የአቶ አንዳርጋቸው ይዞታና የሂዩመንራይትስ ዋች ጥሪ | ኢትዮጵያ | DW | 09.07.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የአቶ አንዳርጋቸው ይዞታና የሂዩመንራይትስ ዋች ጥሪ

የመን ለኢትዮጵያ መንግሥት አሳልፋ የሰጠቻቸው የግንቦት 7 የፍትህ የነፃነትና የዴሞክራሲ ፓርቲ ዋና ፀሃፊ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በኢትዮጵያ እሥር ቤት ውስጥ ይበደላሉ ብሎ እንደሚፈራ ዓለም ዓቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሂዩመን ራይትስ ዋች አስታወቀ ።

የድርጅቱ የአፍሪቃ ጉዳዮች ምክትል ሃላፊ ሚስ ሌስሊ ሌፍኮው ድርጅታቸዉ ሥለ ኢትዮጵያ የእስረኞች ይዞታ ያለዉን ልምድ ጠቅሰዉ እንዳሉት አቶ አንዳርጋቸው በኢትዮጵያ እሥር ቤት ይንገላታሉ የሚል ስጋት አለው ። ሌፍኮው የብሪታኒያ መንግሥት የአቶ አንዳርጋቸው መብት እንዲከበር አስፈላጊውን ጫና እንዲያደርግም ጠይቀዋል ። የግንቦት 7 የፍትህ የነፃነትና የዴሞክራሲ ፓርቲ ዋና ፀሃፊ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ኢትዮጵያ እስር ቤት ዉስጥ በደል-ይደርስባቸዋል ለማለት ሑዩማን ራይትስ ዋች የመጀመሪያዉ አይደለም።ሌላዉ አለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ድርጅት አምንስቲ ኢንተርናሽንልም ባወጣዉ መግለጫ ተመሳሳይ ሥጋቱን አስታዉቋል።

የሑዩማን ራይትስ ዋች የአፍሪቃ ጉዳዮች ምክትል ሃላፊ ሚስ ሌስሊ ሌፍኮው ለዶቼቬለ እንደተናገሩት ድርጅታቸው መዝግቦ በያዘው መረጃ መሠረት የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ ቀደም በእስረኞች ላይ ግፍ በመፈፀም ይታወቃል ። የአቶ አንዳርጋቸው እጣም ከዚህ የተለየ አይሆንም የሚል ስጋት አለው ።

Symbolbild Amnesty International und Human Rights Watch gegen Hinrichtung von Jugendlichen

« አይንገላቱም የሚል ተስፋ አለኝ ። ሆኖም መንግሥት በዚህ ረገድ ከዚህ ቀደም የተመዘገባበት መረጃ ጥሩ አይደለም ። ሂዩመን ራይትስ ዋችና ሌሎች ድርጅቶች መንግሥት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከባድ በደሎች እንደሚፈፅም መዝግበዋል ። እንደ አቶ አንዳርጋቸው ከባድ በሚባሉ ወንጀሎች የሚከሰሱ ሰዎች በኢትዮጵያ ፖሊስና የፀጥታ ኃይሎች የሚፈፀሙባቸውን ከባድ በደሎች መዝግበናል ። ስለዚህ እርሳቸውም ተመሳሳይ በደል ይፈፀምባቸዋል የሚል በምክንያት የተደገፈ ስጋት አለን ።

የኢትዮጵያ መንግሥት አቶ አንዳርጋቸውን መያዙን ትናንት ነው ያረጋገጠው ። መንግሥት በሚቆጣጠረዉ ቴሌቪን በሰጠው መግለጫ መሠረት አቶ አንዳርጋቸው ሰኔ 16 2006 ዓም በሰንዓ በኩል ወደ ኤርትራ ሊጓዙ ሲሉ ተይዘው በዚያኑ እለት ነው ለኢትዮጵያ ተላልፈው የተሰጡት ። ሌፍኮ የመን አቶ አንዳርጋቸውን አሳልፋ መስጠቷ ዓለም ዓቀፍ ህግን የሚፃረር እርምጃ ነው ይላሉ ።

« አቶ አንዳርጋቸው ከየመን ወደ ኢትዮጵያ ተላልፈው መሰጠታቸው ያሳስበናል ። ምክንያቱም አሳልፎ መስጠት በራሱ ህገ ወጥ ነው ። የየመን መንግሥት ፀረ ቁም ስቅል ስምምነት ፈርሟል ። ለቁም ስቅል ውይም ደግሞ ለመንገላታት አደጋ ወደ ሚጋለጡበት አገር አሳልፎ ያለመስጠት ግዴታ አለባቸው።አቶ አንዳርጋቸውን በዚህ መንገድ ለኢትዮጵያ መስጠታቸው ዓለም ዓቀፍ ግዴታዎቻቸውን በግልፅ ጥሰዋል። »

Logo von Human Rights Watch der UNO

ሌፍኮ እንደሚሉት ኢትዮጵያ የያዘቻቸውን በትውልድ ኢትዮጵዊ በዜግነት ብሪታያዊ የሆኑትን የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌን መብቶች ማክበር ይኖርባታል ።አቶ አንዳርጋቸው ከጠበቆቻቸው፤ ከቤተሰቦቻቸውና ከብሪታኒያ ኤምባሲ ባለሥልጣናት ጋር በአስቸኳይ እንዲገናኙ ማደረግ ይገባዋል ያሉት ሌፍኮ ይህ ተግባራዊ እንዲሆን የብሪታኒያ መንግሥትም ግፊት እንዲያደርግ ጠይቀዋል ።

«የብሪታኒያ መንግሥት አንዳርጋቸውን ማየት እንዲቻል ና መብታቸውም እንዲጠበቅ የሚችለውን ሁሉ ጠንካራ እርምጃ ይወስዳል ብዮ እጠብቃለሁ ። ብሪታኒያም ለማንኛውም ዜጋዋ ይህን የማድረግ ግዴታ አለባት ። አቶ አንዳርጋቸው ባልተገኙበት የፍርድ ሂደት ሞት የተበየነባቸው ሰው ናቸው ። ሰዎች በሌሉበት የሚሰጡ ብይኖች የተለየ ስጋት ያሳድራሉ ። ስለዚህ የሞት ቅጣትን በመቃወም ጠንካራ አቋም ያለው የብሪታኒያ መንግሥት ጉዳዩን በልዩ ሁኔታ ሊያሳስብና መብታቸው እንዲጠበቅም የሚችለውን ሁሉ ጫና ሊያደርግ ይገባል ።»

ሂሩት መለሰ

ነጋሽ መሃመድ

Audios and videos on the topic