1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚአፍሪቃ

የትግራይ ክልል ነጋዴዎች ለመንቀሳቀስ መቸገራቸውን ገለጡ

ሐሙስ፣ መጋቢት 12 2016

ትግራይ ክልልን ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል በሚያገናኙ የአስፋልት መንገዶች የተለያዩ ችግሮች እየገጠሟቸው መሆኑ ሹፌሮች እና ነጋዴዎች ይገልፃሉ። በመንገዶች ደህንነት እና ሌሎች ጦርነቱ የፈጠራቸው ችግሮች ምክንያት ለኪሳራ እንደተዳረጉም በትግራይ ክልል የሚገኙ ነጋዴዎች ያነሳሉ ።

https://p.dw.com/p/4dyy4
የትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቐለ ። ፎቶ፦ ከክምችት ማኅደር
የትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቐለ ። ፎቶ፦ ከክምችት ማኅደርምስል Million Haileselassie/DW

የትግራይ ነጋዴዎች የመንገዶቹ ደህንነት የተጠበቀ አይደለም አሉ

ትግራይ ክልልን ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል በሚያገናኙ የአስፋልት መንገዶች የተለያዩ ችግሮች እየገጠሟቸው መሆኑ ሹፌሮች እና ነጋዴዎች ይገልፃሉ። በመንገዶች ደህንነት እና ሌሎች ጦርነቱ የፈጠራቸው ችግሮች ምክንያት ለኪሳራ እንደተዳረጉም በትግራይ የሚገኙ ነጋዴዎች ያነሳሉ ። 

በጦርነቱ ወቅት ሙሉ በሙሉ ተዘግተው የነበሩ ትግራይ ክልልን ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል የሚያገናኙ አውራ ጎዳናዎች፥ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በከፊል ለንግድ ጨምሮ ለተለያዩ አገልግሎቶች ቢከፈቱም፤ አሁንም የመንገዶቹ ደህንነት የተጠበቀ ባለመሆኑ የተለያዩ ችግሮች እየገጠሟቸው መሆኑ በጎዳናዎቹ የሚንቀሳቀሱ ሹፌሮች እና ነጋዴዎች ያነሳሉ። 
ከመቐለ ተነስተው በአማራ እና አፋር ክልል በኩል ወደ ማሀል ሀገር ለሥራ የሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎች እና ሹፌሮች እንደሚሉት ከደህንነት አንፃር የተሻሉ በተባሉ መንገዶች እንኳን መንገድ መዝጋት፣ ዝርፍያ፣ ገንዘብ አስገድዶ መቀበል እና የተለያዩ ጥቃቶች የየዕለቱ ክስተት መሆኑ ይገልፃሉ። ብዙ ግዜ ከአዲስአበባ መቐለ እንዲሁም ከመቐለ አዲስአበባ የተለያዩ ሸቀጦች ጭኖ የሚመላለሰው ያነጋገርነው ለድህንነቱ ሲባል ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ የአይሱዙ ሹፌር፥ በመንገዱ በተደጋጋሚ የንብረት ዝርፍያ፣ ገንዘብ መቀማት እና አካላዊ ድብደባ ጭምር እንደደረሰው ይናገራል። ለእነዚህ ሀገር አቋራጭ መንገዶች የሚደረግ ጥበቃ ለመኖሩ ተከትሎ የሚደረጉ የንግድ ይሁኑ ማሕበራዊ እንቅስቃሴዎች አስጊ ሆነው መቀጠላቸው ሹፌሩ ጨምሮ ይገልፃል። 

"ለምሳሌ ከመቐለ ወደ አላማጣ፥ ከዛ ወደ ወልድያ በሚወስድ መንገድ በኩል ባለመገንጠያ ወደ አፋር እንገባለን። ብዙ ጊዜ በዚህኛው መንገድ ነው የምንሄደው። ይሁንና ከመገንጠያው እስከ ሚለ ያለው መንገድ እጅግ በጣም የከፋው ነው። በየመንገዱ መኪና እያስቆሙ የሚዘርፉ በርካታ ናቸው። ገንዘብ ካልከፈልክ አታልፍም የሚሉ በየቦታው አሉ። መንገድ ይዘጋሉ፣ በጣም አስቸጋሪ ነው። በየቦታው እየተዘረፍክ፣ ገንዘብ እየከፈልክ ነው የምታልፈው" ይላል ሹፌሩ። 

የትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቐለ
የትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቐለ ። ፎቶ፦ ከክምችት ማኅደርምስል Million Hailesilassie/DW

ተመሳሳይ አስተያየት በተለያዩ አቅጣጫዎች ከትግራይ ወደ ተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች እየተጓዙ ከሚሰሩ ሹፌሮች ይሰጣሉ። ከጦርነቱ በኋላ  በትግራይ እና የተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል መካከል የነበረው የንግድ እንቅስቃሴ ዳግም ቢመለስም፥ የመንገዶች ድህንነት ግን አሳሳቢ ሆኖ መቀጠሉ የትግራይ ንግድና ዘርፍ ማሕበራት ይገልፃል። ይህን ችግር ለመቅረፍ የትግራይ ንግድና ዘርፍ ማሕበራት ከአፋር እና አማራ ክልል አቻ ማሕበራት ጀምሮ ከተለያዩ አካላት እና ከሌሎች ክልሎች ጋር ግንኙነት ለመፍጠር እንዲሁም የንግድ መስመሩ ድህንነት ለማረጋገጥ ጥረት ላይ መሆኑ የትግራይ ንግድ እና ዘርፍ ማሕበራት ምክርቤት ፕሬዝደንት አሰፋ ገብረስላሴ ይገልፃሉ።

"የግንኙነት ፎረም እየፈጠርን ነው። ለምሳሌ በቅርቡ በመቐለ የሚመለከታቸው የንግዱና የመንግስት አካላት ከተለያዩ ክልሎች ጠርተን ውይይት አድርገናል" ያሉት አቶ አሰፋ ገብረስላሴ፥ በሌላ በኩል ደግሞ የንግድና ዘርፍ ማሕበራቱ ልኡክ ወደ አፋር ክልል ተጉዞ ያሉ ችግሮች በሚፈቱበት ሁኔታ ከሚመለከታቸው ጋር መምከሩ አንስተዋል። 

የፕሪቶሪያ ስምምነት በትግራይ ጦርነቱ እንዲቆም ቢያስችልም ነጋዴዎች በአውራ ጎዳናዎች ላይ በሚደርስባቸው መጉላላት መቸገራቸውን ይናገራሉ
በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ፊርማ ላይ የተገኙት የደቡብ አፍሪቃ የዓለም አቀፍ ግንኙነትና ትብብር ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር የኢትዮጵያ መንግስት ተወካይ አቶ ሬድዋን ሁሴን፤ የኬንያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኡኹሩ ኬንያታ፤ የናይጀሪያ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ፤ የሕወሓት ተወካይ ጌታቸው ረዳ፤ እንዲሁም የደቡብ አፍሪቃ የቀድሞ ምክትል ፕሬዝዳንት ፉምዚለ ሚላምቦ ኩካምስል PHILL MAGAKOE/AFP

በዚህና ሌሎች ምክንያቶች ችግር ላይ መሆናቸው የሚያነሱ በትግራይ ክልል የሚገኙ ነጋዴዎች፥ ሁሉም የግልና መንግስት ባንኮች ደግሞ ለወሰዱት ብድር የጦርነቱ ጊዜ ወለድ ጨምረው እንዲከፍሏቸው መጠየቃቸው ተከትሎ ስራቸው አደጋ ላይ መሆኑ ይገልፃሉ። ባለፈው ሳምንት ከትግራይ ከተወከሉ የተለያዩ የማሕበረሰብ ክፍሎች ጋር ተወያይተው የነበሩ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አሕመድ በክልሉ ከሚገኙ ነጋዴዎች በተለይም ከባንክ ወለድ ጋር በተያያዘ ለቀረበ ቅሬታ፥ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እንደሚታይ መናገራቸው ይታወሳል።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ታምራት ዲንሳ