የአፍሪቃ የመጨረሻዉ ንጉሰ ነገሥት | ባህል | DW | 30.05.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

የአፍሪቃ የመጨረሻዉ ንጉሰ ነገሥት

« የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥታዊ መንግሥት ለጀርመን መንግሥት ከፍተኛ እርዳታ አድርጎ ነበር። በዝያን ግዜ እንደሚባለዉ ለጀርመን ወደ 200 ሽ ዶላር ርዳታ ኢትዮጵያ ሰታለች» ይላሉ ዶክተር አስፋዉ ወሰን አስራተ፤

ዶ/ር ልጅ አስፋዉ ወሰን አስራተ፤ የአፍሪቃና የመካከለኛዉ ምሥራቅ አማካሪ፤ በጀርመን የታወቁ ደራሲ እና የቱቢንገን ዩንቨርስቲ የክብር ሴናተር ናቸዉ። ዶ/ር ልጅ አስፋዉ ወሰን አስራተ፤ የዛሬ ሶስት ወር ግድም፤ በጀርመንኛ « ዴር ሌትዝተ ካይዘር ፎን አፍሪቃ፤ ማለትም የአፍሪቃ የመጨረሻዉ ንጉሰ ነገሥት» በሚል ስለ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ፤ 415 ገጾች ያሉት፤ ዳጎስ ያለ ታሪክ አዘል መጽሐፍን፤ ለአንባብያን አቅርበዉ፤ በጀርመን የመጽሐፍ ዓለም፤ በሶስት ወር ግዜ ዉስጥ እጅግ ብዙ ከተነበቡ መጻሕፍት መዘርዝር መካከል አንዱ ለመሆን በቅቶአል። በተለያዩ የጀርመን ከተሞች በሚገኙ፤ የተለያዩ ተቋማትና የብዙኃን መገናኛዎች፤ መጽሐፋቸዉ እንዲተርኩ እና የክብር ፊርማቸዉን እንዲያኖሩ የሚጋበዙት ዶክተር ልጅ አስፋውሰን አስራተ፤ ባለፈዉ ሳምንት መጠናቀቅያ ላይ ራድዮ ጣብያችን በሚገኝበት ቦን ከተማ በተዘጋጀላቸዉ የሥነ-ጽሑፍ ፊስቲቫል ምሽት ላይ ተገኝተዉ፤ ስለ ፃፉት መጽሐፋቸዉ እና ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ሰፊ ማብራርያ ሰጥተዉ፤ በርካቶችን አስደምመዋል፤ በዚሁ የስነ-ፅሁፍ ፊስቲቫል ላይ ተገኝተን ከዶክተር ልጅ አስፋዉ ወሰን አስራተ ጋር ዉይይት አድርገን በዛሪዉ ዝግጅታችን ይዘን ቀርበናል፤

ዶ/ር ልጅ አስፋዉ ወሰን አስራተ፤ «ሥነ-ጽሑፍ በከተማዋ በሚገኙ ቤቶች» በተሰኘዉ በቦን ከተማ በተለያዩ ግዝያት በሚዘጋጀዉ ደማቅ የስነ-ጽሑፍ ፊስቲቫል ላይ ተጋብዘዉ ሲገኙ፤ የፌደራል ጀርመን ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት የፀደቀበት፤ ሥልሳ-አምስተኛ ዓመት እየተከበረ ባለበት፤ በዚህ ዓመት እና ሕገ-መንግሥቱ ከፀደቀ ከአምስት ዓመት በኃላ እ,ጎ,አ በ1954 ዓ,ም ፌደራል ጀርመን ሪፐብሊክን፤ ለመጎብኘት በዝያ ወቅት መዲና ወደ ነበረችዉ ወደ ቦን ከተማ የተጋበዙት የመጀመርያዉ የሀገር መሬ አፄ ኃይለስላሴ፤ ከምንግዜዉም በላይ እየታወሱ ባለበት ወቅት ነዉ። የስነ-ጽሁፍ ምሽቱን ያዘጋጁት ፍሪድሪከ ሽትሪተር ይህ ሁኔታ በመግጠሙ እጅግ መገረማቸዉን በመግለፅ ነበር፤ ዶ/ር ልጅ አስፋዉ ወሰን አስራተን፤ ወደ መድረኩ የጋበዝዋቸዉ፤

የ20 ዓመት እድሜ ሳሉ በጎርጎረሳዊዉ 1968 ዓ,ም ወደ ጀርመን ሀገር እንደመጡ በመተረክ ንግግራቸዉን የጀመሩት፤ ዶ/ር ልጅ አስፋዉ ወሰን አስራተ፤ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህታቸዉን አዲስ አበባ ተከታትለዉ፤ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቅያ ፈተናን በጀርመን ሀገር ነዉ የወሰዱት፣ በኃላም፤ በጀርመን እና በብሪታንያ ኬምብሪጅ ዩንቨርስቲ፤ በታሪክ፤ በሕግ እና በኤኮኖሚ ሞያ፤ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን አጠናቀዋል። የንጉሳዊ ቤተሰብ የሆኑት ፤ዶክተር ልጅ አስፋወሰን፤ ጃንሆይ ለኢትዮጵያ ብዙ ነገሮችን እንዳደረጉ የዛኑ ያህል ደግሞ በርካታ ስህተቶችን እንደፈፀሙ በሥነ-ጽሑፍ ፊስቲቫሉ ላይ ለተገኙት ታዳሚዎች በዝርዝር አስረድተዋል። « የመጨረሻዉ የአፍሪቃ ንጉሰ ነገሥት » በሚል በጀርመንኛ ቋንቋ ስለ አፄ ኃይለ ስላሴ ታሪክ ያስቀመጡበት መጻሕፍ እንደ ርዕሱ ሁሉ፤ እዉነት ከእንግዲህ በአፍሪቃ የንጉሰ ነገሥት ሥርዓት አይመጣም ማለቶ ይሆን? ብዬ ላቀረብኩላቸዉ ጥያቄ ፤ አይደለም ነበር መልሳቸዉ፤

በወጣትነት እድሚያቸዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ያወቋት ጀርመናዊት መምህራቸዉ ቋንቋን እና ባህልን ስላስተዋወቀቻቸዉ ወደ ጀርመን በመጡ ግዜ በተለይ በመጀመርያዎቹ ቀናት እንብዛም እንዳልተደናገራቸዉ፤ ዶክተር ልጅ አስፋወሰን ለፊስቲቫሉ ታዳሚዎች ገልፀዋል። ግን አሉ የጀርመንን ቋንቋ የአኗኗር ባህልን ሳያቁ ከሚመጡ ከአፍሪቃዉያን ወንድም እና እህቶቼ ጋር ስተያይ፤ የእኔ ሁኔታ የተመቻቸ ነበር ሲሉ የገለፁት ልጅ አስፋወሰን ፤ ይህን መድረክ በመጠቀም፤ የጀርመን ህዝብ ከሁሉም በላይ ደግሞ የጀርመንን መንግሥት፤ ስደተኞች ወደ ጀርመን ከመጡ፤ ከመጀመርያዉ ቀን ጀምሮ፤ ቋንቋን እንዲያዉቁ እድል እንዲሰጣቸዉ ከልቤ ጠይቀዋል ሲሉ ተናግረዋል። የአፄ ኃይለስላሴ ለስልጣን መብቃት ብዙ ዉስብስብና ዉዝግብ እንዳለበት፤ የሰዉ ሕይወት የጠፋበት እንደሆነ ነዉ የሚነገረዉ። በሌላ በኩል በዝያን ግዜ መፍቀሪ ጀርመን ነበሩ የሚባሉት ልጅ እያሱ፤ ሰልመዋል መባላቸዉ ለአፄ ኃይለስላሴ ለስልጣን መብቃት የእንግሊዝ እና የፈረንሳይ ሚና እንዳለበት ሁሉ ይነገገራል። ዶክተር ልጅ አስፋወሰን አስራተ የአፄ ኃይለስላሴን ወደ ስልጣን መምጣት እንዴት ነዉ የሚያዩት ሌላዉ ያቀረብኩላቸዉ ጥቃቄ ነበር። እንደ አስፋወሰን ልጅ እያሱ፤ በወቅቱ ያልታወቀላቸዉ ትልቅ ባለስልጣን እንደነበሩ በዝርዝር አስረድተዋል።

የሁለተኛዉ ዓለም ጦርነት ባበቃ በዘጠነኛዉ ዓመት እና የፌደራል ጀርመን ሪፐብሊክ በተቋቋመ ልክ በአምስተኛዉ ዓመት፤ በጎርጎረሳዊዉ 1954 ወደ ጀርመን የተጋበዙት የመጀመርያዉ የሀገር መሪ፤ ንጉሰ ነገሥት አፄ ኃይለስላሴ ፤ ቦን ከተማን ሲጎበኙ እጅግ ደማቅ አቀባበል ነበር የተደረገላቸዉ ።እንደ ልጅ አስፋወሰን፤ጀርመናዉያኑ ጃንሆይን ለማስደሰት በየመንገዱ ዳር ዘንባባ እና የዝሆን ምስልን በማቆም አፍሪቃዊ ክብርን አሳይተዋቸዉ ነበር ሲሉም በፊስቲቫሉ ላይ የተገኘዉን ታዳሚ ፈገግ አሰኝተዉታል። ታድያ አፄ ኃይለስላሴ ጀርመንን በጎበኙ በ20ኛዉ ዓመት፤

በጎርጎረሳዉያኑ 1973 ዓ,ም በጀርመን ሽቱትጋርት ከተማ የነበረዉን አንድ የኢትዮጵያ ዓዉደ ርዕይ ለመክፈት እና ለሁለተኛ ግዜ ጀርመንን በጎበኙበት ግዜ በጀርመን መንግሥት ደማቅ አቀባበል ቢደረግላቸዉም፤ በዝያን ግዜ በጀርመን ከነበሩ ኢትዮጵያዉያን ተማሪዎች የገጠማቸዉ ተቃዉሞ ነበር ። «ኢንፔርያሊዝምን እንዋጋለን» «ንጉሱ ሂድና ሕዝብህን መግብ» የመሳሰሉ የተቃዉሞ በራሪ ወረቀቶችን የበተኑ ሰልፈኞች ጉብኝታቸዉን በተቃዉሞ እንዳጨፈገጉባቸዉ ዶክተር ልጅ አስፋወሰን አስራተ አልደበቁም። በዝያም ግዜ ልጅ አስፋ ወሰን አስራተ ጃንሆይን ለመጀመርያ ግዜ እንዳገኝዋቸዉም ተናግረዋል። በደርግ ሥርዓተ ማሕበርም ቢሆን፤ አፄ ኃይለስላሴ በተማረዉ ማሕበረሰብ ምንም እንዳልሰሩ ሲኮነኑ እንደነበር ይታወቃል፤ ልጅ ዶክተር አስፋዉ ወሰን በበኩላቸዉ፤ ይህ ፈፅሞ የተሳሳተ አስተሳሰብ ነዉ ሲሉ ገልፀዋል። እንድያም ሆኖ ሰዉ እንደመሆናቸዊ አፄ ኃይለስላሴ በሥልጣን ዘመነ መንግሥታቸዉ ስህተት አልሰሩም ማለት እንዳልሆነም በዝርዝር አስረድተዋል።

የመጨረሻዉ የአፍሪቃ ንጉስ » በሚል ከዶክተር ልጅ አስፋወሰን አስራቴ ለአንባብያን ባቀረቡት መጻሐፍ ላይ የጀመርነዉን ዉይይት አላበቃም፤ በሥነ-ጽሑፍ ፊስቲቫሉ ላይ የተገኙ የጀርመናዉያንንም አስተያየት አካተን የመጨረሻዉን እና ሁለተኛዉን ክፍል ዝግጅት ይዘን እንቀርባለን። እንብሩን የድምፅ ማድመጫዉን በመጫን ይከታተሉ!

አዜብ ታደሰ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic