1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢሰመኮ እና የአፋር ተፈናቃዮች ስጋት

ሐሙስ፣ የካቲት 16 2015

በአፋር ክልል በጦርነት ምክንያት ለተደጋጋሚ መፈናቀል የተጋለጡ የሁለት ዞን ነዋሪዎች ለከፍተኛ የሰብአዊ ቀውስ መጋለጣቸው ተገለጠ። በተጨማሪም የንግድ እንቅስቃሴው ገደብ በመኖሩ ላልተገባ ኢኮኖሚያዊ ጫና መጋለጣቸውን እና በዘላቂነት እንዲቋቋሙ አለመደረጉን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባደረገው ክትትል ማረጋገጡን አስታወቀ።

https://p.dw.com/p/4NtnT
Äthiopien l IDPs in Afar region
ምስል Seyoum Hailu/DW

የኢሰመኮ እና የአፋር ተፈናቃዮች ስጋት

 ኮሚሽኑ ከኅዳር 10 እስከ ታኅሣሥ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. አደረግሁት ባለው ክትትል ተፈናቃዮች ቤተሰቦቻቸውን በሞት ከማጣት ባለፈ ለአካል ጉዳት ብሎም ለንብረት ውድመት ሰለባ መሆናቸውን ገልፀዋል። የኮሚሽኑ ዘገባ «በትግራይ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የሚኖሩ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ዳግም ግጭት ሊከሰት ይችላል የሚል ሥጋት እንዳለባቸው» ይፋ አድርጓል።
ኮሚሽኑ ተመላሾች በራሳቸው ሙሉ ፈቃድ የተመለሱ ቢሆንም፤ መደበኛ ኑሯቸውን ለመቀጠል የሚያስችላቸውን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ለተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ ማፈላለግን በተመለከተ ችግር መኖሩን በክትትሉ አመልክቷል። 
በአፋር ክልል የጦርነት ተፈናቃዮች በተለያዩ የመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ሆነው የቆዩ ሲሆን ከወራት በፊት በፈቃደኝነት ወደነበሩበት እንዲመለሱ ተደርጓል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከኅዳር 10 እስከ ታኅሣሥ 1 ቀን 2015 ዓ.ም አደረግሁት ባለው ክትትል ተፈናቃዮች ወደቀደመ መኖሪያቸው ሲመለሱ ሦስት መሠረታዊ ችግሮች ገጥሟቸዋል።
የነበራቸው ንብረት እና ሀብት ሙሉ በሙሉ መውደሙ ፣ ሲመለሱ በመንግሥትም ሆነ በሌሎች አካላት የተለየ የመቋቋሚያ እገዛ አለማግኘታቸው እና የሰላም ስምምነት እስከተፈረመበት ጊዜ ድረስ የንግድ እንቅስቃሴ ገደብ በመንግሥት ተጥሎ በመቆየቱ አኗኗራቸው ላይ ተጽእኖ ማሳደሩ መሆናቸውን በኢሰመኮ የሰመራ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኡስማን አህመድ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።
ኢሰመኮ ጦርነቱ ካስከተለው የሰብአዊ ቀውስ በተጨማሪ በቂ እና ወቅቱን የጠበቀ የሰብአዊ ድጋፍ አለመቅረቡ ፣ የንግድ እንቅስቃሴ ገደብ አለመነሳቱ የተፈናቃዮችን ሕይወት ፈታኝ አድርጎታል ሲል አስታውቋል። አቶ አብርሃ የተባሉ ተፈናቃይ በአፋር አዋሳኝ አካባቢ የትግራይ ታጣቂዎች ሥጋት ሆነውባቸው እንደቆዩ ፣ የኬላ ፍተሻና ክፍያው ከፍተኛ መሆኑ  ለሸቀጦች ዋጋ መናር ምክንያት ሆኖ እንደነበር ገልፀዋል።
ጦርነቱ በስፋት የጎዳው የአብአላ ከተማ ወጣቶች ጽ/ቤት ኃላፊ  አቶ አብደላ አሚንን ለተደጋጋሚ መፈናቀል ተዳርገው ፣ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ የቆዩት ሰዎች ሥጋት ምክንያት እንደሆን ጠይቀናቸዋል። ኢሰመኮ ባከናወነው ክትትል የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችና ተመላሾች በቂ፣ ወቅቱን የጠበቀ እና ተደራሽ ምግብ፣ ውኃ፣ መጠለያ፣ የጤና ፣ የትምህርት እና ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ያካተተ የሰብአዊ ድጋፍ እየቀረበላቸው እንዳልሆነ ተመልክቷል፡፡ እነዚህን ሰዎች ጦርነት ዳግም እንዳይነሳ በሚል ለሥጋት የዳረጋቸው ጉዳይ ምን እንደሆነ በኢሰመኮ የሰመራ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኡስማን አህመድን ጠይቀናቸዋል።
ኢሰመኮ ክትትል ባደረገበት ወቅት ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ በአፋር ክልል ዞን ሁለት እና ዞን አራት በኩል በየብስ ትራንስፖርት ወደ ትግራይ ክልል ተጓጉዘው ይገቡ የነበሩ ነዳጅን ጨምሮ የተለያዩ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች እንዳይገቡ የተጣለው እገዳ ባለመነሳቱ በሁለቱ ዞኖች ውስጥ የሚደረገውን የንግድ እንቅስቃሴ ከመገደቡ በተጨማሪ በፍጆታ ዕቃዎች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ አስከትሎ እንደቆየ ገልጾ እንዲስተካከል ጠይቋል። አቶ አብደላ አሚን ይህንን በተመለከተ ምላሽ ሰጥተዋል። በአፋር ክልል ዞን ሁለት እና ዞን አራት በተደጋጋሚ በሕወሓት ኃይሎች ጥቃት ተከፍቶባቸው ጦርነት ውስጥ የነበሩ ናቸው። እነዚህ አካባቢዎች ሞት፣ መፈናቀል፣ የንብረት ውድመት፣ ዘረፋ እና ሌሎች ችግሮች በስፋት የተስተዋሉባቸው ናቸው።

 Ethiopian Human Rights Commission about SNNPR human rights case
ምስል Ethiopian Human Rights Commission

ሰለሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ