1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የነዳጅ እጥረት በኦሮሚያ ክልል

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 24 2016

በኦሮሚያ ክልል ከሰሞኑ ባጋጠመው ከፍተኛ የነዳጅ እጥረት የትራንስፖርት አገልግሎቱን ስለማቃወሱ ተገለጸ ። ከክልሉ አስተያየታቸውን የሰጡ አሽከርካሪዎች እና የተሽከርካሪ ባለንብረቶች በተለይም በርካታ የትራንስፖርት ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎች የሚጠቀሙባቸው የናፍጣ እጥረት ከፍተኛ መጉላላት ስለመፍጠሩም ነው የተገለጸው፡፡

https://p.dw.com/p/4fRJK
Äthiopien Addis Abeba | Treibstoffknappheit nach schweren Regenfällen
ምስል Solomon Muchie/DW

ከፍተኛ የነዳጅ እጥረት

በኦሮሚያ ክልል ከሰሞኑ ባጋጠመው ከፍተኛ የነዳጅ እጥረት የትራንስፖርት አገልግሎቱን ስለማቃወሱ ተገለጸ ። ከክልሉ አስተያየታቸውን የሰጡ አሽከርካሪዎች እና የተሽከርካሪ ባለንብረቶች በተለይም በርካታ የትራንስፖርት ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎች የሚጠቀሙባቸው የናፍጣ እጥረት ከፍተኛ መጉላላት ስለመፍጠሩም ነው የተገለጸው፡፡ ከሰሞኑ በአዲስ አበባም የዚህ ተጽእኖ መሳያ የሆነው ከፍተኛ ቁትር ያላቸው የናፍጣ ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎች በርካታ የነዳጅ ማደያዎችን አጨናንቀውት ተስተውሏል፡፡ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ሰሞነኛውን የከፋ የነዳጅ እጥረት ችግር ከአቅርቦት ችግር ሳይሆን "ከሎጂስቲክ ችግር የተከሰተ ነው” ይላል፡፡ 

ደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ

አስተያየታቸውን ከኦሮሚያ ክልል ጅማ ከተማ የሰጡን ህይወታቸውን በአሽከርካሪነት የሚመሩ አስተያየት ሰጪ፤ በሰሞነኛው የናፍጣ እጥረት ህይወታቸው ክፉኛ መፈተኑን ያስረዳሉ፡፡ የቤንዚንም ሆነ የናፍታ እጥረቱ ካጋጠመ አንድ ወር ገደማ መሆኑን የሚያስረዱት እኚህ አስተያየት ሰጪ አንድ ጊዜ ነዳጅ ቀድቶ ለመውታት ከስደስት እስከ ሰባት ሰዓታት ተሰልፎ መጠበቅ ግድ ሆኗል ነው የሚሉት፡፡

"ነዳጅ መኖሩን አለ፡፡ ግን እጥረት ስላለው ከአንድ ወር ገደማ ወዲህ ማደያ ህደህ ለመቅዳት ብርቱ ሰልፍ ይጠብቅሃል፡፡ እንደ ጅማ ከተማ ሶስት ማደያዎች አሉ፤ ሶስቱም ሰልፍ ናቸው፡፡ በፊት ወደ ከተማው ስንገባ መኪናችን ሞልተን ነበር የምንወጣው፡፡ ለስራችንም  ቀለን ነበር፡፡ መኪና ስናከራይ ነዳጅ በቀላሉ ሞልተን የተጠቀመው ሰው ወዲያው ተካልን ነበር፡፡ አሁን ያም ነው የተፈተነው፡፡ የቤንዚንም እጥረት በተለይም ባለሶስት እግር ተሽከርካሪዎች ክፉና እንድቸገሩ አድርጓል፡፡ በሁሉም ከባድ ሰልፍ ነው ያለው” ብለዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ከሰሞኑ ባጋጠመው ከፍተኛ የነዳጅ እጥረት የትራንስፖርት አገልግሎቱን ስለማቃወሱ ተገለጸ
በኦሮሚያ ክልል ከሰሞኑ ባጋጠመው ከፍተኛ የነዳጅ እጥረት የትራንስፖርት አገልግሎቱን ስለማቃወሱ ተገለጸ ምስል Solomon Muchie/DW

ምዕራብ ኦሮሚያ

ሌላኘው ከምዕራብ ሸዋ አምቦ ከተማ አስተያየታቸው የሰጡን የተሽከርካሪ ባለንብረት ያጋጠመው የነዳጅ እጥረትስራቸውን በብርቱ መፈተኑን ገልጸዋል፡፡ ባላቸው ተሳቢ ተሽከርካሪ እየሰሩ ቤተሰባቸውን እንደሚያስተዳድሩ የሚገልጹት እኚህ ነዋሪ ከአንድ ወር ወዲህ በከፋ ሁኔታ ተከሰተ ያሉት በተለይም የናፍጣ እጥረት ስራቸውን መፈተኑን አክለው አስረድተዋል፡፡ "እንደ ኦሮሚያ የታል፤ የለም ነዳጅ፡፡ አዲስ አበባ ውስጥም በሰልፍ ነው እየተቀዳ ያለው፡፡ ወደዚህ መጥተን ሰባት ሰዓት ገደማ እየተሰለፍን ነው የንቀዳው፡፡ ለወር እየተቃረብን ነው፤ አሁን የበዛ እጥረት ያለው ናፍጣ ላይ ነው፡፡ በዚያ ላይ እንደ ወትሮ አሁን ላይ ለሊት ተንቀሳቅሰን መስራት ስለማንችል ስራችንን ፈትኗል፡፡ አሁን ኦሮሚያ ውስጥ ብዙ ቦታ ሌሊት መንቀሳቀስ ክልክል ነው፡፡ በዚህ ላይ የናፍጣ ሰልፍ ታክሎበት ስራችንን አስቸጋሪ አድርጓል” ነው ያሉት አስተያየት ሰጪው፡፡

መሰል የኦሮሚያ ክልል የነዳጅ እጥረት ጫና ከሰሞኑ ተጽእኖው በአዲስ አበባ ውስጥም በስፋት ተስተውሏል፡፡ በተለይም የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች እና የጭነት መኪናዎች በናፍጣ ሰልፍ ላይ በረጅሙ ተሰልፈው ታይተዋል፡፡

የነዳጅ እጥረትችግሩ መዲናዋ አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው አገሪቱ ተስተውሏል
የነዳጅ እጥረትችግሩ መዲናዋ አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው አገሪቱ ተስተውሏልምስል Solomon Muchie/DW

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ምላሽ

ዶይቼ ቬለ የእጥረቱን መንስኤ እና መፍትሄውን አስመልክቶ ማብራሪያ ለመጠየቅ ለኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ጥያቄውን አቅርቧል፡፡ የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለ ማሪያም ሰሞኑን የተከሰተውየነዳጅ እጥረት በአንድ አከባቢ ብቻ ሳይሆን እንደመላው አገሪቱ ነው  ይላሉ፡፡ ችግሩም የተከሰተው፤ በአቅርቦት ሳይሆን ባጋጠመው የማጓጓዣ ችግር ነው ብለዋል፡፡

"እጥረቱ የገጠመን በነዳጅ አቅርቦት ሳይሆን በሎጂስቲክ (ማጓጓዣ) ችግር ነው፡፡ ከወደብ ወስዶ ነዳጅ ወደ መሃል አገር እና ወደ ተለያዩ አከባቢዎች ለማሰራጨት ሰሞነኛው የጎርፍ ጉዳይም የተሸከርካሪዎችን ፍጥነት ገድቧል” ያሉት አቶ ታደሰ፤ በዚህ ክፍተት የተፈጠረው እጥረት ችግሩ እንዲስተዋል አድርጓል ነው ያሉት፡፡ ይህም የኢትዮጵያ የነዳጅ አቅርቦት "ከእጅ ወደ አፍ”ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተከሰተ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ምላሽ
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ምላሽምስል Seyoum Getu/DW

ችግሩ መዲናዋ አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው አገሪቱ መስተዋሉን ያነሱት አቶ ታደሰ አሁን ላይ ክፍተቶቹ እየተሞሉ ወደ ማረጋጋት እየተመጣ ነውም ብለዋል፡፡ ዛሬ ዶይቼ ቬለ የተመለከታቸው የአዲስ አበባ ነዳጅ ማደያ ማዕከላትም ከሰሞኑ መጠነኛ መረጋጋት እና አነስተኛ የተሽከርካሪዎች ሰልፍ መስተዋሉን ተገንዝበናል፡፡ 

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ