የተፈጥሮ ደንና የቡና ትስስር | ጤና እና አካባቢ | DW | 28.01.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

የተፈጥሮ ደንና የቡና ትስስር

ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚበቅለዉ የጫካ ቡና ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ማደጉ በዓለም ቡና ጠጭዎች ዘንድ ተወዳጅነት ማትረፉ ይነገርለታል።

የቡናዉ አምራቾች ከዓለም የቡና ገበያ የልፋታቸዉን ተገቢ ዋጋ እንዲያገኙ የሚደረገዉ ጥረት በቂ ባይባልም ተጠናክሮ ቢቀጥል የተሻለ ዉጤት ማየት እንደሚቻል በቅርቡ በጅማ ዞን የተፈጥሮ ደንን በመጠበቅ የቡናዉን ጥራት ከፍ ለማድረግ የሚካሄደዉን ጥረት የቃኘዉ የዶቼ ቬለ ተባባሪ ዘጋቢ ጀምስ ጄፈሪ በላከዉ ዘገባ ዘርዝሯል። ቡና ፈላጊዉ ዓለም በተለይ በተፈጥሮ መንገድ ለሚያድገዉ የጫካ ቡና የሰጠዉ ትኩረት የኢትዮጵያን ደን ከዉድመት ይታደገዉ ይሆን?

በዓለማችን የጫካ ወይም ወፍ ዘራሽ ቡናን የሚያመርቱ ሃገራት ሶስት ብቻ ናቸዉ። ኢትዮጵያ፣ ብራዚል እና የመን። ከእነዚህ ሃገራት አንዷ ደግሞ በሀገር በቀል የተፈጥሮ ደን ዉስጥ ይህን ቡናዋን በማብቀል ትታወቃለች። ይህችዉም ቡናን በዉድ ዋጋ ለጠጪዎች ማቅረቡን የሚያዉቅበት ዓለም በኩራት ጠቀም ባለ ገንዘብ የሚቸበችበዉ አረቢካ የተሰኘዉ ቡና መገኛ ምድር ኢትዮጵያ ናት።

Japan Äthiopien Kaffee Projekt

ተወዳጁን ቡና ያቀፈዉ ደን

ይሄ ሁሉ ዝናና ታሪክ ግን ተፈላጊዉን የጫካ ቡና ለሚያመርቱት የጅማዉ በለጠ ገራ የተፈጥሮ ደን የኢትዮጵያ ቡና አምራቾች የእዉቅናዉን ያህል ብዙም ጥቅም እንዳላስገኘላቸዉ አካባቢዉን ጎብኝቶ የሚመለከታቸዉን ያነጋገረዉ ጄምስ ጄፈሪ ይገልጻል። ለዚህም እሱ እንደሚለዉ የጥራት ቁጥጥር ዋነኛዉ ጉዳይ ነዉ። ካለፈዉ ሐምሌ ወር አንስቶ ለጥራቱ ማረጋገጫ የተሰጠዉ የጫካ ቡና ማምረትና ማሻሻጫ ፕሮጀክት የቡናዉን የጥራት ደረጃ ብቻ ሳይሆን የአምራቾቹን ገቢና የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል እንዲሁም 3,296 ሄክታር የተፈጥሮ የደን ይዞታ ለማስጠበቅ እየተንቀሳቀሰ ነዉ። እንደጄፈሪ የኢትዮጵያ ደን ተመናምኗል። 95 በመቶ የሚሆነዉ የተፈጥሮ ደን በእርሻ ሥራ ማስፋፊያ፣ በሰዎች መኖሪያና በሰፈራ እንቅስቃሴዎች እንዳልነበር ሆኗል። የደን መጨፍጨፍና ምንጠራዉ ተግባርም በፍጥነት እያደገ ከሚሄደዉ የሕዝብ ቁጥር ጋ ተዳምሮ አብዛኛዉ ቤተሰብ ለማገዶም ሆነ በተለያዩ መንገዶች ኑሮዉን ለመደገፍ ደኑን ከመመንጠር ሌላ በምንም አማራጭ እንደሌለዉ ያመለክታል። አብዛኞቹ ገበሬዎችም ከዚህ የተለየ አማራጭ እንደሌላቸዉ ያስረዳል። በአሁኑ ወቅት ካለዉ የደን ሀብት 70 በመቶዉ የሚገኘዉ በኦሮሚያ መስተዳድና አካባቢዉ ነዉ። ጄፍሪ ያነጋገራቸዉ የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ተቋም አማካሪ እንደሚሉት አማራጭ አጥቶ እንጂ ሕብረተሰቡ የደን ሀብቱን በመንከባከብ ሊያገኝ የሚችለዉን ጥቅም አልዘነጋዉም። ቡናዉ በዓለም ገበያ እዉቅና አግኝቶለት ኑሮዉን የሚያሻሽልበት አማራጭ ሲቀርብለት መተባበሩም ይህንኑ አመላካች ነዉ።

Japan Äthiopien Kaffee Projekt

የቡና ጥራት ቅምሻዉ

የደን ሀብቱ ሳይጎዳ ወፍ ዘራሹን ቡና በተፈጥሯዊ መንገድ ለፍሬ የሚያበቃለትን ምክር በመቀበሉም ተጠቃሚ ለመሆን የሚችልባቸዉ ስልቶች እየተቀየሱ መሆኑን የኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳት ድርጅት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አራርሳ ረጋሳ ያብራራሉ፤

ዝናብ ጠገብ ደን ዉስጥ ቡናዉ ማደጉን የሚያረጋግጥ ሰርተፊኬት ነዉ የተጠቀሰዉ አካባቢ ያገኘዉ። ይህም ገበሬዎቹ ለዓለም ገበያ ለሚያቀርቡት ቡና ጥራት ትልቅ ዋስትና ነዉ። ዑሺማ ካፌ የተሰኘዉ የጃፓን የቡና አስመጪ ኩባንያ ከዚህ ስፍራ የሚገኘዉ የኢትዮጵያ ወፍ ዘራሽ ቡና ለሀገሩ ቡና ጠጪዎች ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ሃገራት ጥራቱን በጠበቀ የተፈጥሮ ደን ዉስጥ እንደሚበቅል እያስተዋወቀ ነዉ። እንደዘገባዉ ጃፓኖች በፈጣን ባቡሮቻቸዉ ለሚጓዙ መንገደኞች ይህንን ከጅማ ዞን የተፈጥሮ ደን ዉስጥ የበቀለ ቡና ማቅረብ ከጀመሩ አራት ወራት ተቆጥረዋል። አነስተኛ ቡና አምራቾቹ የጥራት ደረጃዉን ጠብቀዉ ዓለም ዓቀፉን የምርጥ ቡና ምልክት ተቀዳጅተዉ ገበያዉን እንዲቆጣጠሩት ደግሞ የዉጭም ሆነ የሀገር ዉስጥ ድርጅቶችና መንግሥታትን ትኩረትና የተቀናጀ ትብብር እንደሚያስፈልጋቸዉም ያስገነዝባል። በዓለም ገበያ እጅግ ተፈላጊ የሆነዉ ወፍ ዘራሹ የጫካ ቡና ህልዉና እንዲቀጥልም የተፈጥሮ ደኑን መጠበቁ አማራጭ እንደሌለዉ ነዉ ግልፅ የሆነዉ። ይህንነዉ አቶ አራርሶ የሚያስረዱት፤

Japan Äthiopien Kaffee Projekt

የቡና አምራቾቹ

ጉዳዩን በቅርበት የተከታተሉና ጄምስ ጄፍሬ ያነጋገራቸዉ ባለሙያዎች እንደሚሉት ከመነሻዉ በርካታ ገበሬዎች ለቡናቸዉ ጥራት ማረጋገጫ የማግኘቱን ርምጃ ብዙም ትኩረት አልሰጡትም ነበር። ሆኖም ከሽያጩ ያገኙት ከበፊቱ የተሻለ ገቢ ትርጉም ሳይኖረዉ የቀረ አይመስም። ምንም እንኳን አንዳንዶቹ አሁንም ያገኙት ገቢ የእነሱን ወገብ በጣሽ ልፋትና የፈሰሰ ላብ እንደማያካክስ በግልፅ ቢናገሩም። ሌላዉ አስተያየት ሰጪ በፕሮጀክቱ ተሳታፊ ከሆኑት ዋናዉ የጃፓን የቡና አስመጪ ኩባንያ አማካሪ እንደሚሉት ደግሞ እየተጀመረዉ መልካምነቱ ባያነጋግርም ዘላቂነቱን ለማረጋገጥም ሆነ ዋጋዉን ከፍ ለማድረግ ግን ትርጉም ያለዉ ጥረት ይጠይቃል። በዚህ መልኩ እንቅስቃሴዉ ተጠናክሮ የኢትዮጵያ የጫካ ቡና ልዩ ሆኖ በዓለም ገበያ ሲቀርብም ደንን ከመራቆት መታደግ መቻሉም ትልቅ ግምት ይሰጠዋል።

አቶ አራርሳም እንደገለፁት አሳታፊዉ የደን ይዞታ በእርግጥም ለጅማ ዞኑ በለጠ ገራ ደን የቡና አምራች ገበሬዎቹን ምርት ወደጃፓን የቡና ገበያ ያሻገረ ስልት ነዉ። ይህ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንደመምታት የሚቆጠረዉ የተፈጥሮ ደኑን እየጠበቁ ወፍ ዘራሹን ቡና የማምረቱ ስልት አጀማመሩ በአንድ አካባቢ ይሁን እንጂ ወደሌላዉም የኦሮሚያ የደን አካባቢ እየተዳረሰ እንደሆነም ገልጸዋል።

ለቡናዉ ተፈጥሯዊ አስተዳደግ አስፈላጊ የሆነዉን የደን ሀብት የቡናዉ ገበሬዎች የሚንከባከቡት የኦሮሚያ ደንና ዱር አራዊት ጥበቃ ተቋሙና ኅብረተሰቡ በጋራ በአሳታፊዉ የደን ክብካቤ ስልት እንደመሆኑ ኅብረተሰቡ ለግል ፍጆታዉ የሚሆነዉን ዛፍ እየተከለ እንዲጠቀም አሠራሩ በመግባባት መመቻቸቱን አራርሳ ያስረዳሉ፤

የደኑን ህልዉና ለማስቀጠል የኅብረተሰቡ የአኗኗር ሁኔታ መለወጥ እንደሚኖርበት ያመላከቱ ወገኖች አልጠፉም። ተመሳሳይ ሃሳብ የሰነዘሩት የኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳት ድርጅት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አራርሳ ረጋሳም የተፈጥሮ ደኑ እንዲጠበቅ የኅብረተሰቡ ኑሮ መለወጥ ወሳኝ እንደሆነ ነዉ አፅንኦት የሰጡት። ማብራሪያ በመስጠት የተባበሩንን የኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳት ድርጅት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አራርሳ ረጋሳን ከልብ እናመሰግናለን።

James Jeffrey /ጀምስ ጄፈሪ /ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic