1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውድቀት መፍትሄ ፤ የአውሮጳ ሊጎች መጀመር

ሰኞ፣ ነሐሴ 13 2016

ዉጤት እየራቀው የሄደው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ አመራሩ ኃላፊነት እንዲወስድ እና ከስልጣን እንዲለቅ የሚጠይቁ ድምጾች ጎልተው ተሰምተዋል። በበርካቶች ዘንድ ሲጠበቅ የሰነበተው የአውሮጳ ኃያላን ክለቦች የእግር ኳስ ውድድሮች ካለፈው አርብ ጀምሮ በድምቀት ተጀምሯል።

https://p.dw.com/p/4jdxQ
Olympia 2024 | Äthiopiens Olympia-Team kommt in Paris an
ምስል Haimanot Tiruneh/DW

የነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ/ም የስፖርት ዝግጅት

አትሌቲክስ
ዉጤት እየራቀው የሄደው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ አመራሩ ኃላፊነት እንዲወስድ እና ከስልጣን እንዲለቅ የሚጠይቁ ድምጾች ጎልተው እየተሰሙ ባሉበት ወቅት በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ከኦሎምፒክ ኮሚቴ  እና የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንቶች አንደበት የተለያዩ ሃሳቦች ተሰምተዋል። 

ኬንያ ለከዋክብት አትሌቶቿ የቆሙ እና አሳፋሪ ናቸው ያለቻቸውን ሀውልቶች አፍርሳለች ። 
በበርካቶች ዘንድ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የአውሮጳ ኃያላን የእግር ኳስ ሊጎች በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ዉድድሮቻቸውን በድምቀት ጀምረዋል። በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ያለፈው የውድድር ዘመን ቀዳሚዎቹ አራት ክለቦች የመክፈቻ ጨዋታዎቻቸውን በድል ጀምረዋል። 

የ33ኛው የፓሪስ ኦሎምፒክ ፍጻሜ እና ኢትዮጵያ

በብስክሌት እሽቅድምድም ፖላንዳዊቷ ካታዢና ኒቪያዶማ ለመጀመሪያ ጊዜ የቱር ዲ ፍራንስ ሻምፒዮና ሆናለች 
።  

ኢትዮጵያ በ33ኛው የፓሪስ ኦሎምፒክ ባስመዘገበችው ዝቅተኛ ውጤት በስፖርቱ ደጋፊዎች ዘንድ ብርቱ ቅሬታ ፣ በኦሎምፒክ ኮሚቴው እና የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ላይ ደግሞ ብርቱ ትችት እና ዉግዘት አስከትሏል። ባለስልጣናቱ ከኃላፊነት እንዲለቁ የሚጠይቁ ድምጾችም ከፍ ብለው ሲደመጡ ሰንብተዋል። 
ባለፉት የሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ከወደ አዲስ አበባ የተሰሙ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ኮሚቴn ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ ከኃላፊነታቸው እንደማይለቁ ግልጽ ያደረጉበት ሃሳብ አንዱ ነበር ።

የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ በበኩሏ ከፊታችን ጥቅምት ወይም ህዳር ፌዴሬሽኑ አዲስ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እንደሚመርጥ ፍንጭ ሰጥታለች። የኢትዮጵያውያን ኩራት የሆነው የአትሌቲክስ ስፖርት ውጤት ለማስመለስ የሚደረገውን ጥረት በተመለከተ ከሰሞኑ የተደረጉ ዉይይቶችን በተመለከተ የአዲስ አበባውን ተባባሪ ዘጋቢያችን ኦምና ታደለን በስልክ አነጋግሬው ነበር ። የውይይቱን አንድምታ በማስወደም ይጀምራል። 

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሄራዊ ቡድን
የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ በበኩሏ ከፊታችን ጥቅምት ወይም ህዳር ፌዴሬሽኑ አዲስ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እንደሚመርጥ ፍንጭ ሰጥታለች።ምስል Million Hailesilassie/DW

አልሻል ያለው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ መፍትሄው ምን ይሆን ?

  ኢትዮጵያ በ33ኛው የፓሪስ ኦሎምፒክ ተሳትፎዋ አንድ የወርቅ እና ሶስት የብር ሜዳሊያዎችን በ,ድምሩ አራት ሜዳሊያዎች በማግኘት ከዓለም በ47ኛ ከአፍሪቃ አራተኛ ሆና አጠናቃለች። ቀጣዮ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከአንድ ዓመት በኋላ በጃፓን አስተናጋጅነት እንዲሆም ቀጣዩ የኦሎምፒክ ጫወታዎች ከአራት አመታት በኋላ በአሜሪካ አስተናጋጅነት ይከናወናል። 

እግር ኳስ 
በበርካቶች ዘንድ ሲጠበቅ የሰነበተው የአውሮጳ ኃያላን ክለቦች የእግር ኳስ ውድድሮች ካለፈው አርብ ጀምሮ በድምቀት ተጀምሯል። በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ባለፈው አርብ ማንችስተር ዩናይትድ ፉልሃምን በሜዳው ባስተናገደው ጫወታ አንድ ብሎ ሲጀመር ባለሜዳዎቹ ቀያይ ሴይጣኖች 1 ለ 0 በማሸነፍ አዲሱን የሊግ ዘመን በድል ጀምረዋል። 
በፕሪምየር ሊጉ ባለፈው የውድድር ዘመን እስከ አራተኛ ያጠናቀቁ ቡድኖች የመጀመሪያዉን ጫወታቸውን በድል ሲጀምሩ አዲሱ የውድድር ዓመት ብርቱ ፉክክር የሚደረግበት እንደሚሆን ፍንጭ ሰጥተዋል። 

የአርሴናል አማካይ ኦዲጋርድ እና አጥቂው ካይ ሃቬርትስ
አርሴናል በሜዳው ወለቨርሃምፕተንን አስተናግዶ በተመሳሳይ 2 ለ 0 አሸንፏል። ምስል Frank Augstein/AP Photo/picture alliance

ስፔንን ለድል ያበቁት የዘር ሐረጋቸው ከአፍሪቃ የሚመዘዝ ተጨዋቾች
ባለፈው ቅዳሜ ከሜዳው  ውጭ አዲስ መጪውን የኢፕስዊች ታወንን የገጠመው ሊቨርፑል 2 ለ 0 ሲያሸንፍ አርሴናል በሜዳው ወለቨርሃምፕተንን አስተናግዶ በተመሳሳይ 2 ለ 0 አሸንፏል። አስቶንቪላ በበኩሉ ከሜዳው ውጭ ተጉዞ ዌስትሃምን 2 ለ 1 አሸንፎ ሶስት ነጥቡን አስከብሮ ተመልሷል። 
የስፔኑ ላሊጋም ባለፈው ሐሙስ አዲሱን የሊግ ዘመን በይፋ ጀምሯል። ያለፈው የውድድር አመት ሻምፒዮናው ሪያል ማድሪስ ወደ ማሎርካ ተጉዞ አንድ አቻ መለያየቱን ተከትሎ የመጀመሪያውን የዓመቱን የሊግ ጨዋታ ነጥብ በመጣል ጀምሯል። ባርሴሎና ከሜዳው ውጭ ቫሌንሲያን 2 ለ 1 ሲያሸንፍ የአትሌቲኮ ማድርድ እና ቪላሪያል የምሽቱ ጫወታ ይጠበቃል። 
የፈረንሳይ ሊግም በተመሳሳይ ባለፈው አርብ በድምቀት የተጀመረ ሲሆን ያለፈው የውድድር ዓመት ሻምፒዮናው ፒኤስ ጂ ከሜዳው ውጭ ሌሃቭሬን ገጥሞ 4 ለ 1 በሆነ ሰፊ የጎል ልየት አሸንፎ ተመልሷል። ሞናኮ እና ሎስክም በሜዳ እና ከሜዳ ውጭ ድል ቀንቷቸው ተመልሰዋል። 
ተጠባቂው የጀርመን ቡንደስ ሊጋ ደግሞ የፊታችን አርብ ይጀመራል።

የሪያል ማድሪድ እግር ኳስ ክለብ
ያለፈው የውድድር አመት ሻምፒዮናው ሪያል ማድሪስ ወደ ማሎርካ ተጉዞ አንድ አቻ መለያየቱን ተከትሎ የመጀመሪያውን የዓመቱን የሊግ ጨዋታ ነጥብ በመጣል ጀምሯል።ምስል Alberto Gardin/IPA Sport/ipa-agency/picture alliance


ብስክሌት
በቱር ዲ ፍራንስ የሴቶች የብስክሌት እሽቅድምድም ፖላንዳዊቷ ካታዢና ኒቪያዶማ ለመጀመሪያ ጊዜ ሻምፒዮን መሆን ችላለች ። ካታዢና አጠቃላይ የቱር ዲ ፍራንስ ውድድርን 24 ሰዓታት ከ 36 ደቂቃ 07 ሰከንድ በሆነ ድምር ውጡት ነው አሸናፊነቷን ያረጋገጠችው ። ብስክሌት ጋላቢዋ በተለያዩ ቀናት በዙር የተደረገውን ውድድር ሻምፒዮና ስትሆንም ይህ የመጀመሪያዋ ነው። ከሁለት ሳምንት በፊት በፓሪስ ኦሎምፒክ በውድድር ላይ እያለች ተጋጭታ በመውደቋ ከውድድሩ መውጣቷ አበሳጭቷት እንደነበረ የተናገረችው ካታዢና አሁን እጅጉን መደሰቷን ተናግራለች። ድሉ የቡድን አጋሮቼም ጭምር ነው ብላለች ። በውድድሩ ኔዘርላንዳዊቷ  ዴሚ ፎለሪንግ ሁለተኛ ስትወጣ ሌላዋ ኔዘርላንዳዊት ፓውሊና ሮይጃከርስ ሶስተኛ ወጥታለች። 
 

ዝነናው ቱር ዲ ፍራንስ
በቱር ዲ ፍራንስ የሴቶች የብስክሌት እሽቅድምድም ፖላንዳዊቷ ካታዢና ኒቪያዶማ ለመጀመሪያ ጊዜ ሻምፒዮን መሆን ችላለች ።ምስል Daniel Cole/AP/dpa/picture alliance´

የኤርትራዊዉ የቢኒያም ግርማይ የብስክሌት ዉድድር ድል

ትንግርት 

በመጨረሻም ኬንያ በአንዲት የአትሌቶች መፍለቂያ ከተማ ለከዋክብት አትሌቶቿ የቆሙ ሀውልቶች አሳፋሪ ናቸው በማለት አፍርሳለች። በስምጥ ሸለቆ ውስጥ የምትገኘው የኬንያዋ የኤልዶሬት ከተማ የኢትዮጵያዋ ቦቆጂ ተምሳሌት ናት ይላሉ ብዙዎች። በበርካታ ዓለማቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች የነገሱ አትሌቶችን ያፈራች ከተማም ናት ።  ነገር ግን ከሰሞኑ ፌይዝ ኪፕቲገንን ጨምሮ ለሶስት ብርቅዬ አትሌቶች ክብር ስትል ያቆመቻቸው ሀውሎቶች መሳቂያ መሳለቂያ ከማድረግ አልፎ የማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን ዘመቻ እንዲከፈት ምክንያትም ሆነዋል። ፕሬዚደንት ዊልያም ሩቶ በከተማዋ ተገኝተው የሚሰጡት የእውቅና ስነ ስረዓት ከመከናወኑ በፊት ግን ሀውልቶቹ እንዲፈርሱ መደረጉ ተዘግቧል። ኬንያዉያኑ ልክ እንደጎረቤታቸው ኢትዮጵያ የሐውልቱ ነገር አልሆነላቸውም ። እንግዲህ አድማጮች ለዛሬ ያልነው ስፖርታዊ ዝግጅታችን የእስካሁንን ይመስል ነበር ፤ ሳምንት በሌሎች ስፖርታዊ መረጃዎች እንጠብቃችኋለን ፤ እስከዚያው ጤናይስጥልን ። 
ታምራት ዲንሳ 
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሄር