የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የፀጥታ ሥጋት
ማክሰኞ፣ መስከረም 14 2017"በውጭ ኃይላት የሚደረግ የጦር መሣሪያ አቅርቦት መጨረሻው አሸባሪዎች እጅ ላይ ሊወደቅ እንደሚችል" ሥጋት መኖሩን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ ተናገሩ።የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ባልተረጋጋ የደህንነት ሁኔታ ውስጥ የምትገኘው ሶማሊያን በተመለከተ ከተባበሩት መንግሥትታት የሰላም ግንባታ እና ፖለቲካ ጉዳዮች ረዳት ዋና ፀሐፊ ሮዝማሪ ዲካርሎ ጋር በኒውዮርክ ከተነገገሩ በኋላ ነው ይህንን የተናገሩት።
እየተካረረ በመጣው የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ግንኙነት ውስጥ ሶማሊያ የኢትዮጵያ መንግሥት ለፑንትላንድ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ሰጥቷል በሚል ክስ ስታቀርብ፣ ግብጽ በፊናዋ ለሁለተኛ ጊዜ ለሶማሊያ የጦር መሣሪያ ድጋፍ ማድረጓ ተሰምቷል።
በኢኮኖሚ፣ በባህል፣ በፖለቲካ፣ በታሪክ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች የቀረበ ትስስር የነበራቸው ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ግንኙነት መሻከር የአፍሪካ ቀንድን የባለ ብዙ ወገን የግንኙነት መስክ ትኩረት በእጅጉ የሳበ እና ብርቱ የፖለቲካ ውዝግብ መነሃሪያነት እያጎላ መጥቷል። ቀድሞውንም የእርስ በርስ ግጭት እና ጦርነት ብሎም የሽብር ጥቃት ቀውስ የማይለየው ይህ አከባቢ የኢትዮጵያ እና የራስ ገዟ ሶማሊላንድ የባሕር በር ማግኛ የመግባቢያ ስምምነት መፈረምን ተከትሎ ውጥረቱ እና ልዩነቱ እንዲያይል አድርጓል።
ሶማሊያ ኢትዮጵያ ለሌላኛዋ ግዛቷ ፑንትላንድ በሁሉት የጭነት ተሽከርካሪዎች የጦር መሣሪያ ድጋፍ ሰጥታለች በሚል ሰሞኑን ልዩነቱን ይበልጥ የሚያሰፋ ወንጅላ አቅርባለች። ድርጊቱ ሉዓላዊነቷን እንደጣሰ የገለፀችው ሶማሊያ አልፎም በብሔራዊ ደህንነቷን እና በቀጣናው ሥጋትን የሚደቅን መሆኑን በመጥቀስ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሁኔታውን እንዲያወግዙ አቤት ብላለች።
በጉዳዩ ላይ ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ ማብራሪያ የተጠየቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደት ነቢያት ጌታቸው ምላሽ አልሰጡበትም። ለዚሁ ጉዳይ ምላሽ እንዲሰጡበት ትናንት እና ዛሬ ልናገኛቸው ያደረግነው ጥረትም አልተሳካም።
የሶማሊያ መንግሥት ግን ኢትዮጵያን ይህንን ድርጊት ሽን ባስቸኳይ እንድታቆም አሳስባለች። ሶማሊያ ከወራት በፊትም ኢትዮጵያ መሰል የጦር መሣሪያ ዝውውር በሉዓላዊ ግዛቷ ውስጥ ማድረጓን በመጥቀስ ድርጊቱን ኮንና ነበር።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አምባሳደር ታየ አፅቀ ሥላሴ ከሦስት ሳምንታት በፊት በሰጡት መግለጫ አካባቢውን የግጭት ማዕከል የማድረግ እንቅስቃሴ መኖሩን በአጽንዖት ጠቅሰው ነበር።
አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሤ ኒውዮርክ እየተካሄደ ከሚገኙው 79ኛው የመንግሥታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን ከድርጅቱ የሰላም ግንባታ እና የፖለቲካ ጉዳዮች ረዳት ዋና ፀሐፊ ሮዝማሪ ዲካርሎ ጋር ሶማሊያን በተመለከተ ባደረጉት ውይይት ኢትዮጵያ ሽብርተኞችን ለመዋጋት የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥል ስለመግለፃቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫ ያሳያል።
የግብጽ በአካባቢው ፖለቲካ ውስጥ ዘልቆ የመግባት እውነታ በጉል እየተስተዋለ ሲሆን ለሶማሊያ ሁለተኛ ዙር የጦር መሳሪያ አቅርቦት ትናንት መላኳ ጉዳዩን የበለጠ አወሳስቦታል። ግብጽ በሞቃዲሾ ወደብ በኩል ለሶማሊያ የላከችው ከባድ እና ቀላል የጦር መሣሪያዎችን መሆኑ ተነግሯል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ ባልተረጋጋ ባሉት የደህንነት ሁኔታ ውስጥ "በውጭ ኃይላት የሚደረግ የጦር መሣሪያ አቅርቦት መጨረሻው አሸባሪዎች እጅ ላይ ሊወደቅ እንደሚችል" ሥጋት መኖሩን ገልፀዋል።ሚኒስትሩ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ አልሸበብ እጅግ በሀብት አቅሙ የፈረጠመ የሽብር ቡድን መሆኑን ገልፀው የአከባቢው ሁኔታ ለቡድኑ የተመቸ እንዳይሆን አሳስበው ነበር።
ጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ከግብጽ የጦር መሣሪያ ድጋፍ እየወሰደች ያለችው ሠራዊቷን ለማጠናከር ብሎም ከብዙ ሀገራት በተውጣጣ ሰላም አስከባሪ ኃይል የሚጠበቀው ሰላምና ደህንነቷን ለሻሻል ለምታደርገው ጥረት አቅም እንዲሆን መሆኑን ስትገልጽ፣ ራስ ገዟ ሶማሊላንድ ግን ድጋፉ አሳሳቢ እርምጃ መሆኑን በማንሳት በበሩ ስትቃወመው ጊዜ አልወሰደባትም።
ሰለሞን ሙጬ
ነጋሽ መሐመድ
ታምራት ዲንሳ