የኃይለኞቹ ፍጥጫ፣የየመኖች እልቂት | ዓለም | DW | 20.05.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የኃይለኞቹ ፍጥጫ፣የየመኖች እልቂት

የሪያድ ገዢዎች ዋሽግተኖችን ለማስደሰት በኢራንና በኢራን ይደገፋሉ በሚባሉ መንግሥታትና ቡድናት ላይ ቁጣ፣ዛቻ፣ፉከራቸዉን ሲያሰሙ፣ እንዳዴም ጡንቻቸዉን ሲሰነዝሩ ያሁኑ በርግጥ የመጀመሪያቸዉ ዓይደለም።ከ1980ዎቹ የሊባኖስ ጦርነት እስከ ኢራቅ-ኢራን ዉጊያ፣ ከኢራቁ ወረራ እስከ ሶሪያዉ ፍጅት ሁሌም ዋሽግተኖች ሲያስነጥሱ ሪያዶች እንዳሳሉ ነዉ

አውዲዮውን ያዳምጡ። 14:21

መካከለኛዉ ምሥራቅ ሌላ ፍጥጫ

የቀድሞዉ የሶቭየት ሕብረት ጠንካራ መሪ ጆሴፍ ስታሊን «የዉጪ ጉዳይ ሚንስትሩ የሠላም  ጉባኤ ካልተደረገ ሞቼ እገኛለሁ እያለ ከተከራከረ፣ መከላከያ ሚንስትሩ ለዉጊያ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠርጥር ዓይነት አባባል ነበራቸዉ አሉ።አሜሪካኖች ኢራንን ሊያጠፉ ያቅራራሉ።ሳዑዲዎች በኢራን ላይ ይዝታሉ።ኢራኖች የዋሽግተን-ሪያድ ጠላቶቻቸዉን አሳፍረዉ ሊመልሱ ይፎክራሉ።ደግሞ በተቃራኒዉ የሶስቱም መንግሥታት ባለሥልጣናት «ጦርነት አንፈልግም» ይላሉ።የመኖች ግን ሰዓት በሰዓት ያልቃሉ።የመናዊቱ ጋዜጠኛ አፍራሕ ናስር «ወላጆቼን ብትጠይቅ አለችዉ ለጠየቃት ጋዜጠኛ በቀደም «አሜሪካ፣ ሳዑዲ አረቢያም ሆነች ኢራን ለኛ ሕይወት ደንታ የላቸዉም ይሉኃል» አለችዉ ጠያቂዉ እንደፃፈዉ።

የኢራኑ ላዕላይ መሪ አያቶላሕ ዓሊ ኻማኒ የካቲት 17፣ 2017 ዘመኑ (በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር የጦር ሠራዊት አዛዦቻቸዉን ሠብስበዉ «ይሕን አዲሱን ፕሬዝደንት በዉነቱ ማመስገን አለብን» አሉ-ከወር በፊት ሥልጣን ያያዙትን የአሜሪካን ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕን ማለታቸዉ ነዉ።«እና መሰግነዋለን፣ ምክንያቱም የዩናይትድ ስቴትስን ትክክለኛ ገፅታ በቀላሉ እንድናዉቅ አድርገዋልና።»

በርግጥም የዲፕሎማሲ ጥበብ፣የፖለቲከኛ ብልጣብልጥነት፤ ሐገር-ሕዝብን የማስተዳደር ዘዴ ብዙም የማይገባቸዉ ቱጃሩ ፖለቲከኛ ያሻቸዉን የሚሉ-የሚያደርጉም ናቸዉ።ሰዉዬዉ ከተፈጥሮ ጥበቃ ዉል እስከ ንግድ ሥምምነት፣ ከወታደራዊ ትብብር እስከ ስደተኞች ደንብ የሚደርሱ ዓለም አቀፍ ሥምምቶችንና መርሆችን እየመነቃቀሩ ዉድቅ አድርገዋል።

የኢራን የኑክሌር መርሐ ግብርን ለማስቆም የተደረገዉን ዓለም አቀፍ ሥምምነትንም እንደሚያፈርሱ፣ በስምምነቱ ምክንያት ዩናይትድ ስቴትስ ከኢራን ላይ አንስታዉ የነበረዉን ማዕቀብ መልሰዉ እንደሚጥሉ ከምረጡኝ ዘመቻቸዉ ጊዜ ጀምሮ በግልፅ ያልተናገሩበት ጊዜ አልነበረም።የአሜሪካ ሕዝብ በሰጡት ቃል፣ ተስፋ አምኗቸዉ፣ ደግፏቸዉ ከሌሎች ብዙ ብጤዎቻቸዉ አብልጦ መረጣቸዉ።የተፈጥሮ ጥበቃ ይሁን የንግድ፣የኑክሌር ይባል የስደተኛ ዉል ወይም ስምምነት ዓለም አቀፍ ከሆነ ማክበርና ማስከበር

ያለበት ድፍን ዓለም ነዉ።ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ዘመቻቸዉ ለሕዝባቸዉ የገቡትን ቃል ተራ-በተራ ገቢር ሲያደርጉ የብራስልስ-ለንደን፣ የሞስኮ-ቤጂንግ ኃያላን የፈረሙትን ሥምምነት ሊያስከብሩ ቀርቶ ዉልፊጥም አላሉም።

ቱጃሩ ፖለቲከኛ ዓለም አቀፍ ሥምምነትን፣ ደንብና መርሕን እየጣሱ፣ እየሻሩ ወይም እያፈረሱ በሌሎች ሐገራት ሸቀጦች ላይ ግብር እየጨመሩ ዓለምን የማርበድበዳቸዉን ያክል ሰሜን ኮሪያን በ «እቶንና መዓት ለመቅጣት የዛቱ የፎከሩት በርግጥ ከዛቻ አላለፈም።

ድርድሩም «ትንሹ የሮኬት ሰዉ» እያሉ ከሰደቧቸዉ ከሰሜን ኮሪያዉ ሊቀመንንበር ኪሞ ጆንግ ኡን ጋር ከመጨባበጥ ያለፈ የተከረዉ የለም።ሰሞኑን ደግሞ የትራምፕ እና የባለስልጣኖቻቸዉ ስድብ፣ዛቻ፣ ፉከራ በኢራን ላይ ጠንክሯል።ደግሞ መለስ ብለዉ ጦርነት አልፈልግም ይላሉ።

«ኑክሌር ጦር መሳሪያ እንዲኖራቸዉ አልፈልግም።እና እኛን ማስጋትም የለባቸዉም።ይኸ ሁሉ ነገር እየተደረገ ቢሆንም እኔ ጦርነት መዋጋት የምፈልግ ሰዉ አይደለሁም።»

ይበሉ እንጂ፣ መስተዳድራቸዉ ኢራንን የሚወጋ ተጨማሪ አሜሪካ ወታደር፣ ተዋጊ አዉሮፕላኖች፣ ፀረ-ሚሳዬል ሚሳዬሎች እና አዉሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ወደ ፋርስ ባሕለሰላጤ እያዘመተ ነዉ።መካከለኛዉ

ምሥራቅ፣ አፍሪቃ፣ቀይ ባሕርና ሜድትራኒያን ባሕር የሠፈሩ ወታደሮች የዉጊያ ልምምድ አድርገዋል።

ለኢራን በሚጎራበቱ ኢራቅን በመሳሰሉ ሐገራት የሚኖሩ የዩናይትድ ስቴትስ ሲቢል ዜጎችን ከያሉበት አስወጥቷልም።ጦርነት የማይፈልጉት ትራምፕ በሚወዱት የትዊተር ገፃቸዉ ትናንት «ኢራን መዋጋት ከፈለገች ያ በይፋ መጥፊዋ ነዉ---» ብለዋል። የአያቶላሕ ኻሚኒ ምፅት ትክክል ትክክል ይሆን?

 

ዩናይትድ ስቴትስ ከኢራን ጋር ዉጊያ ከገጠመች ዉጊያ የምትገጥመዉ ድፍን ኢራንን ለማጥፋት እንጂ በዲፕሎማሲ፣ፖለቲካዉ ወግ ለመሸፋፈን እንደሚደረገዉ የቴሕራን ገዢዎችን ብቻ ለማጥፋት አይደለም።ኢራቃዊዉ የፖለቲካ ተንታኝ ዋቲቅ አል ሐሺሚ እንደሚያምኑት ዩናይትድ ስቴትስና ወይም ዩናይትድ ስቴትስ፣እስራኤል፣ ሳዑዲ አረቢያ፣የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችና ተከታዮቻቸዉ ኢራንን በቀጥታ አይወጉ ይሆናል።ይሁንና ዩናይትድ ስቴትስ 3 ነገሮች እስኪሟሉላት ድረስ አሜሪካና ተከታዮችዋ ኢራንን በጦር ኃይል ማስፈራራታቸዉ አይቀርም።

«ዩናይትድ ስቴትስ 3 ዓላማዎችዋ እስኪሳኩላት ድረስ ዉጥረቱን ማባባስዋን ትቀጥላለች።የመጀመሪያዉ በኢራን ላይ የዉስጥ ተቃዉሞና አመፅን መቀስቀስ ነዉ።ሁለተኛዉ፤ኢራን የመን፣ሊባኖስ፣ ሶሪያና በሌሎች የመካከለኛዉ ምሥራቅ ሐገራት ዉስጥ ያላት ተፅዕኖ እንዲቀንስ ማድረግ፣ ሶስተኛዉና ዋናዉ ዓላማ  ዩናይትድ ስቴትስ የምትፈልገዉን ኢራን ተቀብላ ሥለ ኢራን የኑክሌር መርሐ-ግብር የሚደረገዉ ድርድር እንዲቀጥል ማስገደድ ነዉ።»

ዋሽግተኖች ሲጠሯቸዉ አቤት፣ ሲልኳቸዉ ወዴትን የተካኑበት የሪያድና የአቡዳቢ ገዢዎች ኢራንን ለማዳከም የመን ላይ የከፈቱት ጦርነት ጥንታዊቱን

ደሐ-አረባዊት ሐገርን ከማጥፋት ባለፍ አሸናፊም ተሸናፊም ሳይለይ ለአምስተኛ ዓመት ቀጥሏል።የጦርነቱ መዘዝ ለሳዑዲ አረቢያ ሕዝብ ተርፎ የሪያድ፣የጂዳ፣ የጣኢፍ ሰማይ የሚሳዬልና የድሮን መወናጨፊያ ሆኗል።የህዝቡም ሥጋት ንሯል።ዛሬም ጭምር።የጂዳዉ ወኪላችን ነብዩ ሲራክ እንደነገረን ዛሬ የየመን ሁቲ አማፂያን ተኮሱት የተባለ ሚሳዬልን የሳዑዲ አረቢያ ጦር አክሽፏል።

                                            

የሪያድ ገዢዎች ዋሽግተኖችን ለማስደሰት በኢራንና በኢራን ይደገፋሉ በሚባሉ መንግሥታትና ቡድናት ላይ ቁጣ፣ዛቻ፣ፉከራቸዉን ሲያሰሙ፣ እንዳዴም ጡንቻቸዉን ሲሰነዝሩ ያሁኑ በርግጥ የመጀመሪያቸዉ ዓይደለም።ከ1980ዎቹ የሊባኖስ ጦርነት እስከ ኢራቅ-ኢራን ዉጊያ፣ ከኢራቁ ወረራ እስከ ሶሪያዉ ፍጅት ሁሌም ዋሽግተኖች ሲያስነጥሱ ሪያዶች እንዳሳሉ ነዉ።ለነገሩ ሕዝባቸዉን ረግጠዉ እየገዙ የሚደላቀቁበት ሥልጣን መሠረቱ የዋሽግተኖች ድጋፍ በመሆኑ ዋሽግተኖች ሲያዳልጣቸዉ ሪያዶች ቢደፉ በርግጥ አይገርምም።ፕሬዝደንት ትራምፕም አልሸሸጉትም።

«ሳዑዲ አረቢያን ከጥቃት እንከላከላለን።ሐብታም ናቸዉ።ንጉሱን እወዳቸዋለሁ።ንጉስ ሰልማንን።ግን ንጉስ ሆይ አልኳቸዉ እኛ ባንጠብቅዎት ሁለት ሳምንት እንኳን አይኖሩም።ለወታደራዊ (ድጋፋችን) መክፈል አለብዎት።»

የትራምፕ መስተዳድር

ከኢራን የሚሰነዘር «ጥቃትን» ለመከላከል ላለዉ ዘመቻ ጦሩን ወደ መካከለኛዉ ምሥራቅ ሲያዘምት፣ የሪያድ ገዢዎች «የሺዓ ደፈጣ ተዋጊዎች» ያሏቸዉን ቢያንስ ስምንት ዜጎቻቸዉን ጭዳ አድርገዋል።

ባለፈዉ ሳምንት በነዳጅ ማመላለሻ ቧምቧና መርከብ ላይ ደረሰ ለተባለዉ ጥቃትም የቁጣ-በቀላቸዉ ማብረጃ ያደረጉት ወትሮም የወደመችዉን የመንን በተለይ ደግሞ ርዕሠ-ከተማ ሰነዓን ነዉ።የሳዑዲ አረቢያ የጦር ጄቶች ባለፈዉ አርብ ዳዓይሩ በተባለዉ የሰነዓ መንደር ላይ በዘረገፉት ቦምብ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች ገድለዋል።የሁቲ መንግስት የሠብአዊ መብት ሚንስትር አሊያ አል-ሾአቢ እንዳሉት የሳዑዲ አረቢያ ገዢዎች ሕፃናትን ካልገደሉ ወንጀላቸዉ የተጓደለ ይመስላቸዋል።

 

«ወንጀለኞቹ 76 ሰዎችን ገድለዋል፤አቁስለዋልም።አራቱ ሕፃናት ናቸዉ።ሳዑዲ አረቢያ የየመን ሕፃናትን ካልገደለች ወንጀልዋ የጎደለባት ይመስላታል።»የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚለዉ አምስተኛ ዓመቱን በያዘዉ የየመን ጦርነት ከ7,300 በላይ ልጆች ተገድለዋል፣1,2 ሚሊዮን ልጆች አንድም ቆስለዋል አለያም ታመዋል።2,5 ሚሊዮን በምግብ እጥረት ይሰቃያሉ።

ዩናይትድ ስቴትስ፣ ሳዑዲ አረቢያም ሆነች  ኢራን አንዳቸዉ ሌላቸዉን ለማጥፋት ሲዛዛቱ የመን ትወድማለች።ሕዝቧ ያልቃል።ጋዜጠኛ አፍራሕ ናስር እንዳለችዉ ለየመን  ሕዝብ ባጠቃላይ ለሕፃናቱ ሕይወት በተለይ የሚጨነቅ የለም።

ጦርነቱ ከነዳጅ ዘይት ሽያጭ የሚዛቀዉን የሳዑዲ አረቢያ፣የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶችና የተከታዮቻቸዉን ካዝናም እያራቆተዉ ነዉ።የጦርነቱ ዘዋሪዎች በደኸዉ የየመን ሕዝብ ላይ የሚያደርሱትን እልቂትም ሆነ ከየሕዝባቸዉ ቀምተዉ እሳት ዉስጥ የሚሞጅሩት ገንዘብ ሥላደረሰና ስለሚያደርሰዉ ኪሳራ ለየሕዝባቸዉ አይገልፁም።

                                      

ንጉስ ሠልማን የአረብ ሊግ አባል ሐገራት መሪዎችን ለግንቦት 30 መካሕ ላሕ ጉባኤ ጠርተዋል።ጉባኤዉን የጠሩት የሊጉ

አባል የሆነችዉ የመን ከጥፋት የምትድንበትን ብልሐት ጉባኤተኞቹ እንዲያፈላልጉ ለመጠየቅ አይደለም።በጦርነቱ የቆሰለ፣የተፈናቀለና ለረሐብ የተጋለጠዉን ሕዝብ አባል ሐገራት እንዲረዱ ለማስተባበር አይለም።

ጉባኤተኞች ኢራንን አዉግዘዉ፣ ቀጠርን ወቅሰዉ ሪያድን አሞግሰዉ ዑሙራቸዉን አድርሰዉ ወደየመጡበት ለመመለስ መሆኑን ለማወቅ እስከ ጉባኤዉን መግለጫ መጠበቅ አያስፈልግም።«ለየመኖች የሚጨነቅ የለም» አለች ጋዜጠኛዋ።

የሳዑዲ አረቢያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ደ ኤታ አድል አል-ጁቤይር ባለፈዉ ቅዳሜ እንዳሉት ሳዑዲ አረቢያ ጦርነት አትፈልግም። ጦርነትን ለማስወገድ አቅሟ የፈቀደዉን ሁሉ ታደርጋለች።» የመኖችን የሚፈጀዉ ለሪያዶች ሠርግ-ይሆን? ወይስ እንደጋዜጠኛዋ ለየመን ሕዝብ የሚጨነቅ የለም እንበል። ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ተስፋአለም ወልደየስ 

 

 

 

 

 

 

Audios and videos on the topic