1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስአፍሪቃ

የአሜሪካን ፕሬዚዳንታዊ ሽልማት ያሸነፉት ኢትዮጵያዊው የሂሳብ ሊቅ 

ረቡዕ፣ መስከረም 6 2013

ኢትዮጵያዊው ዶክተር ሙላቱ ለማ በአሜሪካ ጆርጂያ ግዛት የሳቫና ስቴት ዩንቨርስቲ የሂሳብ ፕሮፈሰር ናቸው። የዘንድሮውን አሜሪካ ከፍተኛ የፕሬዚዳንታዊ ሽልማት ካሸነፉ 12 ታላላቅ ሰዎች ውስጥም አንዱ ናቸው። ፕሮፈሰር ሙላቱ ተወልደው ያደጉት በአርሲ ዞን ሳቩሬ ከተማነዉ። የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ አግኝተዋል።

https://p.dw.com/p/3iYqJ
Professor Mulatu Lemma
ምስል Privat

«ተሸላሚው ኢትዮጵያዊ የሂሳብ ሊቅ»


ኢትዮጵያዊው ዶክተር ሙላቱ ለማ በአሜሪካ ጆርጂያ ግዛት የሳቫና ስቴት ዩንቨርስቲ የሂሳብ ፕሮፈሰር ናቸው። የዘንድሮውን አሜሪካ ከፍተኛ የፕሬዚዳንታዊ ሽልማት ካሸነፉ 12 ታላላቅ ሰዎች ውስጥም አንዱ ናቸው። ፕሮፈሰር ሙላቱ ፤ሽልማቱን ማሸነፋቸው በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሰሞኑን ይፋ የተደረገ ሲሆን ፤ይህንን ከፍተኛ ክብር ያለው ሽልማት ያገኙት ላለፉት 25 ዓመታት ባስተማሩበት የሳቫና ዩንቨርሲቲ በሳይንስ ፣በሂሳብ፣ በምህንድስና በኮምፒዩተር ሳይንስ ተማሪዎችን በማገዝና በማማከር ለሂሳብ ትምህርት የተለዬ ፍላጎት እንዲያድርባቸው በማድረግና በማብቃት ላቅ ያለ ድርሻ በማበርከታቸው ነው። 
«ሽልማቱ ከተማሪዎች ጋር በመስራት ነው።በተለይ «ማይኖሪቲስ»ወደ «ማቲማቲክስ አትራክት»ለማድረግ የሚረዳ ነው።የጀመረው በ1995 ዓ/ም ነው።እኔ ደግሞ ከተማሪዎች ጋር ብዙ እሰራለሁ።ይህ ከተማሪዎች ጋር የመስራት ፀባዬ እዚህ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያም ጀምሬ የምሰራው ነው።ተማሪዎችን አበረታታለሁ ።» ካሉ በኋላ «ከተማሪዎች ጋር ምርምር እሰራለሁ።የኔ «ፐብሊኬሽን» በአጠቃላይ 122 ደርሷል ከነዚህ ውስጥ 32ቱ ከተማሪዎች ጋር ነው።ያ ተማሪዎች ወደ «ማቲማቲክስ»እንዲመጡ ያደርጋል።» 


ይህንን ለተማሪዎች የሚያደርጉትን ከፍተኛ ድጋፍ የሚያውቁ አንድ የስራ ባልደረባቸው ታዲያ መጭውን የሳይንስና የቴክኖሎጅ ህይወት የተሻለ ለማድረግ አናሳዎችን በተለይ ጥቁር አሜሪካውያንን በሳይንስና በሂሳብ ትምህርት ብቁ ለማድረግ የሚጥሩ ሙህራን በሚሳተፉበት በዚህ ውድድር እንዲመዘገቡ ያበረታቷቸዋል። 
«እና ይህንን ስለምሰራ አምና ወደ «ኖቬምበር» አካባቢ «አድቨርታይዝ»ሲደረግ እኔ ብዙም አልፈለኩም ነበር።ግን አንድ የማውቀው ሰው «ዴድ ላይኑ»አርብ ሊሆን ረቡዕ ዕለት ደውሎ ነገረኝና ከዚያ ሀሙስ ዕለት ጨርሼ «አፕላይ» አደረኩ። ከዚያ ምንም ሳልሰማ ወደ ሚያዚያ አካባቢ ደውለው ዶክተር ለማ ያንተን «አፕሊኩሽ ኮንሲደር» እያደረግን ስለሆነ ፎቶ ላክ አሉኝ።ሰኔ ላይ ደግሞ ተመርጠሃል ግን ይፋ እስክናረገው ከቤተሰብ በስተቀር ለማንም እንዳትናገር አሉኝ።ከዚያ ነሀሴ ሶስት ይፋ ተደረገ።» 

Professor Mulatu Lemma
ምስል Privat


ከዚህ በተጨማሪ ሂሳብ ከባዮሎጅ፣ ከኢንጅነሪንግና ኮምፒዩተር ሳይንስን ከመሳሰሉ የሳይንስ ትምህርቶች ጋር በማዛመድ በርካታ ጥናቶችን ሰርተዋል።ለዚህ ስራቸውም በ2010 ከሳቫና ስቴት ዩንቨርስቲ፣በ2012 ከጆርጂያ ዩንቨርሲቲ፣በ2013 በአጠቃላይ በጆርጂያ ከሚገኙ ዩንቨርሲቲዎች ፣በ2015 ደግሞ ከ36 የአሜሪካ ግዛቶች የዓመቱ ምርጥ ፕሮፌሰር ወይም«ፕሮፈሰር ኦፍ ዘ ይር»ተብለው ተሸልመዋል።በአጠቃላይ ሰሞኑን ያገኙትን ፕሬዝዳንታዊ ሽልማት ጨምሮ ባስተማሩባቸው 25 ዓመታት ስምንት ታላላቅ ሽልማቶችን አግኝተዋል። 
«ከተማሪዎች ጋር መስራት ያስደስተኛል»የሚሉት ዶክተር ሙላቱ፤ተማሪዎች የሂሳብ ትምህርትን በቀላሉ እንዲረዱትና ለትምህርቱ ፍላጎት እንዲያድርባቸው ከመደበኛዉ የማስተማር ዘዴ በዘለለ የራሳቸውን የሂሳብ ቀመር የፈጠሩ ሊቅ ናቸው።በጎርጎሪያኑ 2011 ዓ/ም «Mulatu Numbers » ወይም የሙላቱ ቁጥሮች በሚል የፈለሰፉት ይህ የሂሳብ ቀመር ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቅ ሲሆን የተለያዩ ዩንቨርሲቲዎችና ተመራማሪዎችም ለማጣቀሻና ለምርምር ስራ ይጠቀሙበታል። በኢትዮጵያም ይህንን ቀመር የሚጠቀሙ መምህራን መኖራቸውን ገልፀዋል።ያም ሆኖ ይህንን ቀመር ማግኜት ከስራና ከቤተሰብ ሀላፊነት ጋር ቀላል ባለመሆኑ ድፍን ሶስት አመታትን እንደወሰደባቸው ያስታውሳሉ። 
«ሉካስ ነምበር» የሚባል አለ።የዛሬ መቶ አመት የተፈጠረ።እና በሱ ላይ ብዙ ጥናት ሳደርግ ለምን የራሴን ቁጥር አልፈጥርም? አልኩና ጀመርኩ።ከዚያ ከባድ አልመሰለኝም ነበር ፤ግን ሶስት አመት ወሰደብኝ።» 


ፕሮፈሰር ሙላቱ ለማ ተወልደው ያደጉት በአርሲ ዞን ሳቩሬ ከተማ ሲሆን የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተወልደው ባደጉበት ከተማ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በአሰላ ከተማ ተከታትለዋል፣የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ካገኙ በኃላ በሀዋሳ እርሻ ኮሌጅ ለአምስት ዓመታት በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ለሁለት ዓመታት በመምህርነት አገልግለዋል።በጎርጎሪያኑ 1988 ለተጨማሪ ትምህርት ወደ አሜሪካ የሄዱ ሲሆን በ1993 ዓ/ም ሌላ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በ1994 ዓ/ም ደግሞ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በኦሃዮ ዩንቨርሲቲ አግኝተዋል።ዶክተር ሙላቱ በልጅነት ዕድሜያቸው ትምህርት ቤት የገቡበትንና ወደ ሂሳብ ትምህርት ያዘነበሉበትን አጋጣሚም አይረሱትም። 

Professor Mulatu Lemma
ምስል Privat


«እኔ የተወለድኩት በአርሲ ዞን ሳቩሬ የምትባል ከተማ ነው።የገበሬ ልጅ ነኝ።አባቴ ገበሬ ነው። እና ትምህርት ቤት የገባሁት በ12 አመቴ ነው።»ይሉና «እስከ አራተኛ ክፍል ትምህርቱ ከብዶኝ ነበር።አራተኛ ክፍል ጎበዝ መሆን ጀመርኩ።ሂሳብ ፍላጎቱ ያደረብኝ ሰባተኛ ክፍል ነው።ምክንያቱም ሰባተኛ ክፍል የክፍሉን ብቻ ሳይሆን የውጩን ሁሉ መስራት ጀመርኩ።መነሻው አንድ «ቴስት» ከመቶ ሃያ ዘጠኝ አገኘሁ።እና አስተማሪው በጣም ተናደደ።በዚያ በቃ ተነሳሁ።ያ መነሻዬ ያ ነው።ያ አስተማሪ ከሁለት ዓመት በኋላ ሲያስተምረኝ ፤ እኔ አምስተኛ ክፍል ያስተማርኩት ተማሪ አይደለም። ምን አመጣህ? አለኝ።ማጥናት ጀመርኩ። አልኩት። እንደዚያው ቀጠልኩ «ሀይስኩልም»ከዚያ የሂሳብ ፍቅር አደረብኝ ከዚያ ማን ያቁመኝ።»በማለት ገልፀዋል። 
ዶክተር ሙላቱ እንደሚሉት በብዙዎች ዘንድ ቁጥርን አክብዶ የማየት ሁኔታ ቢኖርም ማንኛውም ሰው ሂሳብን መማርና መረዳት ይችላል። ለዚህም መምህራን ተማሪዎቻቸውን መረዳትና እንዴት እንደሚያስተምሩ ማወቅ እንዲሁም ከነሱ ጋር የሚጣጣም ዘዴ መጠቀም አስፈላጊ ነው።ይህንን ዘዴ ተግባራዊ በማድረጋቸውም ለሳይንስ መሰረት በሆነው የሂሳብ ትምህርት በርካታ ተማሪዎቻቸውን ውጤታማ ማድረጋቸውን ገልፀዋል። 


ሳይማር ያስተማረኝን ህዝብ መርዳት እፈልጋለሁ የሚሉት ዶክተር ሙላቱ ለማ ፤የበርካታ አመት የምርምር ልምዳቸውንና ዕውቀታቸውን ለሀገራቸው ኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የማካፋልና የመስራት የወደፊት ዕቅድ አላቸው። «የወደፊት ዕቅዴ ሀገሬ ሄጀ የተለያዩ ዩንቨርሲቲዎች ማቲማቲክስና ሪሰርችን ማስፋፋት ነው።ወጣቱን መርዳት ነው።«ሙላቱ ነምበርስ»ን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ለማስተማር ነው።እኔ «ሪሰርች» ብዙ «ኤክስፔሪያንስ» አለኝ።አሁን መቶ ሃያ ሁለት «ፐብሊኬሽን» አለኝ።ያ ትልቅ ነው በጣም።እና ያን «ሸር» አድርጌ ኢትዮጵያ ሀገሬ ውስጥ ማስፋፋት አለብኝ።ይሄ ነው ትልቁ ዓላማዬ።» 


ፀሀይ ጫኔ 
አዜብ ታደሰ