስንመለከተዉ የሚያዋጣን የኢንደስትሪ ዘርፉ ነዉ።»ብለዋል።

Äthiopien Währung Birr
ምስል DW/Eshete Bekele Tekle
Äthiopien Währung Birr
ምስል DW/Eshete Bekele Tekle

በሁለተኛ ደረጃ የተነሳዉ ምክንያት ደግሞ መንግስት የልማት ተቋማትን ወደግል የማዞር ዕቅድ ለባለሀብቶቹ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል የሚል ነዉ። በተለይም መንግስት የቴሌኮም ዘርፉን ክፍት በማድረግ አዳዲስ የአገልግሎት ሰጪዎች ወደ ዘርፉ ለማስገባት የተጀመረዉ እንቅስቃሴ ለባለሀብቶች ከፍ ያለ ዕድል መሆኑን ዘገባዉ አትቷል።
በተለይም ኢትዮጵያን የሚያዉቋት ባለሀብቶች የበለጠ ዉጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉም በዚሁ ዘገባ ተጠቅሷል። ይህ ምን ማለት ይሆን? አቶ ጌታቸዉ ተ/ማርያም ማብራሪያ አላቸዉ። 

«ኢትዮጵያን የሚያዉቁ የሚለዉ ይህ ገበያ የራሱ የሆኑ ባህሪያት አሉት።በአንድ በኩል የቢሮክራሲዉን አሰራር ለመረዳት ጊዜ ይፈጃል። በሌላ በኩል የተጠቃሚዉ አይነት ፣ተጠቃሚዉ የሚገኝባቸዉ ቦታዎች፣ የተጠቃሚዉ የመጠቀም ባህል፣እሱን የተረዳ አካባቢዉ ላይ የቆዩ ኢንቨስተሮች» መሆናቸዉን ነዉ የተናገሩት።

የኢትዮጵያ መንግስት ባለፉት ሁለት ዐሥርተ ዓመታት በመቶ የሚቆጠሩ የልማት ድርጅቶችን በመሸጥ በቢሊዮን የሚቆጠር ብር ገቢ ማግኘቱን ዘገባዎች ያሳያሉ። ያም ሆኖ ግን አብዛኞቹ የልማት ድርጅቶች ወደ ግል ሲዞሩ  ለመንግስት ገቢ ከማስገኘት በዘለለ ውጤታማ መሆን እንዳልቻሉ እየተነገረ ነዉ። ለዚህም መንግስት ከተቋማቱ ሽያጭ ከሚያገኘዉ ገቢ ባሻገር ያሉበትን ሁኔታ ክትትል አለማድረጉ እንደ ችግር ይነሳል።
አሜሪካን ሀገር በዊስከንሰን ዩንቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር ዳንኤል ተፈራ ግን መንግስት የልማት  ድርጅቶችን  ወደ ግል ማዞርን ብቸኛ አማራጭ አድርጎ  መመልከት የለበትም ባይ ናቸዉ።

Äthiopien landwirtschaftliche Erzeugnisse auf einem Markt
ምስል DW/M. Haileselassie

 ኢትዮጵያን ወደ ገበያ-መር ኢኮኖሚ ማስገባት የተሻለ እና አስፈላጊ ነው ሲሉ ጠቁመዋል። መንግስት ከገበያዉ እጁን በማንሳት የገበያ ስርዓት ሽግግር ማድረግ ጠቃሚ መሆኑንም አስገንዝበዋል። ያ ሲሆን ህዝቡ አምራችም ሸማችም በመሆን ከኢኮኖሚዉ ተጠቃሚ ይሆናል ብለዋል። ለዚህም ኢኮኖሚዉ በፖለቲካ ከመመራት ይልቅ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ አቅጣጫ ወደ የት ይሂድ በሚለዉ የባለሞያዎች ዉይይት ወሳኝ ነዉ ሲሉ ዶክተር ዳንኤል ተፈራ መክረዋል።
እንደ ባለሞያዎቹ  ከኾነ፦ ዘገባዉ በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታዎች በመመዘን ረገድ ጥሩ ነው። ኾኖም በሀገሪቱ የሚስተዋለዉን ፓለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ በመተንተን ረገድ እያደገ የመጣዉ የበረራ አገልግሎት ዘርፍ ባለሀብቶችን ለመሳብ ያለዉን ጠቀሜታና የተቋማትን ለዉጥ ዘርዝሮና  ለይቶ በማስቀመጥ እጥረት ነበረበትም ብለዋል።
ዘገባዉ ምንም ይሁን ምን የሀገሪቱን የምጣኔ ሀብትና የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ዕድል ለማስፋትና ስጋቶችን ለመቅረፍ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ  ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ጠቃሚ መሆኑን ባለሞያዎቹ ያስረዳሉ። ለዚህም  በቅርቡ በመንግስት የተነደፈዉ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕቅድ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን የሚያፋጥኑ ነገሮች ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ መዋቅራዊ ችግሮች ላይ እንዲያተኩር ማድረግና በሀገሪቱ ሰላምን ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑ አቶ ጌታቸዉ አስምረዉበታል።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነዉ ያድምጡ።

ፀሐይ ጫኔ

ማንተጋፍቶት ስለሺ