1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዲሱ ገዥ ማሞ ምኅረቱ ምን ይጠብቃቸዋል?

ሐሙስ፣ ጥር 18 2015

አቶ ማሞ ምኅረቱ "ገንዘብ የማተምና የማሠራጨት፣ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ማስተዳደር፣ የገንዘብ ፖሊሲ የማውጣትና የመተግበር" ኃላፊነት የተሰጠውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በገዥነት ሲመሩ በርካታ ፈተናዎች ይጠብቋቸዋል። የዋጋ ንረትና የውጭ ምንዛሪ እጥረት የባንኩና የገዥውን መፍትሔ ከሚሹ መካከል ናቸው። ስለ ሹመታቸው ባለሙያዎች ምን ይላሉ?

https://p.dw.com/p/4MhIC
Mamo Mihretu
ምስል CC BY 2.0/U.S. Institute of Peace

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዲሱ ገዥ ማሞ ምኅረቱ ምን ይጠብቃቸዋል?

የ44 ዓመቱ ጎልማሳ ማሞ ምኅረቱ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ባንክ ገዥ ቢሮ ሲረከቡ በዶክተር ይናገር ደሴ የአመራር ዘመን ከ30 በመቶ የተሻገረው የዋጋ ንረት መፍትሔ የሚሻ አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኖ ይጠብቃቸዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ግሽበቱን ወደ "ነጠላ አሐዝ የማውረድ" ዕቅድ ቢኖረውም ተሰናባቹ ገዥ ይናገር ደሴ ግን እስከ ሰኔ ባሉት ወራት ይሳካል የሚል እምነት የላቸውም።

የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ "የዋጋ ግሽበት እና ብር ከውጭ አገር ገንዘቦች ጋር" ሚዛኑን የጠበቀ የምንዛሪ ተመን እንዲኖረው ማድረግ  የብሔራዊው ባንክ አንገብጋቢ ጉዳዮች እንደሆኑ ይናገራሉ።

አቶ ማሞ በገዥነት የተሾሙለት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ "ገንዘብ የማተምና የማሠራጨት፣ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ማስተዳደር፣ የገንዘብ ፖሊሲ የማውጣትና የመተግበር፣ ለገንዘብ ድርጅቶች ፈቃድ መስጠትና መቆጣጠር" ላይ እንዲያተኩር ሆኖ የተቋቋመው በ1955 ነበር። የባንኩን ማቋቋሚያ አዋጆች በማሻሻል ደርግ እና ኢሕአዴግ በተለያዩ ጊዜያት ይከተሏቸው ከነበሩ የፖለቲካ ፍልስፍናዎች የተጣጣመ ሚና እንዲኖረው ሊያደርጉ ሞክረዋል። የብሔራዊ ባንኩም ሆኑ የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ያሉባቸው ችግሮች ለረዥም ዓመታት ሲንከባለሉ የቆዩ እና በተለያዩ ምክንያቶች እየተወሳሰቡ የሔዱ ናቸው።

"ባለፉት [ዓመታት] በተወሰዱ የኤኮኖሚ ፖሊሲ ውሳኔዎች የዋጋ ንረት 30 በመቶ ገደማ ነው። የመገበያያ ገንዘብ በመዳከሙ ምክንያት የኢትዮጵያ የዕዳ ክፍያ በ14 ቢሊዮን ዶላር ወይም በ760 ቢሊዮን ብር ጨምሯል" የሚሉት ዋይኤችኤም የተባለው የቢዝነስ እና የመዋዕለ-ንዋይ አማካሪ ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ሐይለመስቀል በብሔራዊው ባንክ ገዥ ላይ የተደረገው ሹም ሽር አስፈልጊ እንደነበር ያምናሉ።

"አንድ ቢሊዮን ዶላር ስትበደር ከታክስ ሰብስበህ የምትከፍለው የዛሬ አምስት ዓመት 22 ቢሊዮን ብር ነበር። አሁን 54 ቢሊዮን ብር ነው። ስለዚህ በሁለት ዓመት ይከፈል የነበረው የኢትዮጵያ ዕዳ አሁን በአምስት ዓመትም አይከፈልም" የሚሉት አቶ ያሬድ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ማሽቆልቆልን ጨምሮ ብሔራዊውን ባንክ እና ኢትዮጵያን የሚፈታተኑ "በጣም ብዙ የኤኮኖሚ ፖሊሲ ችግሮች አሉ" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

የቀድሞው የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ግሽበቱን ወደ "ነጠላ አሐዝ የማውረድ" ዕቅድ ቢኖረውም ተሰናባቹ ገዥ ይናገር ደሴ ግን እስከ ሰኔ ባሉት ወራት ይሳካል የሚል እምነት የላቸውም።ምስል picture-alliance/M.Kamaci

አቶ ማሞ ምኅረቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ በሚሆኑባቸው በመጪዎቹ ዓመታት አገሪቱ ዳጎስ ያለ የውጭ ዕዳ ክፍያ ይጠብቃታል። መፈትሔ ያልተበጀለት የአገሪቱ የንግድ ሚዛን መጓደል፣ ኢትዮጵያ ከውጭ አገራት እና ተቋማት ታገኝ የነበረውን እርዳታ ካሸሸው የሁለት ዓመታት ጦርነት ጋር ተዳምሮ የውጭ ምንዛሪ ክምችቷ እያሽቆለቆለ ስትፈተን ቆይታለች።

ተሰናባቹ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደርን ጠበቅ የሚያደርግ መመሪያ ሥራ ላይ በማዋል ለፈተናው ጊዜያዊ መፍትሔ ለማበጀት ሞክረው ነበር። በተለምዶ "ጥቁር" እየተባለ የሚጠራውን የውጭ ምንዛሪ የጎንዮሽ ገበያ ለመቆጣጠር የተወሰዱ እርምጃዎች ቢኖሩም ሥር ለሰደደው ችግር ዘላቂ መፍትሔ አላበጁም።

አቶ ማሞ የተሾሙት የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ምንዛሪ ግብይት በአቅርቦት እና ፍላጎት እንዲወሰን ያደርጋል ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት ነው። በእርግጥ የገንዘብ ሚኒስትር ድኤታው ዶክተር እዮብ ተካልኝ ጉዳዩን " መሠረተ-ቢስ" ብለው ቢያጣጥሉትም የመንግሥታቸው ሰነዶች "በገበያ ፍላጎትና አቅርቦት የሚመራ የውጭ ምንዛሪ ተመን" በመጪዎቹ ዓመታት ተግባራዊ መሆኑ እንደማይቀር የሚጠቁሙ ናቸው። እነዚህ ጉዳዮች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና ገዥውን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚመለከቱ ናቸው።

አቶ ማሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ባለፉት ዓመታት ተግባራዊ የሚያደርጋቸውን የኤኮኖሚ ማሻሻያዎች በማስፈጸም ረገድ ስማቸው በግንባር ቀደምትነት ከሚጠራ ባለሥልጣናት አንዱ ቢሆኑም የትምህርት ዝግጅታቸው እና የሥራ ልምዳቸው ከአዲሱ ሹመታቸው የተለየ ነው። ይኸ ታዲያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ጥር 12 ቀን 2015 የሰጡትን ሹመት በአንክሮ በተከታተሉ በርካታ ባለሙያዎች ዘንድ አቶ ማሞ ለኃላፊነቱ ምን ያክል ብቁ ናቸው? የሚል ጥያቄ አስነስቷል።

የብሔራዊ ባንክ ገዥዎችን በሙያ ብቃት፣ ለኅትመት ባበቁት ጽሁፍ እና በሚያቀነቅኑት የኤኮኖሚ ፖሊሲ መዝኖ መሾም "ከቀረ ቆይቷል" የሚሉት አቶ ያሬድ ሐይለመስቀል የባንኩ ፖሊሲም በጥናት ላይ የተመሠረተ መሆኑ ቀርቷል ሲሉ ይነቅፋሉ። "የአቶ ማሞ ምኅረቱ መሾምም ብዙ ልዩነት የለውም" የሚሉት አቶ ያሬድ በኢትዮጵያ "የኤኮኖሚ ፖሊሲ ላይ የጻፉት ነገር፤ ያሳተሙት ወይም የተናገሩት ፖሊሲ የለም" ብለዋል። በዚህ ምክንያት ሹመታቸው "ብሔራዊ ባንክ ካለበት ሁኔታ አኳያ ምንም ለውጥ አያመጣም" ከሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል።

በዚህ ሐሳብ የሚስማሙት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ "ይናገር ደሴም የትምህርት ዝግጅታቸው እና የሥራ ልምዳቸው ከብሔራዊ ባንክ ጋር የተያያዘ አይደለም። የሰሩት ዶክትሬትም ከብሔራዊ ባንክ ጋር ግንኙነትም የለውም" ሲሉ ይኸ ፖለቲካዊ ሹመት ከማሞ ምኅረቱ በፊት የተጀመረ እንደሆነ አስረድተዋል።

ለረዥም ዓመታት ብሔራዊ ባንክ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች በገዥነት ይሾሙለት የነበረ ቢሆንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ከያዙ በኋላ ግን "የፖለቲካ ሹመት ወደ መሆን መጥቷል" ሲሉ ዶክተር አብዱልመናን ተናግረዋል። ከሰኔ 2010 ጀምሮ ለአራት ዓመታት ከስምንት ወራት ገደማ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ የነበሩት ዶክተር ይናገር ደሴ እንደ አቶ ማሞ ምኅረቱ ሁሉ የትምህርት ዝግጅታቸው እና የሥራ ልምዳቸው ከኃላፊነታቸው የራቀ ነበር። ባንኩን በገዥነት የመሩት አቶ ተክለወልድ አጥናፉ፣ ተሰናባቹ ዶክተር ይናገር ደሴ እና የአሁኑ አቶ ማሞ ምኅረቱ የገዢው ፓርቲ አባላት ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
ለረዥም ዓመታት ብሔራዊ ባንክ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች በገዥነት ይሾሙለት የነበረ ቢሆንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ከያዙ በኋላ ግን "የፖለቲካ ሹመት ወደ መሆን መጥቷል" ሲሉ የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ ተናግረዋል። ምስል Tiksa Negeri/REUTERS

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምኅረቱ ፈተና ግን ከትምህርት ዝግጅታቸው እና ከሥራ ልምዳቸው የሚመነጭ ብቻ አይደለም። ከዋጋ ንረት እና ከውጭ ምንዛሪ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በብሔራዊ የማክሮ ኤኮኖሚ ኮሚቴ እንደሚወሰን የሚናገሩት ዶክተር አብዱልመናን "ማሞ የብሔራዊ ባንክ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ መወሰን አይችሉም" ሲሉ ሥልጣናቸው የተገደበ እንደሚሆን ገልጸዋል።

ብሔራዊ የማክሮ ኤኮኖሚ ኮሚቴው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራ እና አስር ገደማ አባላት ያሉት ነው። አቶ ማሞ ከዚህ ቀደምም የዚሁ ብሔራዊ የማክሮ ኤኮኖሚ ኮሚቴ አባል ነበሩ። "ወረቀት ላይ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ተብሎ የተቋቋመ አለ። በተግባር ግን በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው ብሔራዊ የማክሮ ኤኮኖሚ ኮሚቴ ስለሚወስን ማሞ የተወሰነውን አስፈጻሚ እንጂ በግላቸው የሚወስኑት ጉልህ ውሳኔ ስለሌለ ብዙ ለውጥ ያመጣሉ የሚል እምነት የለኝም" በማለት ዶክተር አብዱልመናን አስረድተዋል።

አቶ ማሞ በገዥነት የሚመሩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 30 ገደማ ባንኮችን፣ አስራ ስምንት የመድን ዋስትና ኩባንያዎችን እና አርባ ገደማ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትን የመቆጣጠር እና በበላይነት መምራት ኃላፊነት የተጣለበት ነው። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ከሶስት እስከ አምስት ለሚሆኑ የውጭ ባንኮች ፈቃድ መስጠት የሚያስችለውን ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ ተዘግቶ የቆየውን የፋይናንስ ዘርፍ ለድንበር ተሻጋሪ ውድድር ለመክፈት ቆርጧል።

ረቂቅ አዋጁ ጸድቆ ሥራ ላይ ሲውል የውጪ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ መግባት የብሔራዊ ባንክን የቁጥጥርና የክትትል አቅም ሊፈታተን የሚችል እንደሚሆን ይጠበቃል። "በባንክ ክትትል እና ቁጥጥር  ከተወሰኑ የመንግሥት ባንኮች ጋር በተያያዘ መላላት ቢኖርም አጠቃላይ የኢትዮጵያ ባንኮች ክትትል ጥሩ ሲሰራ ነበር።" የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን "ማሞ ቢሾሙም ባለው ሁኔታ ይቀጥላል የሚል እምነት ነው ያለኝ። እዚያ ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል የሚል እምነት የለኝም" ሲሉ ተናግረዋል።  

ማሞ ምኅረቱ እና አሕመድ ሽዴ ከኤፍኤስዲ አፍሪካ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጋር
አቶ ማሞ በብሔራዊ ባንክ ገዥነት ከመሾማቸው በፊት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነበሩ። ኩባንያው የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ኢትዮ ቴሌኮምን ጨምሮ በርካታ ተቋማትን የሚያስተዳድር ነው። መቀመጫውን በናይሮቢ ካደረገው ኤፍኤስዲ አፍሪካ የተባለ ተቋም ጋር የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅን ያቋቁማል። ምስል Ethiopian Investment Holdings (EHI)

አቶ ማሞ ምኅረቱ ማን ናቸው?

አቶ ማሞ የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ኤጀንሲ (ወመዘክር) እንዲሁም የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴርን ወደ ሚያጎራብተው አዲሱ ቢሯቸው ከማምራታቸው በፊት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነበሩ። የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨምሮ 27 የመንግሥት ድርጅቶችን በሥሩ የሚያስተዳድረውን ተቋም የመሩት ግን ለአንድ ዓመት ገደማ ብቻ ነው። ይኸ ግዙፍ ኩባንያ ከመመሥረቱ በፊት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የምጣኔ ሐብት ፖሊሲ አማካሪ እና ዋና የንግድ ተደራዳሪ ሆነው ሰርተዋል።

አቶ ማሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ጥብቅና ተምረው ሥራ የጀመሩት በመምህርነት ነው። በኔዘርላንድስ እና በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ተቋማት በጥምረት በንግድ እና መዋዕለ ንዋይ ጉዳይ የሚሰጡትን ትምህርት ተከታትለዋል። በንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በድርድር ጉዳይ በአማካሪነት ለሶስት ዓመታት ገደማ ከሰሩ በኋላ በአሜሪካው ሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በኬኔዲ ትምህርት ቤት በኤኮኖሚ ፖሊሲ የማስተርስ ዲግሪ አግኝተዋል። ከዚያ በኋላ ነው በኬንያ ዋና ከተማ የሚገኘውን የዓለም ባንክ ጽህፈት ቤት የተቀላቀሉት።

ከአቶ ማሞ ምን ይጠበቃል?

የቀድሞው የኢትዮጵያ መሪ መንግሥቱ ኃይለማርያም ሥልጣን ላይ በነበሩባቸው ዓመታት የወጡ መመሪያዎች ሥራ ላይ እንደሚገኙ የሚናገሩት አቶ ያሬድ "ምንድነው ጥቅማቸው?" ብሎ በመፈተሽ መቀየር ከብሔራዊ ባንክ ገዥ ቀዳሚ የቤት ሥራዎች መካከል ሊሆን እንደሚገባ ይጠቅሳሉ። አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምኅረቱ "የመቀየር፣ የማስተካከል ታሪክ የመስራት ፍላጎት ካላቸው ባለሙያዎችን ሰብስበው የኢትዮጵያን የኤኮኖሚ ፖሊሲ መቀየድ ይችላሉ" ሲሉ አቶ ያሬድ ተስፋቸውን ገልጸዋል።

የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ በበኩላቸው እንደሚሉት አቶ ማሞ "ብሔራዊ ማክሮ ኤኮኖሚ ኮሚቴውን በማሳመን የተረጋጋ የኢትዮጵያ ብር እንዲኖር የሚያስችል ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረግ" አለባቸው። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው "የኢትዮጵያ መንግሥት የበጀት ጉድለት ሲኖርበት ቀጥታ ወደ ብሔራዊ ባንክ እየሔደ የሚበደረውን ነገር እንዲቀንስ ጠንካራ አቋሚ ሊኖራቸው ይገባል" የሚል እምነት አላቸው።  

እሸቴ በቀለ

ታምራት ዲንሳ