የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ላኪዎች ይገጥሙናል ያሉት ተግዳሮት
ቅዳሜ፣ መጋቢት 2 2015
ሐንሳ የአበባ አምራች-ላኪ ኩባንያ ዋና መሰረቱን ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ በአቅራቢያ ቦታ በሆለታ እና መናገሻ ላይ አድርጎ አበባን በማምረት የመላክ ስራ ላይ ተሰማርቷል፡፡ በኢትዮጵያ አምስት የአበባ አምራች-ላኪ እህትማማቾች ኩባንያዎች ያሉት የውጪ ድርጅት የሆነውን አንሳን ወክለው ምርቱን የሚያስተዋውቁትን የድርጅቱ የገበያ ጥናት ተጠሪ ወ/ሮ መቅደስን የተዋወቅናቸው አዲስ አበባ ውስጥ ከየካቲት 29 እስከ መጋቢት 01 ቀን 2015 ዓ.ም. ለ3 ቀናት በተዘጋጀው የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ኤክስፖ ነው፡፡ በዚህ ኤክስፖ ላይ ከውጪ 23 ዓለማቀፍ ኩባንያዎች እንዲሁም ከ60 በላይ የአገር ውስጥ አምራች-ላኪ ድርጅቶች ታድመዋል፡፡
የዚህ ኤክስፖ ታዳሚው የሐንሳ አበባ አምራች-ላኪ ኩባንያ ተወካይ መቅደስ ድርጅታቸው በየቀኑ አበባ አምርቶ ወደ ተለያዩ የውጭ አገራት የገበያ መዳረሻዎቹ እንደሚልክ ያስረዳሉ፡፡ “አጠቃላይ ከ70 ሄክታር በላይ የአበባ እርሻ ኢትዮጵያ ውስጥ አለን፡፡ በዋናነት ሮዝ አበቦች ላይ ትኩረት አድርገን ነው ምርታችንን የምናመርተው፡፡ ለዚሁ ምርታችን ደግሞ የተለያዩ ዓለማቀፍ መዳረሻዎች እና ምርት ማቆያዎች አሉን፡፡ በአውሮፓ እና መካከለኛ ምስራቅ በተለይም ሰፊ ገቢያ አለን፡፡ በስፋትም እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ አገር ውስጥ ያለው የገቢያ አማራጭ ከወጪያችን አንጻር በቂ ትርፍ ስለማያስገኝ ሙለኩ ትኩረታችን ወደ ውጪ ገቢያ መላክ ላይ ነው” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
ይሁንና ይላሉ አስተያየት መቅደስ አበባን አምርቶ መላክ እንዲሁ የዋዛ ስራ አይደለም፡፡ በተለይም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተፈተነው የአበባ ኢንደስትሪና ገበያ አሉታዊ ነው፡፡ “በተለይም በተቀባይ አንጻር አሁን አሁን ኢንደስትሪውን ትገዳሮት እየገጠመው ነው፡፡ ገቢያችንን በተለይም ከአውሮፓ ወደ ሌሎች የመካከለኛ እና ሩቅ ምስራቅ አገራት ለመቀየር እየተገደድን ነው፡፡ በተጨማሪም ኢንደስትሪው አስቸኳይ ተደራሽነት ብፈልግም ከአውሮፕላን በረረራ መራዘምም ጋር ተያይዞ አልፎ አልፎ የሚፈጠሩብን ችግሮች ለዘርፉ ፈታኝ ነው” ብለዋል።
የማምረቻውን ቦታ ደቡብ ክልል ብላቴ አካባቢ ያደረገውን ዳኘ ዳባ የግብርና ምርት አምራች-አቅራቢን ወክለው አስተያየት የሰጡን ሌላው የዚህ ኤክስፖ ተሳታፊ አቶ ፋሲካ በበኩላቸው አይነተ ብዙ የግብርና ውጤት የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን ይዘው ቀርበዋል፡፡
አቶ ፋሲካ በኢትዮጵያ የሚስተዋለው የምርት አላላክ ቅንጅታዊ ስራ መጓደልና አልፎ አልፎ አንዳንድ ቦታዎች ላይ የሚሰሙ የሰላም እጦት ዜናዎች ለዘርፉ ፈተና ነው ባይም ናቸው፡፡ “ለአሁኑ በብዛት ምርታችን የምንልከው ወደ ጎረቤት አገራት ነው፡፡ ግን ወደ ፊት ሌሎች ዓለማቀፍ ገቢያን መዳረሻችን ማድረግ እንፈልጋለን፡፡ ለዚህ ደግሞ ምርቱ በትኩስነቱ እንዲደርስ ችግሩ ለአምራች ብቻ የሚተው ሳይሆን ቅንጅታዊ ስራን ይፈልጋል፡፡ በየቦታው ያሉ የሰላም ችግሮችን ማስተካከል ሌላው ለግብርናው ምርት ላኪዎች እጅግ አስፈላጊ የሆነ ጉዳይ ነው” ሲሉ አቶ ፋሲካ ተናግረዋል።
ለሶስት ቀናት ተካሒዶ ዓርብ የካቲት 10 ቀን 2015 ዓ.ም. የተጠናቀቀውን “ሆርቲ ፍሎራ-ኢትዮጵያ ኤክስፖ” የተባለውን አውደ ርዕይ ያሰናዳው የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራች-ላኪ ማህበር በአውደ ርዕዩ ከ90 በላይ አምራች ኩባንያዎች ምርታቸውን ይዘው መቅረባቸውን ያስረዳል፡፡ ከነዚህም ውስጥ ለአባላቶቹ የገበያ ትስስርና ምርት ልውውጥ ለመፍጠር ከውጪ ዓለማቀፍ ድርጅቶች 23 ገደማ አምራች-ላኪ ድርጅቶች መሳተፋቸው ነው የተገለፀው፡፡ ወይዘሮ የምስራች ብርሃኑ በኢትዮጵያ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራች-ላኪ ማህበር ውስጥ የተግባቦት ተጠሪ ሲሆኑ የማህበሩ አባላት ለሚያቀርቧቸው የገበያ ተደራሽነት ጥያቄ ስለ ሚሰጥ ምላሽ ጠይቀናቸዋል፡፡ “ካሉን ከ60 በላይ አባላት ኃላፊዎቻቸው ተወክለው የመመሪያ ለውጥ ሃሳብም ጭምር እያቀረቡ ከመንግስት ጋር አሉ የተባሉትን ውጣ ውረዶች ለመፍታት ትረት በማድረግ እየሰራን ነው” ብለዋል፡፡
ከአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምርቶ መላክ ኢትዮጵያ ባለፉት 18 ገደማ ኣመታት ከ4 ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ስታገኝ ባለፈው የጎርጎሳውያኑ 2022 ብቻ ደግሞ ከ600 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱንም በማህበሩ የተሰጠን ጥቆማ ያሳያል፡፡
ሥዩም ጌቱ
እሸቴ በቀለ