የአውሮፓ ኅብረት ከአፍሪካ ስደት ለመቀነስ የመደበው የ5 ቢሊዮን ዩሮ ፈንድ ትችት ተሰነዘረበት
ቅዳሜ፣ መስከረም 18 2017የአውሮፓ ኅብረት ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ከአፍሪካ የሚደረገውን ፍልሰት ለመቀነስ የመደበው 5 ቢሊዮን ዩሮ ሥራ ላይ የዋለበት መንገድ በኅብረቱ የኦዲተሮች ችሎት ኃይለኛ ትችት ተሰንዝሮበታል። መቀመጫውን በሉግዘምበርግ ያደረገው የአውሮፓ የኦዲተሮች ችሎት እንዳለው ኢመርጀንሲ ትረስት ፈንድ ፎር አፍሪካ (Emergency Trust Fund for Africa) በሚል ማዕቀፍ የጸደቀው ገንዘብ እንደ ታቀደው ስደትን ለመቀነስ ከታለሙ ሥራዎች ይልቅ በተመሣሣይ ጊዜ በርካታ የተለያዩ ነገሮች ለማከናወን ለሚሞክሩ ዕቅዶች ውሏል።
ኦዲተሮቹ ገንዘቡ በልማት፣ ሰብአዊ ርዳታ እና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ ዘርፎች የተንቦረቀቁ ዕቅዶች ለመደገፍ ሥራ ላይ መዋሉን አስታውቀዋል።
የአውሮፓ ኅብረት ገንዘቡን ያዘጋጀው ከፍተኛ የፍልሰት ቀውስ በተፈጠረበት የጎርጎሮሳዊው 2015 በአፍሪካ የስደት መነሾ ለሆኑ የአለመረጋጋት፣ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት እና የመፈናቀል ችግሮች መፍትሔ ለማበጀት ነበር። ዕቅዱ ተግባራዊ የሚሆንበት ጊዜ ከመጠናቀቁ አንድ ዓመት ቀደም ብለው ኦዲተሮቹ የስደትን ዋና ዋና መንስኤዎች ለመፍታት በቂ ትኩረት አልሰጠም ሲሉ ተችተዋል።
በገንዘቡ ድጋፍ የሚደረግላቸው አብዛኛዎቹ ሥራዎች ተቀባይነት ያላቸው መሆን እንዲችሉ ዓላማዎቹ እና ቅድሚያ የተሰጣቸው ሥራዎች የተለጠጡ እንዲሆኑ ተደርጓል። ነገር ግን በሊቢያ የታደሰው የሮማውያን ቴዓትር እና በሣህል ቀጠና የሚገኝ ራዲዮ ጣቢያን ጨምሮ ድጋፍ የተደረገላቸው አንዳንዶቹ ፕሮጀክቶች ከስደት ጋር ያላቸው ግንኙነት በጣም አናሳ ሆኖ ተገኝቷል።
የገንዘቡ አመዳደብ “ወደ አውሮፓ ኅብረት የሚደርሱ መደበኛ ያልሆኑ ስደተኞች ቁጥር የመሰሉ ስደት ተኮር አመልካቾች ላይ መሠረት ያደረገ እንዳልሆነ” ኦዲተሮቹ በሪፖርቱ ይፋ አድርገዋል። የሥራ ዕድል ፈጠራ መጋነኑን እና የሰብአዊ መብቶች ሥጋቶች ሥጋቶች በአግባቡ መፍትሔ እንዳልተበጀላቸውም የሪፖርቱ ጸሀፊያን ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪ በአንዳንድ ሁኔታዎች የገቢ መጨመር ስደትን ከመግታት ይልቅ የበለጠ በማበረታታት ተቃራኒውን ውጤት የማምጣት ሥጋት መኖሩንም አትተዋል።
“ጉልህ የሆነ የገቢ ዕድገት መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመቋቋም በቀጥታ ላይመራ ይችላል” የሚለው ሰነድ “ነገር ግን ለስኬት እና የተሻለ ሕይወት ቁልፉ ስደት ነው የሚል ጠንካራ አረዳድ በመኖሩ ሳይንቀሳቀሱ የቆዩ መደበኛ ባልሆነ መንገድ የመፍለስ ዕቅዶችን ሊያበረታታ ይችላል” በማለት አደጋውን አብራርቷል።
የአውሮፓ ኦዲተሮች ችሎት አባል እና የኦዲት ሪፖርት ዝግጅቱን በኃላፊነት የመሩት ቤቲና ጃኮብሰን የስደት ጉዳይ የልማት እና የፖለቲካ ዋንኛ አጀንዳ ሆኖ እንዲዘልቅ ኢመርጀንሲ ትረስት ፈንድ ፎር አፍሪካ ቢያግዝም እጅግ ሰፊ በሆነው ትኩረቱ ረገድ ግን ያመጣው ለውጥ አናሳ እንደሆነ ተናግረዋል። ከስምንት ዓመታት ገደማ በፊት ይፋ የሆነው የኦዲት ሪፖርትም ተመሳሳይ ድምዳሜ ላይ የደረሰ ነበር።
ስደትን ለመቀነስ ተስፋ የተጣለበት ኢመርጀንሲ ትረስት ፈንድ ፎር አፍሪካ የተባለ ዕቅድ ይፋ የሆነው የሶርያ ጦርነት ተቀስቅሶ ከፍተኛ ፍልሰት ካስከተለ በኋላ ነው። ባለሙያዎች ግን እጅግ ሰፊ ጂዖግራፊያዊ አካባቢ የተካተተበት የገንዘብ አመዳደቡም በዚያም መንገድ የሆነ እንደሆነ ይተቻሉ።
ዕቅዱ በሳሕል እና የቻድ ሐይቅ ቀጠና፣ ኢትዮጵያ የምትገኝበት የአፍሪካ ቀንድ እና በሰሜን አፍሪካ የሚገኙ በርካታ ቀውሶችን ይሸፍናል። በሦስቱ ቀጠናዎች በ27 ሀገራት በ248 መርሐ-ግብሮች 933 የኮንትራት ውሎች ተፈርመዋል።
በጀርመን የልማት ኢንስቲትዩት (IDOS) ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ኒልስ ካይዘር የተፈረሙት ውሎች ዋናውን ዕቅድ ለማሳካት አስችለዋል ብሎ መናገር ይከብዳል የሚል አቋም አላቸው።
ገንዘቡ በበርካታ ፕሮጀክቶች በአራት ዋና ዋና ዘርፎች የተከፋፈለ ነው። ከፍ ላለ ኤኮኖሚያዊ እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ዕድሎች 17 በመቶ ተመድቧል። የማሕበረሰቦችን የመቋቋም አቅም ለማጠናከር 28 በመቶ፣ የስደት አስተዳደርን ለማሻሻል 31 በመቶ ለተሻለ አስተዳደር እና ግጭትን ለመከላከል ደግሞ ከገንዘቡ የተመደበው 22 በመቶ ነው።
ይሁንና በሪፖርቱ እንደሠፈረው “ከእነዚህ ዐበይት ጉዳዮች የትኛው ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ የሚያመለክት መመሪያ የለም።” በተጨማሪም የሥራ ዕድል ፈጠራ ከመጠን በላይ መጋነኑን እና በበርካታ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል የተባሉ የሥራ ዕድሎች በተጨባጭ ዘላቂ አለመሆናቸውን ሪፖርቱ ይጠቁማል።
ለምሳሌ ያክል ኦዲተሮች ኢንዱስትሪያል ፓርኮች እና የቢዝነስ መሠረተ-ልማቶችን በተመለከተ የተጋነኑ ሪፖርቶች መቅረባቸውን ደርሰውበታል። ኦዲተሮች በማሳያነት የመረመሯቸው አራት ሪፖርቶች “62 የኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ወይም የቢዝነስ መሠረተ-ልማቶች መገንባታቸውን፣ መስፋፋታቸውን ወይም መሻሻላቸውን” ይገልጻሉ። ይሁንና ሪፖርት ከተደረጉት መካከል ግማሽ ያክሉ በተጨባጭ “መኖራቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል ተጨባጭ መረጃ ማግኘት አልቻሉም።”
ኦዲተሮቹ ሌሎች ፕሮጀክቶች እና ተፈጠሩ የተባሉ የሥራ ዕድሎች ተጋነዋል ብለዋል።
ካይዘር እንደሚሉት ከዚህ ቀደም የተደረገ ግምገማ የተመደበው ገንዘብ “አማራጭ መተዳደሪያ በማስፋፋት ረገድ ያበረከተው አስተዋጽዖ መጠነኛ” እንደሆነ ተደርሶበታል። በሁለተኛ ደረጃ “ተገኘ የተባለው መጠነኛ አስተዋጽዖ መደበኛ ያልሆነ ስደትን ለመቀነስ ምን ያህል ሚና እንደተጫወተ መገምገም አስቸጋሪ ነው።”
በኢትዮጵያ የሥራ ዕድልን በማሳደግ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመከላከል የተቀረጸ ፕሮጀክት ሰዎች በብዛት በሚሰደዱባቸው አምስት አካባቢዎች የሥራ አጦችን ቁጥር በ0.32 % ብቻ መቀነስ መቻሉን ሪፖርቱ ይጠቁማል። በዕቅዱ ግን የሥራ አጦችን ቁጥር በ3.61 % ለመቀነስ ተወጥኖ ነበር።
የጀርመን የልማት ኢንስቲትዩት ባልደረባ የሆኑት ኒልስ ካይዘር የአውሮፓ ኅብረት ፈንድ ለምሳሌ ያክል አንዳንድ የኅብረቱ አባል ሀገራት በሦስተኛ ሀገሮች የድንበር ቁጥጥር ጠበቅ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን እና የሕግ አስከባሪ ተቋሞቻቸውን በገንዘብ በመደገፍ ቅድሚያ በመስጠታቸው ከጅማሮው አወዛጋቢ እንደነበር ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ በጎርጎሮሳዊው 2017 የአውሮፓ ኅብረትን የልማት ርዳታ ከጉዳዩ ጋር ማስተባበር ያስፈልጋል የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥተው ነበር።
በሊቢያ በበረታ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ምክንያት ሪፖርቱ እንደሚለው የአውሮፓ ኅብረት “በዐይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የሦስተኛ ወገን የሰብአዊ መብቶች ሥጋቶች ቁጥጥር” ተግባራዊ አድርጓል። ነገር ግን ኮሚሽኑ በአውሮፓ ኅብረት ከሚደገፉ ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዙ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ሪፖርት ለማድረግ፣ ለመመዝገብ እና ለመከታተል የሚያስል መደበኛ አሰራር አልነበረውም።
“ተፈጽመዋል የሚባሉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች በአግባቡ መፈተሻቸውን እና የአውሮፓ ኅብረት የገንዘብ ድጋፍ እንዲቀጥል ወይም እንዲቋረጥ ሲወሰን ከግምት ውስጥ መግባታቸውን የሚያሳይ ሥርዓት የለም” ሲሉ ኦዲተሮቹ ጽፈዋል።
የሰብአዊ መብቶች ተቆጣጣሪዎች በሊቢያ በእስር ላይ የሚገኙ ስደተኞች አያያዝ ለውጥ እንደሌለው ሪፖርት ቢያደርጉም ኦዲተሮቹ ግን በአውሮፓ ኅብረት ገንዘብ የተገነቡ ማናቸውም እስር ቤቶች ለመጎብኘት ፈቃድ እንዳልተሰጣቸው አስታውቀዋል።
የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመከታተል የተቋቋመው ኮሚሽን የተፈጸሙ ኩነቶች በሊቢያ የሚከናወኑ የተወሰኑ ሥራዎች እንዲቋረጡ የሚያደርጉ መሆናቸውን በኦዲት ወቅት እንደገለጸ ዝግጅቱን በኃላፊነት የመሩት ቤቲና ጃኮብሰን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ይሁንና በኅብረቱ ገንዘብ የሚከናወኑ ሥራዎች አልታጠፉም።
ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች ሳይከናወኑ የቀሩ ሥራዎች ጭምር አሉ። ለሊቢያ የባሕር ላይ የነፍስ አድን ማስተባበሪያ ማዕከል ለማቋቋም ኅብረቱ በመደበው ገንዘብ ቁሳቁስ በጎርጎሮሳዊው 2021 ቢገዛም የተባለው ድርጅት እስካሁን አልተቋቋመም።
ግጭት አባባሾችን፣ መደበኛ ላልሆነ ስደት እና መፈናቀል በመረጃ ላይ የተመሠረተ መፍትሔ ለማበጀት በተመደበው ገንዘብ ከ100 በላይ ጥናቶች ተከናውነዋል። ነገር ግን ጥናቶቹ ይፋ ሲሆኑ አብዛኛው የኢመርጀንሲ ትረስት ፈንድ ፎር አፍሪካ ገንዘብ ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ሊሰጥ ቃል ተገብቷል።
አንችል ቮራ/እሸቴ በቀለ
ታምራት ዲንሳ