1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችአፍሪቃ

የአሜሪካ ባለሥልጣናት የመቐለ ጉብኝትና ውይይት

ሐሙስ፣ የካቲት 14 2016

በአሜሪካው የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ አምባሳደር ማይክል ሀመር የተመራ የልዑካን ቡድን ትናንት መቐለ ላይ ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ ህወሓት እና በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ተወያይቷል።

https://p.dw.com/p/4ckbe
መቐለ ከተማ
መቐለ ከተማምስል Million Gebresilassie/DW

የአሜሪካ ባለሥልጣናት የመቐለ ጉብኝትና ውይይት

ልዑካኑ ትናንት በመቐለ በነበራቸው ቆይታ ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች፣ ከህወሓት ሊቀመንበር እንዲሁም በትግራይ ከሚንቀሳቀሱ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መምከራቸው ተገልጿል። አምባሳደር ሀመር እና በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ በተገኙበት የመቐለው ውይይት የፕሪቶርያ ውል የእስካሁን አፈፃፀም፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጉዳይ፣ የትግራይ ወቅታዊ ሰብአዊ ሁኔታ እና ሌሎች አጀንዳዎቹም እንደነበሩ ተነግሯል። ጉብኝቱን እና ውይይቱን አስመልክቶ በመቐለ ለጋዜጠኞች ማብራርያ የሰጡት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ፥ በትግራይ ያለውን ሰብአዊ ቀውስ እንደሚገነዘቡ እና ችግሩ ለማቃለል በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ የገለፁ ሲሆን፥ የተፈናቃዮች ጉዳይም መፍትሔ የሚሻ መሆኑ አንስተዋል።

አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ «የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ወደ ቤታቸው የሚመለሱበት ሁኔታ በጉጉት ይጠብቃሉ። ያሉበት ሁኔታ ወቅታዊ ሁኔታ ለችግር ተጋላጭ የሚያደርግ እና ተቀባይነት የሌለው ነው። ከባድ መሆኑ እንረዳለን። ዛሬ እዚህ ተገኝተን የተረዳነው ምን ያክል ከባድ ሁኔታ እንዳለ ነው። ችግሮቹን ለመፍታት በጋራ እንሰራለን» ብለዋል።

ትናንት በመቐለ ተገኝተው በከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች ጨምሮ ከተለያዩ አካላት ጋር ውይይት ካደረጉ እንግዶች ውጭ በየጊዜው በርካታ የተለያዩ ሃገራት አምባሳደሮች፣ ልዩ ልዑካን፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች፣ የፌደራል መንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና ሌሎችም በትግራይ ክልል የሥራ ጉብኝት ያደርጋሉ። የከፋ የኑሮ ላይ ያሉ ዜጎችም ይመለከታሉ። ከእነዚህ ተደጋጋሚ ጉብኝቶች እና ለመፍትሔ እንሰራለን ከሚሉ ቃላት ውጭ፥ እስካሁን በተጨባጭ ተፈፃሚ የሆኑ አልያም ምላሽ ያገኙ አንገብጋቢ የትግራይ ህዝብ ጥያቄዎች አለመኖራቸውን በማንሳት የተለያዩ አካላት ትችት ያቀርባሉ። በመቐለ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስና እና ስትራቴጂካዊ ጥናቶች ትምህርት ክፍል መምህሩ ገብረ መድኅን ገብረ ሚካኤል፥ በተለይም የፕሪቶርያ ስምምነት በሙሉዕነት እንዲተገበር ጫና በመፍጠር በኩል እነዚህ አካላት የሚጠበቅባቸውን አልተወጡም ባይ ናቸው። ገብረ መድህን «ጉብኝቶቹ መሬት ላይ ጠብ የሚል ፍሬ እስካሁን አላፈሩም»ም ይላሉ። ከዚህ በተጨማሪ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት ሥራ ላይም በበቂ መጠን ምላሽ መስጠቱን በተመለከተም በዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ተዘንግቷል የሚሉ ሲሆን፥ ለዘላቂ ሰላም የሚደረግ ጥረት ከሁሉም እንደሚጠበቅም ያነሳሉ።

ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ