1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የዘጠኝ ወራት ዘገባ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 30 2015

በኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፅሞ ተጠያቂ የሚሆን አካል የለም የሚለው እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል። ሥራውን በገለልተኝነት እንደሚያከናውን ያስታወቀው ኢሰመኮ ኢትዮጵያ ውስጥ ውስብስብና ሥር የሰደደ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መኖሩን አስታውቆ መፍትሔውም የፖለቲካ ቁርጠኝነት መሆኑን ጠቅሷል

https://p.dw.com/p/4R3F1
Äthiopien Addis Ababa Daniel Bekele Äthiopische Menschenrechtesbeauftragter
ምስል Yohannes G/Egziabher/DW Addis Ababa

«በኢትዮጵያ ሰባት አሳሳቢ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች አሁንም ቀጥለዋል »ኢሰመኮ

የሰብዓዊ መብት ጥሰት በሚያደርሱ እና ጥሰቶችን አስቀድሞ ባለመከላከል ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ የመንግሥት አስፈፃሚ አካላት እንዲጠየቁ ግፊት እንዲያደርግ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማሳሰቢያ ቀረበ። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የዚህ ዓመት የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈፃፀሙን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዛሬ ሲያቀርብ  ሰባት አሳሳቢ ያላቸው የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች አሁንም  በአሳሳቢነታቸው ቀጥለዋል ሲል አስታውቋል።
በአማራ ክልል ያለው ወታደራዊ እርምጃ፣ የዘፈቀደ እስርና ተገቢ ያልሆነ አያያዝ፣ ተመጣጣኝ ያልሆነ የኃይል አጠቃቀም፣ በሚዲያና ተቃዋሚዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት፣ ከቦታ ወደ ቦታ መንቀሳቀሰ መብት ላይ የተጣለ የዘፈቀደ ገደብ፣ ሕጋዊ ሂደትን ያልተከተለ የቤቶች ፈረሳ፣ በግዳጅ ማስነሳትና የኑሮ ውድነት የተነሳ የደረሰው እንግልትና የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ጥሰቶች እንዲሁም በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ማቋቋም አሳሳቢነታቸው የቀጠለ ተብለው የቀረቡ  ጉዳዮች ናቸው።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መብት ጥሰት፣ በጋምቤላ ክልል ነዋሪዎች ከደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች የሚደርስ ጥቃት፣ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚደርስ የዜጎች መብት ጥሰት እና ለጥፋቶች ተጠያቂነት በአግባቡ አለመፈፀሙን በማንሳት ኮሚሽኑ ጠንክሮ እንዲሠራ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በበኩሉ በኢትዮጵያ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደተፈጸሙ ጠቅሶ በተለይ ተጠያቂነት እንዲሰፍን የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግና ለዚህም ምክር ቤቱ እገዛ እንዲያደርግ ጠይቋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ ( ዶ/ር ) በዋናነት በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ ምርመራ ከተደረገ በኋላ የሚሰጧቸው ምክረ ሀሳቦች ተፈፃሚነት እና  ያንን ተከትሎ ተጠያቂነትን ማስፈን ላይ ምክር ቤቱ  እገዛ እንዲያደርግ አሳሳቢ ያሉትን በመጥቀስ ጠይቀዋል።
በምክር ቤቱ የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፅሞ ተጠያቂ የሚሆን አካል የለም የሚለው እንዳሳሰባቸው ጠይቀዋል።
ሥራውን በገለልተኝነት እንደሚያከናውን ያስታወቀው ኢሰመኮ ኢትዮጵያ ውስጥ ውስብስብ እና ሥር የሰደደ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መኖሩን አስታውቆ መፍትሔውም የፖለቲካ ቁርጠኝነት መሆኑን ጠቅሷል

Äthiopien l Gebäude Ethiopian Human Rights Commission( EHRC)
ምስል Solomon Muchie/DW

ሰሎሞን ሙጬ 

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ