1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ባንኮች እና ደኅንነታቸው

ሰኞ፣ መጋቢት 9 2016

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ.ም ምሽት "የሲስተም ችግር" እንዳጋጠመው ገልጾ ነበር። በዚሁ ዕለት በተለይ በውስን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ቁጥራቸው በውል ያልተለየ ተማሪዎች በፈጣን የገንዘብ መክፈያ መሣሪያ (ATM) በሒሳብ ቁጥራቸው እንኳን የሌለውን ያህል የገንዘብ መጠን ያለ አግባብ መመንተፋቸው ተነግሯል።

https://p.dw.com/p/4drqu
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክምስል Solomon Muchie/DW

በንግድ ባንክ ላይ የተፈጠረው ምንድን ነው?

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፈው ቅዳሜ ደረሰብኝ ስላለው "የሲስተም ችግር" ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል። የባንኩ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ዛሬ ከቀትር በኋላ ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ ባለፈው አርብ ሌሊት ተፈጠረ ባሉት ስህተት ጤናማ ያልሆነ የገንዘብ እንቅስቃሴ እንደነበር ፤ ሆኖም በባንኩ የደንበኞች የግል ሒሳብ ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ ገልፀዋል።አክለውም በዚሁ ዕለት ከ490 ሺህ በላይ የገንዘብ ዝውውር እንደነበር ገልፀው በዋናነት በዚህ ድርጊት የተሳተፉት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንደነበሩና ገንዘብ እየመለሱ መሆኑን ተናግረዋል።  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ችግሩ የተከሰተው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደኅንነት ፍተሻ እና የማሻሻያ ሥራ ጋር ተያይዞ መሆኑን እና የፋይናንስ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል እንዳልሆነ ማረጋገጡን ገልጿል።ዶቼቬለ በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው አንድ የፋይናንስ ባለሙያ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ማደግ ፣ ለውጭ ባንኮች የሚሰጥ በሀገር ውስጥ የመሥራት ዕድል እንዲሁም የሰነድ መዋዕለ ንዋይ መጀመር በባንኮች ላይ የሚፈፀሙ የማጭበርበር ወንጀሎችን አብረው እንደሚያሳድጉ  ለድቼ ቬለ ገልጸዋል።  ባለሙያው በባንኮች ላይ የሚደርሥ የአሠራር ችግርም ይሁን ሊደርስባቸው የሚችል የማጭበርበር ጥቃት ፤ ባንኮች ላይ ያለውን መተማመን ሊቀንስ ፣ ሰዎችን ወደ መደበኛ የጥሬ ገንዘብ ልውውጥ ሊመልሳቸው  እና በባንኮች እና በደንበኞቻቸው መካከል ውዝግብ ሊፈጥር እንደሚችል ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ባንኮች ለማጭበርበር ምን ያህል ተጋላጭ ናቸው?

በንግድ ባንክ ላይ የተፈጠረው ምንድን ነው?

ባለፈው ቅዳሜ  መጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ከምሽት ጀምሮ "የሲስተም ችግር" እንዳጋጠመው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገልጾ ነበር። በዚሁ ዕለት በተለይ በውስን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ቁጥራቸው በውል ያልተለየ ተማሪዎች በፈጣን የገንዘብ መክፈያ መሣሪያ (ATM) በሒሳብ ቁጥራቸው እንኳን የሌለውን ያህል የገንዘብ መጠን ያለ አግባብ መመንተፋቸው ተነግሯል።ባንኮች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ 70 በመቶውን ለብሔራዊ ባንክ እንዲያስተላልፉ ታዘዙ
ይህንን የተገነዘቡ የአዲስ አበባ፣ የጅማ እንዲሁም የአወሳ ዩኒቨርሲቲዎች ገንዘብ በሕገ ወጥ መንገድ ወጭ ያደረጉ ሁሉ ገንዘቡን ተመላሽ እንዲያደርጉ ማሳሰቢያ አውጥተዋል። 

የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ካሉበት ኃላፊነቶች አንዱ መሰል የገንዘብ ተቋማት በማንኛውም መንገድ የገንዘብ ፍሰት ሥርዓታቸው እንከን እንዳይገጥመው ጥበቃ ማድረግ ነው። ስማቸውን መግለጽ ካልፈለጉ የባንክ ባለሙያዎች ባገኘነው መረጃ ባንኮች ደኅንነታቸውን ለመጠበቅ ሲሉ የመረጃ የሥራ ክፍሎችን በዳይሬክቶሬት ደረጃ ያደራጃሉ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምስል Solomon Muchie/DW

የፋይነንስ ባለሙያ አስተያየት

የኢትዮጵያ ባንኮች የውስጥ የአሠራር ችግርን ተከትሎ በሚመጣ ፈተናም ይሁን ከውጭ ከሚቃጣባቸው የማጭበርበር ጥቃት እንዲጠበቁ ምን ያህል ብቁ አሠራር አላቸው የሚለውን የጠየቅናቸው የፋይናንስና የኢኮኖሚ አማካሪና መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ዳዊት ታደሰ  «የፎረንሲክ፣ አካውንቲንግ እና ፋይናንስ ማለት እውቀቱ የለም። ክስተቱም ሲከሰት እንዴት ነው ምርመራ የምናደርገው? የሚለውን የምንለይበት መንገድ ገና የጎለበተ አይደለም። » ብለዋል። ባለሙያው መሰል ችግሮችን ይቀርፋል ያሉት የትምህርት ዘርፍ በሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ እንዲሰጥ የትምህርት ንድፉ ተቀርጾ መዘጋጀቱን ገልፀዋል።የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዲሱ በዋጋ ላይ የተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ ምን ይፈልጋል?
የኮምፒውተር ጤናማነትን መቆጣጠር ወሳኝ የባንኮች ሥራ መሆኑን የሚገልፁት ረዳት ፕሮፌሰር ዳዊት ታደሰ የገንዘብ ማጭበርበር ወንጀሎች እየተወሳሰቡ ሊሄዱ እንደሚችሉ ገልፀዋል። የቴክኖሎጂው ማደግ ፣ ኢትዮጵያ ለውጭ ባንኮች በር የመክፈትና አሠራር የመዘርጋት አዝማሚያ ማሳያቷ እንዲሁም ፣ የሰነድ መዋዕለ ንዋይ ብቅ ብቅ ማለትን በአስረጂነት ጠቅሰዋል።

የንግድ ባንክ እና የብሔራዊ ባንኮች መግለጫ

ባለፈው ሳምንት በንግድ ባንክ ላይ ያጋጠመው የአገልግሎት መቋረጥ በባንኩ አገልግሎት መስጫ ሥርዓት ላይ ከተደረገ የደኅንነት ፍተሻና የማሻሻያ ሥራ ጋር የተያያዘ ነው ያለው  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተፈጠረው ችግር የባንኩን፣ የደንበኞቹንና አጠቃላይ የፋይናንስ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል አለመሆኑን ማረጋገጡን አስታውቋል።
ብሔራዊ ባንክ "በአሁኑ ጊዜ ቡሁሉም የፋይናንስ ተቋማት የሚገኙ የፋይናንስ ሥርዓቶች ደኅንነታቸው የተጠበቀ"  መሆኑንም አስታውቋል።
ሰሎሞን ሙጬ 
ኂሩት መለሰ
ታምራት ዲንሳ