1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአካባቢ ተፈጥሮ ላይ ያተኮሩ ጉባኤዎች

ማክሰኞ፣ የካቲት 19 2016

ስድስተኛው የተመድ የአካባቢ ጥበቃ ጉባኤ በናይሮቢ ኬንያ ትናንት ተጀምሯል። በርካታ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትሮች እና በሺህዎች የሚገመቱ ተሳታፊዎች የሚገኙት ይህ ጉባኤ የአየር ንብረት ለውጥ ስላስከተለው ቀውስ፤ የተፈጥሮ ይዞታ እና እየጠፋ ስላለው ብዝሃ ሕይወት ከትናንት አንስቶ እስከ ፊታችን ዓርብ ድረስ እንደሚወያይ ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/4cuhD
ፎቶ ከማኅደር፤ የአየር ብክለት በቻይና
ከባቢ አየርን የሚበክለው ከፋብሪካዎች የሚወጣው ጭስ፤ ፎቶ ከማኅደር፤ የአየር ብክለት በቻይና ምስል Xie Zhengyi/dpa/picture alliance

የአካባቢ ተፈጥሮ ላይ ያተኮሩ ጉባኤዎች

 

በየሁለት ዓመቱ የተመድ 193 አባል ሃገራት በጋራ እየተሰባሰቡ ምድራችን የተጋፈጠቻቸውን የሳሳቢ የአካባቢ ተፈጥሮ ጉዳዮችን በማንሳት ይወያያሉ። ለአምስት ቀናት የሚዘልቀው የዘንድሮው ስድስተኛው የመንግሥታቱ ድርጅት የአካባቢ ተፈጥሮ ላይ የሚያተኩረው ጉባኤ ትናንት ናይሮቢ ኬንያ ላይ ተጀምሯል።  የአየር ንብረት ለውጥ በአሁኑ ወቅት በሁሉም ሃገራት ላይ ጫናውን በግላጭ በማሳየት ላይ ነው፤ በየጊዜው የሚካሄዱት የአካባቢ ተፈጥሮን የሚመለከቱ ጉባኤዎች ምን አስገኝተው ይሆን? 

የተመድ የአካባቢ ተፈጥሮ ጉባኤ (UNEA) ምንነት

እንደ የዓለም የአካባቢ ተፈጥሮ ጉዳይ ፓርላማ የሚታየው የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ተፈጥሮ ጉባኤ፤ በእንግሊዝኛው ምህጻሩ UNEA የሚባለው አካል፤ ለአካባቢ ተፈጥሮ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ፖሊሲዎች በመወሰን፣ ለጉዳዮቹ ዓለም አቀፍ ደንብ እንዲያወጣ የተደራጀ ነው። በጎርጎሪዮሳዊው 2012 ዓ,ም ብራዚል ላይ ከተካሄደው የመንግሥታቱ ድርጅት የዘላቂ ልማት ጉባኤ የተፈጠረው ይህ መዋቅር የአካባቢ ተፈጥሮ ጉዳዮችም ሆኑ የጤና ስጋቶችን በሚመለከት የሚደረጉ ማናቸውም እንቅስቃሴዎችም ሆኑ ጥረቶች በተናጠል ሳይሆን በዘርፈ ብዙነት ትኩረት እንዲያገኙ የሚለውን ሃሳብ ማምጣቱ እንደ ስኬት ይታይለታል። በከባቢ አየርና በአካባቢ ተፈጥሮ ላይ የሚደርሰው ብክለትና በእሱ ምክንያት የሚከተለው የተፈጥሮ ምድሪቱን እንደሚያዳርስ ያመለከቱት የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንገር አንደርሰን፤ በምድር ላይ ብቻውን እንደ ደሴት ተነጥሎ መኖር እንደማይችል በማሳሰብ ለጋራ ችግር በጋራ መፍትሄ ከመፈለግ ሌላ አማራጭ የለም ነው ያሉት።

«የትም እንኑር፤ እስያ ውስጥ ብክለት ካለ በአቅራቢያው የምኖረው እኔ ብክለቱ ያገኘኛል። የብዝሃ ሕይወት ውድመት እኛጋ ከተፈጠረ በመላው ዓለም ሰዎች ላይ ጉዳት ይደርሳል። ክፉኛ የውኃ መውረጃዎቻችንን ከበከልናቸው፤ ወይም ከውቅያኖሶቻችን በገፍ ዓሣዎችን ካጠመድን፤ ወይም ደግሞ የፕላስቲክ ቆሻሻዎች ወደ ባሕር የሚጣሉ ከሆነ፤ የኬንያን የባሕር ዳርቻዎች ሊያጥለቀልቅ ይችላል፤ ቆሻሻው ግን ከኬንያ ያልወጣ ይሆናል። ዋና ነጥብ፤ እንዲህ ያሉትን ችግሮች ማቃለል የምንችለው በጋራ ስንንቀሳቀስ ነው። እናም በጋራ መነጋገር ዘርፈ ብዙነት ነው። »

ፎቶ ከማኅደር፤ የፕላስቲክ ብክለት ሰርቢያ
አሳሳቢ የሆነው የውኃ አካላትን ከጥቅም ውጭ እያደረገ የሚገኘው የፕላስቲክ መጠቀሚያዎች አወጋገድ።ፎቶ ከማኅደር፤ የፕላስቲክ ብክለት ሰርቢያምስል Darko Vojinovic/AP/picture alliance

ይህ የመንግሥታቱ ድርጅት የአካባቢ ተፈጥሮ ጉባኤ፤ በዚህ ብቻ የተወሰነም አይደለም። በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰላም ሆነ የጸጥታ ስጋቶች በጋራ መፍትሄ እንዲፈለግላቸውም የሚያመቻች መድረክ በመሆን ይንቀሳቀሳል። ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ካሳለፋቸው ውሳኔዎች መካከልም የዱር እንስሳትን ሕገወጥ ዝውውር፤ እንዲሁም ውጊያ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ለአካባቢ ተፈጥሮ ስለሚደረግ ጥበቃን የሚመለከቱት በዋናነት ይጠቀሳሉ።

የጉባኤዎች ፋይዳ

ጉባኤው በተለይም በአሁኑ ወቅት ዓለምን የሚያሳስቡ ሦስት ዓበይት ጉዳዮች ማለትም የአየር ንብረት ለውጥ፤ የብዝሀ ሕይወት ውድመት እና የአካባቢ ብክለትን በሚመለከት አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ይነጋገራል ነው የተባለው። የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ዋና ጽሕፈት ቤቱ በናይሮቢ ኬንያ ይገኛል። የዚህ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ኢንገር አንደርሰን የምናውቃትን መሬት እንዳለች ለመጠበቅ በመተባበር አስፈላጊውን እርምጃ በአፋጣኝ መውሰድ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በጉባኤው የተገኙ እናንተ አባል ሃገራት ሲደራደሩም፤ በትክክል ጉዳዩን በመመልከት የአካባቢ ተፈጥሮ ቀውስና ተግዳሮቶችን፣ አዳዲስ ተግዳሮቶችን፤ አጣዳፊ ተግዳሮቶችን፤ ሩቅ ባሉ ውቅያኖስ ላይ አሁንም ያሉ ሆኖም ግን እርምጃ ካልተወሰደ ወደ ሁሉንም አካባቢ ሊሳቡ የሚችሉ ፈተናዎችን በአግባቡ እንዲመረምሩም ጠይቀዋል።

ትናንት የናይሮቢውን ስብሰባ የከፈቱት የሞሮኮ የኃይል ሚኒስትርና የስድስተኛው የመንግሥታቱ ድርጅት የአካባቢ ተፈጥሮ ጉባኤ ፕሬዝደንት ለይላ ቤናሊ በበኩላቸው ጉባኤው ሃገራት ያስገቧቸውን 19 ረቂቅ የውሳኔ ሃሳቦች እና የአካባቢ ተፈጥሮን በተመለከተ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባ ያሏቸውን ሁለት ረቂቅ ውሳኔዎችን በማቅረብ መጀመሩን ተናግረዋል። ዓለም ከጉባኤው ውጤት እንደሚጠብቅም አመላክተዋል።

«ዛሬ በ2024 ዓ,ም ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ውጤት እንድናሳየው እየጠበቀን ነው። ይህ ዓለም አቀፉን የአካባቢ ተፈጥሮ ጉዳይ ወደፊት የምናራምድበት ወሳኝ ጊዜያችን ነው። ባለፉት አምስት ጉባኤዎች እና በየጉባኤዎቹ መካከል በተከሰቱ የተለያዩ የአካባቢ ተፈጥሮ ሂደቶች ምክንያት ቃል የተገቡ ውሳኔዎችን የምናጠናክርበት ነው።»

የጉባኤው ታዳሚዎችና አባል ሃገራት ከዚህ ቀደም በሙሉ ድምጽ ካጸደቋቸው ወሳኝ ከተባሉት ነጥቦች መካከል፤ የውኃ እጥረት፤ ማዕድናትን በጥንቃቄ ማውጣት፤ የማዕድናት አያያዝ፤ በተለይ እንደ ፎስፈረስ ያሉትን ማዕድናት ይዞታ፤ ለአየር ንብረት ስጋት የሆኑ ቴክኒዎሎጂዎች፤ እንዲሁም የአካባቢ ተፈጥሮን ለመከላከል የሚደረጉ የገንዘብ ድጋፎችን የሚመለከቱት ቀዳሚዎቹ መሆናቸውንም አመልክተዋል።  በዚህ ጉባኤ መላውን ዓለም የሚያሳስቡ የተባሉት ጉዳዮች መነጋገሪያ ይሁኑ እንጂ ሃገራት ቅድሚያ የሚሰጧቸው አጀንዳዎች እንደሚለያዩ ነው የሚገለጸው። በዚህም ምክንያት በየጉባኤው ብዙ የተደከመባቸው ውሳኔዎች የሚጠበቀውን ያህል የፖለቲካ ተዋናዮቹን ትኩረት አያገኙም ነው የሚሉት እንዲህ ባሉ በርካታ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች የሚሳተፉት የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪው ዶክተር ሚሊየን በላይ።  

በውዳቂ ፕላስኮች ናይሮቢ ኬንያ ላይ የተሠራው ቅርጽ፤ ፎቶ ከማኅደር
በውዳቂ ፕላስኮች ናይሮቢ ኬንያ ላይ የተሠራው ቅርጽ፤ ፎቶ ከማኅደርምስል Brian Inganga/AP/picture alliance

የዘንድሮው ጉባኤው ተሳታፊዎች

ስድስተኛው የተመድ የአካባቢ ተፈጥሮ ጉባኤ ከሰኞ የካቲት 18 ቀን ጀምሮ እስከ ዓርብ የካቲት 22 ቀን 2015 ዓም ድረስ በናይሮቢ ኬንያ በመካሄድ ላይ ነው። በጉባኤው ላይ የሰባት ሃገራት መሪዎችን ጨምሮ የ139 ሃገራት ሚኒስትሮች እና ምክትል ሚኒስትሮች፣ የዘርፉ ምሁራን እና ባለሙያዎች፤ የአካባቢ ተፈጥሮ ተሟጋቾች እንዲሁም የኢንዱስትሪ ተወካዮች ባጠቃላይ ወደ ስድስት ሺህ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ የተመድ የአካባቢ ተፈጥሮ ጉባኤ መረጃ ያመለክታል። የጉባኤው አዘጋጆች ለዘጋቢዎች እንደተናገሩት እንዲህ ቁጥሩ የበዛ ተሳታፊም ሆኑ ሚኒስትሮች የተገኙበት ጉባኤ ናይሮቢ ላይ ታይቶ አይታወቅም። የአካባቢ ተፈጥሮ ይዞታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለወጠ ድርቅና ጎርፍም ሆነ መሰል የተፈጥሮ ቁጣዎች እየጠነከሩ መምጣታቸው የሚያሳስባቸው ወገኖች በሚገኙባቸው በእነዚህ ጉባኤዎች በርካታ ጠቃሚ ጉዳዮች ቢነሱም ተግባራዊነታቸው መዘግየቱ የብዙዎች መነጋገሪያ ከሆነ ውሎ አድሯል።

ለከባቢ አየር መበከል ብሎም ለምድራችን ሙቀት መጨመር መንስኤ የሆኑ ሙቀት አማቂ ጋዞች የሚያመነጩ ስልቶችን ተጠቅመው ወደ ጉባኤዎቹ የሚጓዙት በሺህዎች የሚቆጠሩት ተሳታፊዎችም ለብክለቱ አስተዋጽኦ ማድረጋቸው የማይቀር ነው። ይህን የሚያሳይ መረጃ መመልከታቸውን የገለጹልን ዶክተር ሚሊየን ግኝቱ ያስከተለውን ስሜት ገልጸውልናል። በበርካታ ተመሳሳይ ጉባኤዎች ላይ የታደሙት ሌላው የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪ አቶ አየለ ከበደም ይህንኑ ሃሳብ ያጠናክራሉ።

ፎቶ ከማኅደር፤ ጭጋግ የጋረደው ቀን በታይላንድ
ለከባቢ አየር መበከል ብሎም ለምድራችን ሙቀት መጨመር መንስኤ የሆኑ ሙቀት አማቂ ጋዞች የሚያመነጩ ስልቶችን ተጠቅመው ወደ ጉባኤዎቹ የሚጓዙት በሺህዎች የሚቆጠሩት ተሳታፊዎችም ለብክለቱ አስተዋጽኦ ማድረጋቸው የማይቀር ነው። ፎቶ ከማኅደር፤ ጭጋግ የጋረደው ቀን በታይላንድ ምስል LILLIAN SUWANRUMPHA/AFP/Getty Images

እንዲህ ቢሉም ታዲያ እንዲህ ያሉ ጉባኤዎች ጭራሽ መቅረት አለባቸው ወደሚል ድምዳሜ ግን አልደረሱም። እሳቸው እንደሚሉት በመንግሥታቱ ድርጅት ስር የሚካሄዱ ስብሰባዎች አንዱ ሌላውን ይመግባል። በዚህ ሳምንቱ ጉባኤ ናይሮቢ ኬንያ ላይ የሚነሳው እና በምክረ ሃሳብነት የሚቀርቡ ነጥቦች ለመጪው የተመድ የዓለም አየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤ COP 29 አስተዋጽኦ ይኖረዋል ባይ ናቸው። አቶ አየለ ግን ለመሆኑ መቼ ነው ስለ አየር ንብረት ለውጥም ሆነ ስለ አካባቢ ተፈጥሮ ጉዳት የሚወያዩ ጉባኤዎች የሚያበቁት ብለው ይጠይቃሉ።

እሳቸው እንደገለጹን በዚህ ጉባኤ ለመሳተፍ ለሚላኩ ሰዎች ከፍተኛ ወጪ ይወጣል። ሆኖም ግን ከስብሰባው ይዘውት ስለተመለሱት ውጤት ግን ጠያቂም ሆነ ያንን ማብራሪያ እንዲሰጡ ሁኔታውን የሚያመቻች አሠራር የለም። በዚህም ምክንያት በተለያዩ ሃገራት የሚዘጋጁት ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ግለሰቦች ሀገር የሚጉበኙባቸው የመንሸራሸሪያ አጋጣሚዎች ከመሆን አልዘለሉም ባይ ናቸው። በአሁኑ ጊዜ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ያልነካው ሀገር አገኝም፤ ድርቁ፣ ከባድ ዝናብ እና ጎርፉ፤ በሙቀት ጊዜም ሰደድ እሳትና የሙቀት ማዕበል ዓለምን እያስጨነቀ ነው። ችግሩን የሚያመላክቱ ጉባኤዎች በየጊዜ ይካሄዳሉ፤ የመንግሥታት መሪዎችም በየስብሰባው ይገኛሉ፤ ሃሳብ ይሰማሉ፤ ይሰጣሉ፤ ዛሬም ግን የተወያዩበትን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ይጠየቃሉ። ስጋቱም ጨምሯል። ሃሳባቸውን ያካፈሉንን እናመሰግናለን እናንተም አስተያየታችሁን ላኩልን።

ሸዋዬ ለገሠ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ