1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትግራይ ጊዚያዊ መንግስት ምሥረታ

ሐሙስ፣ መጋቢት 14 2015

በህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ውሳኔ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደርን አቶ ጌታቸው ረዳ እንደሚመሩት የተናገሩት የህወሓቱ ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስትም ለአቶ ጌታቸው ሹመቱ ስለመስጠቱ ዛሬ ይፋ አድርጓል። ህወሐት ከአሸባሪነት መዝገብ መሰረዙ የግዚያዊ አስተዳደሩ ስራ ለማስጀመር ምቹ ሁኔታ የፈጠረ መሆኑ ተገልጧል።

https://p.dw.com/p/4P8ZF
Äthiopien Konflikt in Tigray | Debretsion Gebremichael
ምስል Tiksa Negeri/REUTERS

የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ምስረታ ሒደት

የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደርን ለመመስረት የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች በሙሉ መሟላታቸዉን የእስካሁኑ የክልሉ ገዢ ፓርቲ  የህወሓት ሊቀመንበር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል አስታወቁ። ዶክተር ደብረፅዮን በሰጡት ጋztጣዊ መግለጫ ህወሐት ከአሸባሪነት መዝገብ መሰረዙ ጊዚያዊ አስተዳደሩን ስራ ለማስጀመር በጣም ጠቃሚ ነዉ።እስረኞችን ሥለማስፈታት፣  ክስ ስለማንሳትና ስለመሳሰሉት ጉዳይም ፓርቲያቸዉ ከፌዴራሉ መንግስት ጋር እየተነጋገረ መሆኑን ሊቀመንበሩ አስታዉቀዋል።

በወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ መግለጫ የሰጡት የህወሓቱ ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል፥ በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት በትግራይ ለሚቋቋመው ግዚያዊ አስተዳደር ሙሉ ዝግጅት ተደርጎ ለፌደራል መንግስት ለውሳኔ መቅረቡ እና በቅርቡ ግዚያዊ አስተዳደሩ ወደ ስራ ሊገባ እንደሚጠበቅ ገልፀዋል። የህወሓቱ ሊቀመንበር በመግለጫው በትግራይ የሚቋቋመው ግዚያዊ አስተዳደር ህወሓትና ባይቶና ጨምሮ የተለያዩ የተደራጁ ሀይሎች እንደሚሳተፉበት የተናገሩ ሲሆን፣ የግዚያዊ አስተዳደሩ የማደራጀት ሂደት ከፌዴራሉ መንግስት ጋር በምክክር የተፈፀመ ስለመሆኑ አስታውቀዋል። ዶክተር ደብረፅዮን ""በትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ስራ አስፈፃሚ ከትግራይ የፓለቲካ ፓርቲዎች ህወሓት እና ባይቶና፣ የትግራይ ሰራዊት፣ የትግራይ ምሁራን ተሳታፊ ይሆናሉ። ስለዚህ በኛ በኩል በግዚያዊ አስተዳደሩ መሳተፍ ያለባቸው አባላት ሙሉበሙሉ ጨርሰን ለማእከላዊ መንግስት አሳውቀናል" ብለዋል።

Äthiopien Debretsion Gebremichael, TPLF
ምስል REUTERS

በህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ውሳኔ መሰረት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር አቶ ጌታቸው ረዳ እንደሚመሩት የተናገሩት የህወሓቱ ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል፣ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስትም ለአቶ ጌታቸው ይህ ሹመት ስለመስጠቱ ዛሬ ይፋ አድርጓል። ህወሐት ከአሸባሪነት መዝገብ መሰረዙ ግዚያዊ አስተዳደሩ ስራ ለማስጀመር ምቹ ሁኔታ የፈጠረ መሆኑ ያነሱት ዶክተር ደብረፅዮን በበጀት፣ በእስረኞች መፈታት እና ክስ ማንሳት ዙርያም ከፌዴራሉ መንግስት ጋር ንግግር ስለመጀመራቸው ጠቁመዋል። የህወሓቱ ሊቀመንበር ""ህወሓት ከአሸባሪነት መዝገብ ተሰርዟል። ስለሆነም ግዚያዊ አስተዳደሩ ስራ የሚጀምርበት ሁኔታ ተሟልቷል። የበጀት ማዘጋጀት፣ ከእስረኞች ጋር እንዲሁም ክስ ከማንሳት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ከፌዴራል መንግስት ጋር ግንኙነት ተጀምሯል" ሲሉ አክለዋል።

Äthiopien | Treffen Getachew Reda, Olusegun Obasanjo und Debretsion Gebremichael
ምስል Privat

ግዚያዊ አስተዳደሩ በማቋቋም ሂደት እና እየታዩ ያሉ ለውጦች ዙርያ የጠየቅናቸው በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የሕግና ስነ መንግስት ኮሌጅ መምህሩ አፅብሃ ተኽለ፣ ከቅርብ ቀናት ወዲህ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የማቋቋም ስራ መፋጠን ያደነቁ ቢሆንም ሌሎች አስጊ ያልዎቸው ጉዳዮችም አንስተዋል። አቶ አፅብሃ እንደሚሉት "አቶ ጌታቸው ረዳ በዶክተር አብይ ሹመት እንደተሰጡ ነው እየተነገረ ያለው በፌደራሉ መንግስት። ዶክተር ደብረፅዮን እንደሚሉት ደግሞ ህወሓት ነው የሾማቸው። ሽምያ አለ። እልህ የሚመስል አለ" የሚሉ ሲሆን "አሿሿሙ ሲታይ ደግሞ ልክ 2013 ዓመተምህረት ላይ እንደሆነው ዓይነት ነው" በማለት ትግራይ ላይ ምስለኔ የማስቀመጥ የሚመስል ትርጉም እንዳይሰጥ ያሰጋል ሲሉ ሙሁሩ ይገልፃሉ። 
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከዚህ በፊት ከግዚያዊ አስተዳደሩ ተሳትፎ ራሱ አግልሎ የነበረው ተቃዋሚው ፓርቲ ባይቶና፥ አሁን ላይ በግዚያዊ አስተዳደሩ እንደሚሳተፍ በዶክተር ደብረፅዮን ይፋ ተደርጓል። በዚህ ጉዳይ ዙርያ ማብራሪያ ለመስጠት ነው ተብሎ ዛሬ በባይቶና ፅሕፈት ቤት ተጠርቶ የነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ጋዜጠኞች ከተገኙ በኃላ በፓርቲው አመራሮች መካከል በተነሳ ውዝግብ መግለጫው ሳይሰጥ ቀርቷል።

ሚሊዮን ኃይለስላሴ 

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ