1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማራ ማንነትና የወሰን ጥያቄዎች

ሰኞ፣ ሐምሌ 17 2015

"አሁን አሁን ደግሞ በህዝብ ውሳኔ መሆን አለበት የሚል ድምፀት እየሰማን ነው፣ አማራ ክልል ሲሆን ህዝበ ውሳኔ፣ ሌላው ክልል ሲሆን የመንግስት ውሳኔ፣ ሸገር ከተማን (ኦሮሚያ) ቆርሶ ሲወስድ የትኛው ህዝብ ነው የወሰነው? በደቡብ ክልል ያሉ ጥያቄዎች ሲመለሱ የአማራ ክልል ጥያቄ ዘላቂ ሰላም የማያረጋግጥበት ምክንያት ምንድን ነው? ”

https://p.dw.com/p/4UJoi
Äthiopien | Yilkal Kefale
ምስል Alemenew Mekonnen/DW

የአማራ ማንነትና የወሰን ጥያቄዎች

የአማራ ማንነትና የወሰን ጥያቄዎች ህጋዊ በሆነ መልኩ ባለመመለሳቸው የየአካባቢዎቹ ነዋሪዎች በችግር ላይ መሆናቸውን ሰሞኑን በባሕር ዳር በተካሄደው የክልሉ 6ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ተነስቷል፣የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በበኩላቸው፣ በህዝበ ውሳኔና በሌሎች አማራጮች ጭምር ችግሩ እንደሚፈታ አመልክተዋል፣ በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ያለው የሰላም መደፍረስ በድርድርና በውይይት መፈታት እንደሚገባውም የምክር ቤት አባላት አመልክተዋል፡፡ሰሞኑን በተካሔደው የአማራ ክልል 6ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ትኩረት አግኝተው ውይይት ከተደረገባቸው ጉዳዮች መካከል የአማራ ማንነትና የወሰን ጥያቄ ያለባቸው አካባቢዎች ይጠቀሳሉ፣ የገዥው ብልፅግና ፓርቲ አባል የሆኑት የምክር ቤት አባል አቶ ዮሐንስ ቧያለው የአካባቢዎቹ የአማራ ማንነትና የወሰን ጥያቄዎች ምላሽ ባለማግኘታቸው ነዋሪዎቹ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ተጠቃሚ መሆን አልቻሉም፣ ጥያቄውን ህጋዊ በሆነ መንገድ ለመመለስ ለምን ይህን ያህል ጊዜ ጠየቀ? በሪፖርትስ ለምን አልቀረበም?  ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
“የወሰንና የማንነት ጥያቄ በሪፖርቱ ይቀርባል ብየ ጠብቄ ነበር አልቀረበም፣  ብንሸሸው ብንሸሸው አይለቀንም ይከተለናል፣  የራያ፣ የወልቃይት፣ የጠገዴ፣ የጠለምትና የሌሎች የአማራ ማንነትና የወሰን ጥያቄዎች መቼ ነው የሚፈቱት? አሁን አሁን ደግሞ በህዝብ ውሳኔ መሆን አለበት የሚል ድምፀት እየሰማን ነው፣ አማራ ክልል ሲሆን ህዝበ ውሳኔ፣ ሌላው ክልል ሲሆን የመንግስት ውሳኔ፣ ሸገር ከተማን (ኦሮሚያ) ቆርሶ ሲወስድ የትኛው ህዝብ ነው የወሰነው? በደቡብ ክልል ያሉ ጥያቄዎች ሲመለሱ የአማራ ክልል ጥያቄ ዘላቂ ሰላም የማያረጋግጥበት ምክንያት ምንድን ነው? ”የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋል የአካባቢዎቹ ችግሮች ህዝበ ውሰሳኔን ጨምሮ በሌሎች አማራጮች ጭምር ሊፈታ እንደሚችል በምክር ቤት ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍጭ ሰጥተዋል፡፡“ የማንነትና የወሰን ጉዳዮች  የአማራ ክልል ህዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎች ናቸው፣ እንዚህን አካባቢዎች እንዴት በዘላቂነት ህጋዊ እናድርጋቸው፣ አንዱና ገዥ ሀሳብ ሆኖ የሚወጣው የህዝበ ውሳኔ (Referendum)  ጉዳይ ነው፣ ከዚያ ባለፈ ሁለቱ ክልሎች እርስ በእርስ ተነጋግረው ከተስማሙ ከዚያ በታችም ሊያደርጉት ይችላሉ፣ በጣም ቀላል ከሆነ ደግሞ የፌደሬሽን ምክር ቤት አጥንቶ የህዝቡን ፍላጎት በሚገልፅ አግባብ  ሊወስን ይችላል የሚልም አለ፣ ግን እንዴት ያ አካባቢ፣ ያ ህዝብ፣ ማንነቱን፣ መብቱን፣ ፍላጎቱን ያለምንም ተፅዕኖ እንዲወስን ማድረግ እንችላለን? የሚለው  የሁላችንም ጥያቄ ነው የሚሆነው፡፡”
በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች እየተከሰተ ያለውን የሰላም መደፍረስ በተመለከተ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት  ውይይት እንዲያደርግ የምክር ቤት አባላት አሳስበዋል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ቀደም ሲል ከመንግስት ጋር በጋራ በጦርነቱ የተሳተፉ ታጣቂዎች የተለያየ አማራጭ ተሰጥቷቸው ወደ ሰላማዊ ኑሮ የተመለሱ ቢሆንም በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ የህዝቦችን ሰላማዊ ኑሮ የሚያውኩ ነገሮች በመፈጠራቸው ህግ የማስከበር ስራ ተሰርቷል ብለዋል፣ የአማራ ልዩ ኃይልን መልሶ ከማደራጀት ጋር የነበረውን ችግርም ጠቅሰዋል ርዕሰ መስተዳድሩ “ለውይይት ገና ሳንደርስ ልዩ ኃይላችን ከነበረበት ካምፕ እየወጣ ያው ምን እንደተደረገ ሁላችሁም ታውቃላችሁ፣ ከአዲስ አበባ ጀምሮ ያሉ የአገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ሰዎችና ባለሀብቶች ጭምር፣ በሸዋም፣ በወሎም፣ በጎጃምም ፣ በጎንደርም እንዲያወያዩ አድርገናል፣ ከየአካባቢ የአገር ሽማግሌ በተጨማሪ ማለት ነው፣ የአማራን ህዝብ እርስ በእርሱ በማጋጨት ለማዳከም፣ ለጥቃት ለማጋለጥ የሚመጣ ትርፍ በእኔ በኩል አይታየኝም በእነርሱ በኩል ታይቷቸው ከሆነም ስህተት ነው፡፡” ብለዋል፡፡ አቶ ዮሐንስ ቧያለው እንደሚሉት ደግሞ የአማራ ክልል መንግስት ሁሉን አቀፍ ድርድር እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፤
“ ... ትጥቅ ካነሱም ትጥቅ ካላነሱም፣ ከተሰለፉ ኃሎች ጋር እደራደራለሁ ብለው እንዲነግሩን እንፈልጋለን፣ ያለምንም ጣልቃ ገብነት የአማራ ክልል መንግስት ለመደራደር ዝግጁ ነው የሚለውን በግልፅ ማስቀመጥ አለብን፣ ይህን እድል ሰጥተነው አልደራደርም በሚል ላይ እርምጃ ይወሰድ ቢባል ተገቢነት አለው፣ ካልሆነ በሸኮች፣ በእድር መሪዎች፣ በቄሶች፣ የሚደረገው ባህላዊ የእርቅ ድርድር ሁኔታ መጥፎ ነው አንልም፣ መቀጠል አለበት መሰረታዊ ችግሩን ግን አይፈታውም፡፡”
በርካታ ጉዳዮች በክልሉ ምክር ቤት የተነሱ ሲሆን ከኦሮሚያ ክልል በተለይም ከወለጋ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ከኦሮሚያ ክልል መንገስት ጋር በቅርበት እየተሰራ እንደሆነ ዶ/ር ይልቃል ለምክር ቤቱ አመልክተዋል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ታምራት ዲንሳ