የአፍሪቃ የተማረ የሰው ኃይል ፍልሰት | ወጣቶች | DW | 18.08.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ወጣቶች

የአፍሪቃ የተማረ የሰው ኃይል ፍልሰት

ብዙ ሀገር ጎብኝቶ ልምድ መቅሰም የሰው ልጅን አስተሳሰብ እንደሚያዳብር አያጠራጥርም። ትልቁ ጥያቄ ግን ከሀገር የወጣው የሰው ኃይል ተመልሶ ወደ ሀገሩ ሄዶ ተሞክሮውን ያካፍል ይሆን ወይ? የሚለው ነው። እነዚህ ሰዎች ወደ ሀገራቸው ተመልሰው የቀሰሙትን እውቀት ለማካፈል ፈቃደኛ እየሆኑ፣ የሚያስፈልጋቸው መገልገያ ሲያጥራቸውስ?

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:30
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
09:30 ደቂቃ

አፍሪቃውያን ተማሪዎች

አንድ ሰው ሀብታምም ይሁን ደሀ፤ ከየትም ሀገር ይሁን ከየት ጥሩ የትምህርት እድል አግኝቶ ካደገ እድለኛ ነው። የተማረ ከሆነ እና ትንሽ ገንዘብ ያለው ከሆነ ደግሞ፤ አዲስ ነገር ለመሞከር መፈለጉ አይቀሬ ነው። እንደ የተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ እና ባህል ድርጅት «ዩኔስኮ» ከሆነ በርካታ ሀገሮች በሚቀጥሉት ሀያ አመታት ውስጥ የተማረ የሰው ኃይል ፍልሰት ይገጥማቸዋል። ሰዎች ሀገራቸውን ጥለው የሚሄዱበት ብዙ ምክንያቶች አሉ። ለአንዳንዶች ኤኮኖሚው ይሆናል፤ እንደ አባዮሚ ኦጉንጂሚ ላሉ ደግሞ ምክንያታቸው እውቀት ፍለጋ ነው።« እውቀት ለኔ በጣም ወሳኝ ነው። አዲስ ነገር ማወቅ እሻለሁ። ነገሮችን በአዲስ መልኩ መስራት፣ አዲስ ሀሳቦችን ማፍለቅ እፈልጋለሁ። ወደፊት ለሀገሬ ምናልጋት ለውጥ ለማምጣት ራሴን በዚህ አይነት መንገድ ነው ማስጓዝ የምፈልገው ።»

 

ናይጄሪያዊው ኦጉንጂሚ ብራዚል ውስጥ  በሳን ፓውሎ ዮኒቨርስቲ ለዶክትሬትነት የሚሰራ የ PHD ተማሪ ነው። ወደ ሀገሩ የመመለስ አላማው፣  ሀገራቸውን ለቀው የሚሄዱ የተማሩ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ የሚመለስ እንዳለም ይጠቁማል። ጉዞው የደርሶ  መልስ ሆኗል። አንዳንዶች እንዲያውም ለትምህርት ተብሎ ሀገርን ለቆ መሄድ በአሁኑ ጊዜ አስፈላጊ ነው ብለው  አያምኑም።  የተባበሩት መንግሥታት የህፃናት መርጃ ድርጅት፣ ዩኔስኮ ዘገባ ጅቡቲን እንደ ምሳሌ ጠቅሶ እንዳመላከተው እአአ ከ2006 ዓም አንስቶ ሀገሪቱን ለቆ የወጣው የተማረ የሰው ኃይል በመመለስ ላይ ይገኛል። ናይጄሪያዊው ተማሪም ሀገሩ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ስራ አግኝቷል።  ትልቁ ችግር ግን ይላል የተማረው ኃይል ሲመለስ የሚገጥመው የመገልገያ መሣሪያ እጥረት ነው።«አብዛኛውን ጊዜ ወደ ሀገር በምትመለስበት ጊዜ ካቆምክበት ቀጥለህ መስራት እንዳትችል ከባድ የሚያደርገው የሚያስፈልግህ መሳሪያ ተጓድሎ መገኘት ነው። በብራዚል ወደ ቤተ ሙከራ ስገባ የተሟላ ነው። ያ  እንድታሰላስል ያደርግሀል። አስተሳሰብህን እንድትቀይር ያደርግሀል ።እና ትልቁ ችግራችን የቁሳቁሶች አለመሟላት ነው። »

Afrikanische Studenten in Deutschland Universität Aussicht auf bessere Bildungschancen (picture alliance/dpa)

የተሻለ የትምህርት እድል ለማግኘት በርካታ አፍሪቃውያን አሁንም ወደ አውሮፓ ይጓዛሉ።

ኦጉንጂሚ በብራዚል ቤተ ሙከራ  የሚጠቀምባቸው መገልገያዎች ዘመናዊ እና ከዚህ ቀደም አይቶ የማያውቃቸው ናቸው። የትምህርቱ ትኩረት በመድሀኒት ምርት እና ንጥረ ነገሮች ጥናት ላይ ነው። ትምህርቱን ሲጨርስ ወደ ሀገሩ ይመለሳል።« ካሁኑ ፈተናዎች ገጥመውኛል። ቢሆንም ተመልሼ ሄጄ ለተወሰኑ ወራትም ቢሆን የሚሆነውን አያለሁ። ነገሮች ከተሳኩ ምርምሬን ቀጥዬ ለጋሾች አፈላልግ እና እዛው እቆያለሁ። ካለበለዚያ ግን ወደ ሌላ ቦታ እሄዳለሁ።

ወጣት አፍሪቃውያን የሳይንስ ባለሙያዎች በአገሮቻቸው የሚገጥሟቸውን ችግሮች ጠንቅቀው የሚያውቁ ይመስላል።  ቪዥን ባጎንዛ የታንዛንያ ብሔራዊ የህክምና ትምህርት ቤት ውስጥ ቦታ አግኝታ ነበር። ነገር ግን ወደ ውጪ ሄዶ መማሩን መርጣለች።«ውጪ እንዴት እንደሆነ ማየት ፈለግሁ። መንደሬ ያሉ ችግሮች በህክምና ትምህርት ብቻ እንደማይፈቱ ተረድቻለሁ። ስለዚህ ከዛ ወጥቼ ስመኘው የነበረውን አገኘሁ።»

ትላለች ባጎንዛ። ዩናይትድ ስቴትስ ሚኒያፖሊስ ከሚገኘው አጉስበርግ ኮሌጅ ገና መመረቋ ነው። አንድ ቀን ወደ ሀገሯ መመለስ ትፈልጋለች። እሷ እንደምትለው የሀገሯ ችግር ግን ከተማረ የሰው ኃይል በላይ መፍትሄ ያሻል።« ወደ ሀገር ቤት መመለስ፤ ልክ ነው። ነገር ግን የሚያስፈልጉን ነገሮች ታንዛኒያ ውስጥ እስኪሟሉ እና ውጤታማ እስክንሆን ብዙ ውጣ ውረዶች አሉ። ይህም መገልገያ መሳሪያዎችን  የተማርከውን መሞከር የምትችልበት ሁኔታን ያካትታል፣የአቅም ግንባታ ያስፈልጋሉ። ተራ የሚባሉት መገልገያዎች ፣ የ PCR ማሽንን የመሳሰሉ..»የባጎንዛ ዝርዝር ረዥም ነው።  ተመላሽ የሳይንስ ባለሙያዎቹ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ የተሟሉ መገልገያ መሣሪያዎች ያስፈልጋቸዋል። 

Deutschland Ausstellung Things Fall Apart im Bayreuther Iwalewahaus (Universität Bayreuth/Iwalewahaus)

ኤርሚያስ ከበፊት አፍሪቃውያን ተማሪዎች ጋር ሲነፃጸር አሁን አሁን ብዙ ተማሪዎች ወደ ሀገራቸው እንደሚመለሱ ያምናል።

እንደ ናይጄሪያዊው ኦጉንጂሚ እና ታንዛኒያዊዋ ባጎንዛ በርካታ ኢትዮጵያንም በውጭ ሀገር የከፍተኛ ተቋም ትምህርታቸውን ይከታተላሉ። ከነዚህ መካከል በጀርመን ቦን ከተማ በሚገኘው ዮንቨርስቲ  የPHD ትምህርቷን የምትከታተለው ፅጌ ሀይሌ አንዷ ናት። እንስሳት ማራባት እና ማዳቀል ላይ ጥናት እያካሄደች ትገኛለች። ወደ ጀርመን መጥታ ትምህርት ስትከታተል አሁን ሁለተኛ ጊዜዋ ነው። ከዚህ በፊት ጀርመን ሀገር የሁለተኛ ዲግሪዋን እንደጨረሰች ወደ ኢትዮጵያ ተመልሳ ነበር። አሁንም የ PHD ትምህርቷንም ስታጠናቅቅ ወደ ኢትዮጵያ የመመለስ እቅድ አላት። እንደ ፅጌ ሌላው እዚህ ሀገር የተማረው ኤርሚያስ ሀብቴ በኮሎኝ ዩንቨርስቲ የዶክትሬት ትምህርቱን አጠናቆ ተመልሷል።

ኤርሚያስ ለስራው የሚያስፈልጉትን ነገሮች ኢትዮጵያ ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንደማያገኛቸው ያውቅ ነበር። ያ ግን ከመመለስ አልገታውም።  ኤርሚያስ ጀርመን በነበረበት ጊዜ በርካታ ለትምህርት የመጡ አፍሪቃውያንን አግኝቷል። እንደሱ የተመለሱት ግን የተወሰኑት ብቻ ናቸው። ሆኖም የመሻሻል ሁኔታ እንዳየ ገልጾልናል።

አፍሪቃውያን ተማሪዎቹ ወደ ትውልድ ሀገራቸው ይመለሱም ይቅሩ በመጨረሻ በሚኖሩበት ሀገር ያገኙትን እውቀት ለሌሎች ማካፈላቸው አይቀርም። ነገ አውሮፓም ይሁን አሜሪካ፤ እስያም ይሁን አውስትራሊያ ቢቀሩ፤ የሚኖሩባቸው ማህበረሰቦች አፍሪቃን የሚመለከቱ ርዕሰ ጉዳዮችን ይበልጥ እንዲረዱ ምሁራኑ ሚና ይኖራቸዋል።

 

ዙልፊካር አባኒ / ልደት አበበ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic