የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን አማራና ትግራይ ክልል «መስራት ተሳነኝ» አለ
ሐሙስ፣ ጥቅምት 7 2017በአማራና በትግራይ ክልሎች ያሉ ወቅታዊ ሁኔታዎች ሥራውን በአግባቡ እንዲስራ እንዳላስቻለው የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን አመለከተ። በአማራ ክልል የተወሰኑ ሥራዎች ቢሞከሩም አጠጋቢ አንዳልነበሩ ነው ኮሚሽኑ የገለጠው። በአማራ ክልል በትጥቅ ትግል ከመንግሥት ጋር ለሚዋጉ ኃይሎች በምክክሩ እንዲሳተፉ በይፋ ጥሪ ቢቀርብም በተደራጀ መልኩ ምላሽ እንዳልተገኝም ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሁሉን አቀፍ የሆነ ብሔራዊ ምክክር ለማድረና ከዚህ በፊት ይነሱ የነበሩ ትርክቶች መቋጫ እንዲያገኙ ለማድረግ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ገብቶ የአጀንዳ መለየትና ሌሎች እንቅስቃሴዎችንም መስራት ከጀመር ሰነባብቷል።
በአማራ ክልል ያለው የፀጥታ ሁኔታ በአጀንዳ አሰባሰብ ላይ ችግር ስለመፍጠሩ
ያም ሆኖ በአማራ ክልል ባለው ወቅታዊ የፀጥታ መታወክ ምክንያት የተፈለገውን ያክል ሥራ በክልሉ ማከናወን እንዳልተቻለ የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ ዛሬ ለዶይቼ ቬሌ በስልክ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል እንደሌሎች ክልሎች በሚፈለገው መንገድ መድረስና በጊዜ ሥራውን ማከናወን ያልተቻለው በክልሉ ባለው ወቅታዊ የፀጥታ ችግር እንደሆነ ነው የገለጹት።
ችግሩ እንዳለ ቢሆንም የተወሰኑ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰው ሆኖም አጥጋቢ የሚባል እንዳልሆነ ነው አቶ ጥበቡ ያስረዱት።
ምክክር ኮሚሽኑ ያከናወናቸው ተግባራት
የዩኒቨርሲቲ መምህራን ስልጠና እንደተሰጣቸው ያመለከቱት ኃላፊው፣ ከኮሚሽኑ ጋር የሚሰሩ ሌሎች ተባባሪ አካላትም የተሻለ የፀጥታ ሁኔታ ባለባቸው ወረዳዎች የአጀንዳ መረጣ ተሳታፊዎችን ለመምረጥ ሙከራዎች አድርገውል ብለዋል። ሆኖም ግን የሚፈለገውን ያክል እንዳልሆነ ገልጥዋል።
አሰልጣኞችና ተባባሪ አካላት ወደ ወረዳዎች ተንቀሳቅሰው መስራት ባለምቻላቸውም ኮሚሽኑ ባቀደው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ሠራዎችን ማከናወን አልቻለም ብለዋል።
የሚፈለገውን ያክል መስራት አለመቻል
የፀጥታ ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች ማካተት ባለመቻሉ፣ አሰልጣኞችና ተባባሪ አካላት ተዘዋውረው በሚፈለገው ልክ ባለመስራታቸው ተግዳሮቶች ተፈጥረዋል ነው ያሉት። በአጠቃላይ ወቅታዊ ሁኔታው ኮሚሽኑ በእቅዱ መሰረት አንዳይጓዝ አድርጎታል ብለዋል።
ሰፊ ድርሻ ያለው የአማራ ክልል ባልተካተተበት ሁኔታ የአጀንዳ ማሰባስብም ሆነ የምክክር ጉባኤ ማካሄድ ከፍተኛ ተፅዕኖ ስለሚያሳድር ኮሚሽኑ የክልሉ ነዋሪዎች በአጀንዳ መረጣና በምክክር ጉባኤ በንቃት እንዲሳተፉ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመሆን ጥርቱ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
“አማራ ክልል ትልቁ ባለድርሻ ነው፣ ሰፋ ያለ ሕዝብ የሚኖርበት ክልል ነው፣ የሀሳብ መሪዎች ያሉበት ክልል ነው፣ ምሁራን ያሉበት ነው፣ በረካታ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያቀፈ አካባቢ ነው፣ ይህንን ሰፊ ድርሻ ያለው ክልል ያላካተተ የሚደረግ የቀረጻም ሆነ የምክክር ጉባኤ በጊዜ ለማካሄድ የራሱ ጫና ይኖረዋል” ብለዋል።
በትጥቅ ትግል ላይ ላሉ አካላት የተደረግ ጥሪ
በአማራ ክልል በትጥቅ ትግል ከመንግስት ጋር ውጊያ ላይ ያሉ ኃይሎቸ በምክክር ሂደቱ እንዲሳተፉ በይፋ ጥሪ የተደረገላቸው ቢሆንም እስካሁን በተደራጀ መልክ ምላሽ እንዳልተገኝና እነኚህ ወገኖች የኮሚሽኑን ጥሪ እንዲቀበሉ ግፊቱ አይቋረጥም ብለዋል።
በትግራይ ክልልም በተመሳሳይየአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሥራዎችን መስራት እንዳልቻለ የተናገሩት አቶ ጥበቡ ኮሚሽነሮች በተለያዩ ጊዜዎቸ ወደ መቀሌ በመሄድ ከክልሉ ጊዜያዊ መንግስት ጋር መወያየታችውን ተናግረዋል። ሆኖም በከልሉ ቀዳሚ ሥራዎች መኖራቸውን ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ስለተገለፀላቸው ለጊዜው በትግራይ የኮሚሽኑ ሥራዎች አልተጀመሩም ነው ያሉት።
ዓለምነው መኮንን