1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቱርክ አካባቢያዊ ምርጫ ውጤት አንድምታ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 24 2016

በቱርክ አካባቢያዊ ምርጫ ኢክረም ኤማሞግሉ የሚመሩት ተቃዋሚ ፓርቲ በትልልቆቹ የኢስታንቡል እና አንካራ ከተሞች አሸንፏል። ውጤቱ ለፕሬዝደንት ረቺብ ጠይብ ኤርዶኻን እና ፓርቲያቸው ትልቅ ሽንፈት ነው። ኤርዶኻን በተወለዱባት እና በከንቲባነት በመሯት ኢስታንቡል ፓርቲያቸው እንዲያሸንፍ የምርጫ ዘመቻውን መርተው የነበረ ቢሆንም ሳይሳካላቸው ቀርቷል።

https://p.dw.com/p/4eMeC
የቱርክ አካባቢያዊ ምርጫ
በቱርክ አካባቢያዊ ምርጫ ተቃዋሚ ፓርቲ በኢስታንቡል እና አንካራ ከተሞች አሸንፏልምስል Ali Unal/AP Photo/picture alliance

የቱርክ አካባቢያዊ ምርጫ ውጤት አንድምታ

ባለፈው ዕሁድ በቱርክ በተደረገው የአካባቢ ምርጫ የተቃዋሚው ፓርቲ ድል ቀንቶታል። ለበርካታ አመታት በስልጣን ላይ የቆየው የፕሬዝደንት ረቺብ ጠይብ ኤርዶኻን ፓርቲ ባልተጠበቀ ሁኔታ ክፉኛ ተሸንፏል። ምርጫው የማዘጋጃ ቤት እና የአካባቢ ምርጫ ይሁን እንጂ ውጤቱ በአገሪቱ ውስጣዊ ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በውጭ ፖሊሲም ተጽዕኖ ሊፈጥር፣ ከአውሮፓ እና ኔቶ ጋር ባላት ግንኑነት ላይም ትልቅ ትርጉም ሊኖረው እንደሚችል ይገመታል።

በቱርክ የተደረገው የአካባቢያዊ ርጫ በብዙዎቹ አገሮች እና በራሷ በቱርክ ከሚካሄዱ የፕሬዝዳንታዊ እና የፓርላማ ምርጫዎች ከፍተኛ ውድድር የታየበትና ህዝብ በብዛት የተሳተፈበት፣ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብም በንቃት የተከታተለው ነው። በውጤቱ ተቃዋሚው የሪፑብሊካን ህዝባዊ ፓርቲ ማሸነፉ ሲገለጽ በመላ ቱርክ በተለይም በንግድና ቢዝነስ ማእከሏ ኢስታንቡል የተለየ ስሜት ነበር የተስተዋለው። 

ኢስታንቡል በቱርክ ፖለቲካ ወሳኝ ከተማ!

በቱርክ ምርጫ እና የፖለቲካ ትግል ዋና የመፋለሚያ ሜዳ እንደሆነች በሚነገርላት ኢስታንቡል ዳግም አሸናፊ ከንቲባ ሆነው የተመረጡት የተቃዋሚው የሪፑብሊካን ህዝባዊ ፓርቲ በእንግሊዝኛ ምህጻሩ (CHP) ፓርቲ ቁልፍ ሰው ኤክረም ኢማሞግሉ ባደረጉት ንግግር ውጤቱ የቱርክን ፖለቲካ ለመቀየር ያሚያስችል እንደሆነ ተናግረዋል። “አገር እና ተቋም በህዝብ እንጂ ባንድ ግለሰብ አይታዘዙም። ከዛሬ ጀምሮ የአንድ ሰው ፈላጭ ቆራጭነት አብቅቷል። ህዝባዊ አስተዳደር እና ዴሞክራሲ ከዛሬ ጀምሮ በሙሉ ፍጥነታቸው ወደፊት እየገስገሱ ነው” ብለዋል።

የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ዉሳኔ

ከቱርክ ህዝብ 16 ሚሊዮኑ የሚኖርባት ኢስታንቡል  ትልቋ የንግድ እና የወደብ ከተማ በቱርክ ፖለቲካ ወሳኝ ሚና እንዳላት ነው የሚታመነው። ብዙዎቹ የተሳካላቸው የቱርክ ፖለቲከኞችም ሆኑ ባለሀብቶች  ከኢስታንቡል እንደተገኙ የሚነገር ሲሆን፤ ፕሬዝዳንት ኢርዶጋንም የዚችው ከተማ ፍሬና ከንቲባም እንድነበሩ ይታወቃል።

ኢክረም ኢማሞግሉ
የኢስታንቡል ከንቲባ እና የተቃዋሚ መሪ የሆኑት ኢክረም ኢማሞግሉ እንደ ፕሬዝደንት ረቺብ ጠይብ ኤርዶኻን ተተኪ መታየት ጀምረዋል።ምስል OZAN KOSE/AFP

ከኢስታንቡል የተነሳ እና የተመረጠም ለላቀ አገራዊ ሀላፊነት ብቁ ሊሆን እንደሚችል ስለሚታመን፤ በቤይኮዝ ዩንቨርስቲ የፖለቲክ ሳይንስ ፕሮፈሰር የሆኑ ዶክተር አልሙት ካሲም ሀን እንደሚሉት ኢማምግሉም በኢስታንቡል ማሸነፋቸው ለሌላ ኃላፊነት መታጨታቸውን ያመላክታል።

“ኢስታንቡል ላይ ያሽነፈ ለየትኛም ያገሪቱ ከፍተኛ ስልጣን ተመራጭ  ተወዳዳሪ ነው የሚሆነው። በሚስተር ኢማሞግሉ አንጻር በኢስታንቡል ያገኙት ድል  በጎርጎሪሳዊው 2028 በቱርክ ለሚደረገው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ  እንዲቀርቡ  ትኬት የሚስጥ ነው” በማለት ፕሬዝዳንት ኤርዶጋንን ሊገዳደሩና ሊተኩ የሚችሉት እሳቸው እንደሆኑም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን ፓርቲያቸው መሽነፉን ተቀብለዋል

ፕሬዝዳንት ኤርዶጋንም የፖለቲካ መነሻቸውን እና ያደጉባትን ከተማ የፖለቲካ ጠቀሜታ በሚገባ ስለሚይውቁ በተለይ ከተማዋን በሳቸው ፓርቲ ተወዳደሪዎች እንድትያዝ ለማድረግ በምርጫ ዘመቻው በቀጥታ እንደተሳተፉ ነው የተስተውለው። የምርጫ ውጤቱ ሲታወቅ ግን ፕሬዝዳንት ኦርዶጋን ሸንፈታቸውን ቀድመው በመቀበል የህዝቡን ድምጽ እንደሚያከብሩ ነበር ያሳወቁት።

“የዛሬው ዕለት  የፍጻሜ ቀን አይደለም።  እንደውም ሁኔታዎችን በሚገባ እንድንመረምር እና ራሳችንን እንድፈትሽ የሚያደርግ ነው። የቱርክ ህዝብ በዚህ ምርጫ ለኛ ለፖለቲከኞች መልክት አስተላለፏል” በማለት ውጤቱን በጸጋ መቀበልቸውን የሚገልጽ ንግግር ማድረጋቸው በብዙዎች አምባገነነ ቀመስ መሪ ናቸው በማለት በሚተቿቸው ሁሉ ጭምር አድናቆት ሳይቸራቸው አልቀረም።

የኤርዶኻን ድልና የወደፊቱ ጉዟቸው

የምርጫው ውጤት አሸናፊ የሆኑትን ተቃዋሚዎች  ያስፈነደቀውን ያህል ለፕሬዝዳንት ኤርዶጋን፣ለገዥው ፓርቲ አባላት እና ደጋፊዎች በተለይ ኢስታንቡልን ማጣታቸው ትልቅ ሽንፈት እንደሆነ ነው የሚነገረው። በኢስታንቡል የሴብንሲ ዩንቨርስቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ሴኔም አይዲን በዕሁዱ ምርጫ በኢስታንቡል የተገኘው ድል የከንቲባ ኢማሞግሉ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ተቃዋሚዎች ድል እንደሆነ ነው የተናገሩት

የቱርክ ፕሬዝደንት ረቺብ ጠይብ ኤርዶኻን እና ባለቤታቸው
ኤርዶኻን በተወለዱባት እና በከንቲባነት በመሯት ኢስታንቡል ፓርቲያቸው እንዲያሸንፍ የምርጫ ዘመቻውን መርተው የነበረ ቢሆንም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ምስል Emin Sansar/Anadolu/picture alliance

“ይህ ውጤት እና የተገኘው ትልቅ ድል የኢማሞግሉ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ተቃዋሚዎች ነው ማለት እንችላለን። ውጤቱም በገዥው ፓርቲ ደጋፊዎች ብቻ ሳይሆን በሌሎች  የኩርድ ኮሚኒቲዎች፤ የግራ ፖለቲከኞች  በመሳሰሉት የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ጭምር የተገኘ ነው” በማለት ውጤቱም በኢስታንቡል ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የቱርክ ፖለቲካ ተጽኖ እንደሚኖረው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የምርጫው ዋና አጀንዳና የድሉ ምክንያቶች

ከአንድ አመት በፊት በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ እና ፓርላሜንታዊ ምርጫ ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን እና ፓርቲያቸው  አሸንፈው ሳለ፤ ብዙም ሳይቆይ ባሁኑ  ምርጭ የተለየ ውጤት መገኘቱ አነጋጋሪ  እንደሆነ ነው።  ሆኖም ግን ዋናው የፕሬዝዳንት ኤርዶጋን ሽንፈት የኢኮኖሚው ሁኔታ መባባሱ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። ዶክተር ሴኔን አይዲን ይህንኑ ህሳብ በማጠናከር ዋናው የምርጫው ቁልፍ አጀንዳ ኢክኖሚው እንደሆነ ነው የገለጹት፤

“ዋናው ጉዳይ ኤኮኖሚው ነው። ችግሩ ካለፉት ጥቂት አመታት ጀምሮ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን ህዝቡ ከሚችለው በላይ ሳይሆንበት አልቀረም” በማለት በአካባቢ ምርጫዎች መራጮች የሚያተኩሩት ፊት ለፊት ባሉት ተጨባጭ ችግሮች ላይ እንደሆነ አክለው አስረድተዋል።
ምርጫውን የከታተለችው የፈረንሳይ 24 ጋዜጠኛ ሌኢላ ጃኪኖ በበኩሏ፤ ተቃዋሚው የፕሬዝዳንት ኤርዶጋንን ፓርቲ በዚህ ያህል ልዩነት ሊያሸንፍ የቻለባቸውን ሶስት ምክንያቶች ትጠቅሳለች።

የአንካራ ከተማ ከንቲባ ማንሱር ያቫስ
ማንሱር ያቫስ በድጋሚ የአንካራ ከተማ ከንቲባ ሆነው ተመርጠዋልምስል Ali Unal/AP/picture alliance

“አንደኛ በአካባቢ ምርጫዎች ህዝቡ ድምጹን የሚሰጠው ችግሮቹን መሰረት አድርጎ ሲሆን በዚህ ምርጫም ኢኮኖሚ ዋናው ነው። ሁለተኛ፤ ለውድድር የሚቀርቡ እጩዎች ሰብእና እና ብቃትም ሌላው ምክንያት  ሲሆን፤ በዚህ በኩል የተቃዋሚው ፓርቲ የተሻሉ ተወዳዳሪዎችን አቅርቧል። ሶስተኛ ትንንሽ ፓርቲዎች በዚህ ምርጫ ከትልልቆቹ ሳይጣመሩ ለግላቸው ነው የተወዳደሩት” በማለት ይህም በተለይ የገዥውን ፓርቲ ሳይጎዳው እንዳልቀረ ግምታቸውን  አስቀምጠዋል።

ምርጫው በሥርዓት የተደራጀ እና የተመራ መሆኑን የአውሮፓ ካውንስል የምርጫ ታዛቢ ቡድን አስታዉቋልል። የምርጫ ታዛቢው ቡድን መሪ ዴቪድ ኤሬይ የምርጫው ዕለት ሰላም የሰፈነበት እና በደምብ የተደራጀ ነበር። መራጮችም  በከፍተኛ ቁጥር በመውጣት የተሳተፉበት መሆኑን ገልጸዋል።

የምርጫው ውጤት በአገሪቱ የውጭ ፖሊሲ ላይ ለውጥ ያመጣ ይሆን?

ይህ የቱርክን ፖለቲካ ሊለውጥ ይችላል ተብሎ የሚጠበቀው ውጤት፤ በቱርክ የውጭ ፖሊሲ ላይም በሂደት ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ይገመታል። ቱርክ የአውሮፓ ህብረት ዕጩ አባል ስትሆን በሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ ደግሞ ሁነኛ ቦታ እንዳላት ነው የሚታወቀው።

ሆኖም ግን ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን ሁልጊዜ  ከሸሪኮቻቸው ጋር የማይሂዱ እና አንዳንዴም ከነሱ የተለየ የውጭ ፓሊሲ በማራመድ የሚታወቁ ናቸው። ሩሲያ በዩክሬን የከፈተችውን ጦርነት ተከትሎ በሩሲያ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ባለመተርጎም ይታወቃሉ።

በቱርክ አካባቢያዊ ምርጫ የተሰጡ ድምጾች ሲዘረገፉ ይታያል
የአውሮፓ ምርጫ ታዛቢዎች ሒደቱ በደምብ የተደራጀ እና ሰላም የሰፈነበት እንደነበር መስክረዋል። ምስል Emrah Gurel/AP/dpa/picture alliance

ሀገራቸው ቱርክ ከዩክሬንም ጋር ጥሩ ግንኑነት በመፍጠር የአደራዳሪነት ሚና ስትጫወት ነው የቆየችው። ከአውሮፓ ህብረት ጋርም በመካለኛው ምስራቅ፣ ሊቢያ፤ ቆጵሮስ እና የስደተኞች ጉዳይ ብዙ ልዩነት እንዳላት ነው የሚታውቀው።

የሶማሊያ እና የቱርክ ስምምነት አንድምታዎች

ሆኖም ግን ባላት ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ እና ጉልበትም ጭምር፤ የምዕራቡ አለም ሊያርቃት እንደማይፈልግ ደግሞ ግልጽ ነው። በዚህም ምክንያት በቱርክ የበለጠ የምዕራቡ አለም አፍቃሪ መንግስት ፍላጎት ቢኖርም  አሁን አሸናፊ የሆነው ፓርቲም ግን በተለይ በዩክሬን እና ሩሲያ ውዝግብ ላይ  ብዙም የተለየ ፖሊሲ ማራመዱን የፖለቲካ ተንታኞች ይጠራጠራሉ።

ኢዲኤኤም (EDAM) የተሰኘ በኢስታንቡል የሚገኝ መንግስታዊ ያሆነ ድርጅት የደህንነት እና የመከላከያ ጉዳዮች ተንታኝ “ቱርክ ከዩክሬን ጋር ጥሩ ግኝነት ነው ያላት። ከሩሲያ ጋርም አብራ ትሰራለች።

የኔቶ አባል ሆና ሌሎቹ አባል አገሮች የሌላቸው የስራ ግንኙነት ነው ያላት” በማለት የምርጫው ውጤት ምንም ይሁን ምን ቱርክ የገልተኛ እና አደራዳሪ ቦታዋን ይዛ እንደምትቀጥል ነው ሲናገሩ የተሰሙት። በመሆኑም ከዚህ በኋላም ቱርክ በዋናነት በውስጥ ፖለቲካዋ እና ኤኮኖሚዋ ካልሆነ በስተቀር፤ በአካባቢ እና ዓለም አቀፋዊ ፖሊሲዎቿ ብዙም ለውጥ እንደማታደርግ ነው ብዙዎች የሚ ገምቱት።


ገበያው ንጉሴ

እሸቴ በቀለ