የአዲስ ዓመት የበዓል የሥጋ ተዋጽዖ ግብይት በአዲስ አበባ
ረቡዕ፣ መስከረም 1 2017በአዲስ አበባ ከተማ ለእርድ የሚውሉ የቁም እንስሳት እና የዶሮ ግብይት ስፍራዎችን ተዟዙረን ተመልክተናል። በጥቅሉ የዋጋ ጭማሪ በሁሉም የእርድ እንስሳት ላይ ታይቷል። የፈረንጅ የሚባለው የውጭ ዝርያ ያለው አካላዊ ግዝፈት እንጅ ጣዕሙ እንደ ሐበሻው ያልሆነው ዶሮ በስፋት ከመቅረቡ በላይ ከ 400 እስከ 500 ብር ይሸጣል። የሐበሻ የሚባለው ዶሮ ደግሞ ሰፊ አቅርቦት የለውም። ከ 900 እስከ 1500 ብርም ይሸጣል።
አንድ ኪሎ ሥጋ የመኖሪያ መንደሮች አካባቢ ከ600 ብር ጀምሮ ይሸጣል። በሌላ በኩል ስም፣ የደንበኛ ብዛት፣ የተስፋፋ ቦታ የያዙ ሥጋ፣ ቁርጥ እና ክትፎ ቤቶች በአዲስ አበባ ወቅታዊ ጥሩ የገቢ ማስገኛ የንግድ ተቋማት እየሆኑ በብዙ እየተከፈቱ ነው። የኑሮ ልዩነቱን በጉልህ የሚያንፀባርቁት እነዚህ ቤቶች እንደየ ደረጃቸው አንድ ኪሎ ግራም ሥጋን አብስለውና አዘጋጅተው እስከ 2000 እና ከዚያም በላይ ብር ድረስ ይሸጣሉ።
በሌላ በኩል የበግ፣ የፍየል እንዲሁም የበሬ አቅርቦት እንደከዚህ ቀደሙ አይደለም። በግ ከ ስድስት ሺህ እስከ 25 ሺህ ብር ይሸጣል።
የበሬ ግብይት ላይ ሰፊ የአቅርቦት ማነስ መኖሩን ማስተዋል ችለናል። ለዚህም ነው በየካ ክፍለ ከተማ ያለው ካራሎ የቁም እንስሳት የገበያ ማዕከል ያለ ከወትሮው በተለየ ተቀዛቅዞ የተስተዋለው። እንዲያም ሆኖ በሬ ከ 50 እስከ 100 ሺህ ብር ድረስ እየተገበየ ይገኛል።
እንቁላል ከ 13 እስከ 16 ብር ይሸጣል። በጥቅሉ የገበያውም ሆነ የበዓል ድባቡ ከእስከዛሬው ተቀዛቅዞ ተስተውሏል። ሰብሰብ ተብሎ ወዳጅ ዘመድ በጋራ የሚካፈለው ቅርጫም በመደብ እስከ 3 ሺህ ብር ዋጋው ጨምሯል።
የፀጥታ ሥጋት ፣ የመንገድ ላይ እገታ ሥጋቶች፣ የሰው የመግዛት አቅም መዳከም፣ የሰላም እጦት እንዲሁም የዶላር ከብር ምንዛሪ አንፃር ጭማሪ አለ በሚል ነጋዴዎች ዋጋ መጨመራቸው በበዓል ግብይቱ ላይ የዋጋ ጭማሪ አስከትሏል።
ሰለሞን ሙጩ
ልደት አበበ
ነጋሽ መሀመድ