የአፍሪቃውያን ስደተኞች ሁኔታ | አፍሪቃ | DW | 21.06.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የአፍሪቃውያን ስደተኞች ሁኔታ

ትናንት ታስቦ የዋለውን የዓለም ስደተኞች ቀን ምክንያት በማድረግ የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች መስሪያ ቤት፣ በምሕፃሩ « ዩ ኤን ኤች ሲአር» ባወጣው ዘገባ ከሁለተኛ ዓለም ጦርነት ወዲህ ትውልድ ሀገሩን ለቆ መሰደድ የተገደደው ሰው ቁጥር እንዲህ እንዳሁኑ በዝቶ እንደማያውቅ አመልክቶዋል።

ሽብር ለመሸሽ ብለው ብዙዎች ቤታቸውን እና የሚተዳደሩበትን እርሻ እየተዉ ወደ መዲናይቱ አቡጃ መሄድ ይዘዋል። ከነዚሁ መካከል ቦኮ ሀራም በየቀኑ ለማለት ይቻላል መንደሮችን ከሚያጋይበት እና ነዋሪዎቹንም ከሚገድልበት የቦርኖ ግዛት ሕይወታቸውን ለማዳወደ አቡጃ የሄዱ ባል እና ሚስት ይገኙባቸዋል።
« የሕገ ወጦች ቡድን ነው። ሁሉም ይህንን ቡድን ይፈራል። ለዚህም ነው መንደሬን ለቅቄ የሸሸሁት። አንድ ቄስ ዓይኔ እያየ ሲገድሉ ተመልክቼአለሁ። ሌሎችንም በቆንጨራ ገድለዋል። »

UNHCR Flüchtlingskommissar António Guterres


ግለሰቡ በሙስሊሙ ቤተሰባቸው ውስጥ ብቸኛው ክርስትያን ቢሆኑም፣ በመንደራቸው ለብዙ ዓመታት ካላንዳች ችግር ነበር ይኖሩ ነበር። ይሁንና፣ ቦኮ ሀራም የተባለው ፅንፈኛ ቡድን ከመጣ እና ከቡድኑ አባላት የተለየ አስተሳሰብ ያላቸውን እያደነ መግደል ከጀመረ በኋላ ሁኔታዎች መለዋወጣቸውን በማስረዳት ፣ በተለይ ወንድማቸው የዚሁ ፅንፈኛ ቡድን አባል በመሆኑ የተሰማቸውን ሀፍረት ገልጸዋል።
« ብዙዎች ቦኮ ሀራምን የተቀላቀሉት እንዳይገደሉ ስለሚፈሩ ነው። ወንድሜ ቡድኑን ከተቀላቀለ ወዲህ አላየሁትም። »
ይሁንና፣ በቦኮ ሀራም ሽብር ሰለባ የሆነው የክርስትና እምነት ተከታዩ ብቻ አይደለም። ቡድኑ እአአ ከ2009 ዓም ወዲህ በሰሜን ምሥራቃዊ ናይጀሪያ ከ 5,000 የሚበልጥ ሰው የገደለ ሲሆን ፣ ከነዚህ መካከል ብዙዎቹ ሙሥሊሞች መሆናቸውን ከሁለት ዓመት በፊት የቦኮ ሀራም ጥቃት ሰለባ ከመሆን ለጥቂት ያመለጠችው እና የትውልድ ቦታዋን ቦርኖን ለቃ ከአቡጃ በመኪና የሦስት ሰዓት መንገድ ርቃ ወደምትገኘው ካዱና መሸሽ የተገደደችው ጋዜጠኛዋ ሀፍሳት ማይና አስታውቃለች።
« ከሀይማኖት ጋ የሚያገናኘው ነገር የለም። ይህ አስከፊ የችካኔ ተግባር ነው። ሕፃናትን፣ ሴቶችን ፣ ወጣቶችን መግደል፣ ወጣት ልጃገረዶችን ማገት ፣ ሕይወታቸውን ማናጋት፣ ማንነታቸውን እንዲጠሉ ማድረግ ይህ የጨካኝ ሰው ስራ ነው። ከሀይማኖት፣ ከጎሣ ጋር የተያያዘ አይደለም። »
የናይጀሪያ የአደጋ እና አስቸኳ ሁኔታ ተመልካች መስሪያ ቤት እንዳስታወቀው፣ ከማይዱግሪ ከተማ እና አካባቢዋ በአሁኑ ጊዜ ወደ 250,000 ሰው ከቦኮ ሀራም ሽብር ለማምለጥ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሎዋል። ከ60,000 የሚበልጥ ወደ ጎረቤት ካሜሩን፣ ቻድ እና ኒዠር ሸሽቶዋል። የነዚሁ ሀገራት መንግሥታት እንደሚፈለገው ለስደተኞቹ መጠለያ ጣቢያዎች ባለማዘጋጀታቸው ስደተኞች ተልቅ ችግር ላይ እንደሚገኙ ነው የተሰማው። ለችግሩም ባፋጣኝ መፍትሔ የሚገኝለት አይመስልም። የናይጀሪያ መንግሥት ቦኮ ሀራም በሚንቀሳቀስበት አካባቢ የአስቸኳይ ጊዜ ቢያውጅም፣ እስካሁን ጦሩ በዚሁ ፅንፈኛ ቡድን አንፃር በጀመረው ዘመቻ ያስመዘገበው ውጤት በጣም ንዑስ ነው። በናይጀሪያ መንግሥት እና በቦኮ ሀራም መካከልም እስካሁን ይህ ነው የሚባል ድርድር ተካሂዶ አያውቅም። ግን፣ የናይጀሪያ መንግሥት የቦኮ ሀራምን ሽብር በሆነ መንገድ እንዲያበቃ የብዙዎች ምኞት መሆኑን ሁኔታው እንዲህ ሊቀጥል አይችልም የምትለው ጋዜጠኛዋ ሀፍሳት ማይና ገልጻለች።

አርያም ተክሌ
አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic