1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የነዳጅ ምርቶች ዋጋ መናር

ሥዩም ጌቱ
ረቡዕ፣ መስከረም 29 2017

“የኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋ ከጎረቤት አገራ ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ እንደሆነ ጥርጥር የለውም፡፡ ከዚህ የተነሳ በኮንትሮባንድ ሊሸሽ ይችላል፡፡ ግን ይህን መቆጣጠር የመንግስት ሚና ስለሆነ ይህ እንደ ምክንያት ባይቀርብ መልካም ነው” የምጣኔ ሐብት ባለሙያ

https://p.dw.com/p/4lZcr
Äthiopien Addis Abeba | Anstieg des Gasölpreises
ምስል Seyoum Getu/DW

የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ


በኢትዮጵያ የሁሉም የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ከትናንት ማክሰኞ ጥቅምት 28 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ጭማሪ መደረጉን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ “ጥንቃቄ በተሞላበት” ያለው የነዳጅ የችርቻሮ የመሸጫ ዋጋ ሁኔታ የህዝቡን አቅምና የአገሪቱን የኢኮኖሚ ሁኔታ ያገናዘበ የዋጋ ማስተካከያ ነው ብሏልም፡፡
የኢኮኖሚው ማሻሻያን ተከትሎ ይህ እንደሚከተል ተጠባቂ ነው ያሉት የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ግን የነዳጅ ጭማሪው በብዙ መልኩ የዋጋ ንረትና የኑሮ ጫናን ማስከተሉ አይቀሬ ነው ይላሉ፡፡
እንደ የንግድ ሚኒስቴር መረጃ በመንግስት ተነድፎ ተግባራዊ የሚደረገው የነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ማስተካከያው ሁለት መነሻ ምክንያቶች ያለው ነው፡፡ አንደኛው የአለም የነዳጅ ዋጋ በተለያዩ ምክንያቶች መዋዠቅ ሲሆን ሁለተኛው ምክንያት በቅርቡ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በተለይም የውጭ ምንዛሬ ተመን ለውጥን ተከትሎ ነው፡፡
በአዲሱ ጭማሪው መሰረት የአዲስ አበባ የነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ቤንዚን በሊትር 82.60 ብር የነበረ ሲሆን በአዲሱ ተመን ከትናንት ምሽት 12 ሰዓት ጀምሮ ወደ 91.14 ብር አሻቅቧል፡፡ በሊትር 83.74 ብር የነበረው ናፍጣም ወደ 90.28 ብር ከፍ ብሏል፡፡ 
አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ አብዱልመናን መሃመድ ይህ ተጠባቂ የነበረ ነው ይላሉ፡፡ “መንግስት ከዚህ በፊት ነዳጅን ስያስገባ የነበረው ዶላርን በ57 ብር ከባንኮች ቀጥታ እየመነዘረ ነው የነበረው፡፡ አሁን በአዲሱ የውጪ ምንዛሪ ስርዓት በእጥፍ ጨምሯልና ከዚህም በላይ ወደ ፊት መጨመሩ ግድ እንደሚሆን መገመት ቀላል ነው” ብለዋል፡፡
የመንገስት አዲስ የነዳጅ ድጎማ ስሌቱ ለቀጣይ ሶስት ወራት የሚቆይ መሆኑ የተነገረ ሲሆን በየሶስት ወሩ በሂደት እየጨመረ ለአንድ ዓመት የሚዘልቅ እንዲሆን መቀመሩም ተነግሯል፡፡ በብዛት ለየብስ ትራንስፖር አገልግሎት ወሳኝ የሆኑ የቤንዝን እና ናፍጣ ዋጋ በአሁናዊ ስሌት ተመን 177 ብር ግድም ሊደርስ እንደሚችልም ተጠቁሟል፡፡

እንደ የንግድ ሚኒስቴር መግለጫም አሁን ባለው የውጭ ምንዛሬ ተመን መነሻ ነዳጅ ከውጭ ተገዝቶና ተጓጉዞ በኢትዮጵያ ገበያ ለመሸጥ ዋጋው በሊትር 120 ብር ሊደርስ ይችላል፡፡ ሆኖም ተጠቃሚው ላይ የሚደርሰውን ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቀነስ ጥቅል ድጎማ እንዲደረግበትና አብዛኛውን ሸክም በተለይም ነጭ ናፍጣና ኬሮሲን ላይ 80 በመቶ የሚሆነውን የጭማሪ ልዩነት መንግስት የሚደጉም ሲሆን 20 በመቶ ጭማሪውን ደግሞ ተጠቃሚው ህብረተሰብ እንዲከፍል ተወስኗል፡፡ በቤንዚንና በአውሮፕላን ነዳጅ ላይ የ75 በመቶ ጨማሪ በመንግስት ጥቅል ድጎማ ተደርጎ ቀሪውን 25 በመቶ ደግሞ ተጠቃሚው እንዲሸፍን መሆኑ ተነግሯልም፡፡

የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ኑሮ ላይ የሚያስከትለው ተጽእኖ ከባድ እንደሚሆን የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች ጠቅሰዋል።
የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ኑሮ ላይ የሚያስከትለው ተጽእኖ ከባድ እንደሚሆን የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች ጠቅሰዋል።ምስል Seyoum Getu/DW

የኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋ ከጎረቤት አገራት ጋር ስነጻጸር አነስተኛ መሆኑ የነዳጅ ኮንትሮባንድ ንግድን እንዳያስከትል ጭማሪው አስፈላጊ ለመሆኑ እንደ ሌላው ምክንያት ተጠቅሷል፡፡ የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሃመድ ግን ይህ እንኳ ለጭማሪው በቂ ምክንያት አይመስልም ይላሉ፡፡ “የኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋ ከጎረቤት አገራ ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ እንደሆነ ጥርጥር የለውም፡፡ ከዚህ የተነሳ በኮንትሮባንድ ሊሸሽ ይችላል፡፡ ግን ይህን መቆጣጠር የመንግስት ሚና ስለሆነ ይህ እንደ ምክንያት ባይቀርብ መልካም ነው” ያሉት ባለሙያው የዓለማቀፍ የነዳጅ ዋጋ መናርና የብር ዋጋ ከዶላር አንጻር መዳከም ለጭማሪው ምክንያታዊ መሆን እንደሚችሉ ግን ጠቁመዋል፡፡
የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ኑሮ ላይ የሚያስከትለው ተጽእኖ
ባለሙያው አክለውም፤ “የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው በ10 በመቶ ገደማ ሲስተዋል ሌላው መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ከዚያም በላቀ ልጨም እንደምችሉ መገመት ይቻላል” በመላት መንግስት ከግሉም ዘርፍ በከፋ በራሱ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ያደረገው የዋጋ ጭማሪ ኑሮን ሊያከብዱ እንደሚችሉ ገምተዋል፡፡ 
በነዳጅ ላይ የተደረገውን የዋጋ ጭማሪ ተከትሎ በትራንስፖርት አገልግሎት ክፍያ ላይ  “አግባብነት ያለው” የተባለው የታሪፍ ጭማሪ እንደሚደረግም ነው የተገለጸው፡፡ የናፍጣን ዋጋ ከሌላው በበለጠ መደጎም ያስፈለገውም በትራንስፖርት ወጪ መናር ምክንያት የሚፈጠረውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር ታስቦ ነው ተብሏል፡፡ የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አገር አቋራጭ እና የከተማ አውቶቦሶች እስካሁን የሚጠቀሙት ድጎማ እንደተጠበቀ ሆኖ በዚህ ስትራቴጂም ተጠቃሚነታቸው እንደሚቀጥልም ነው የተጠቆመው፡፡
ይህ የነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ማስተካከያ ስትራቴጂ ዓለማቀፍ የገበያ ዋጋ ሁኔታ እና በነዳጅ አምራች ሀገሮች ያለዉ ያለመረጋጋት በዚሁ ከቀጠለ የነዳጅ ውጤቶች የችርቻሮ መሸጫ  ለአንድ ዓመት ሊቆይ እንደሚችልና ለድጎማው መንግስትን እስከ 300 ቢሊዮን ብር እንደሚያስወጣ ተነስቷል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ኂሩት መለሰ