1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት እና የአርሶ አደሩ ተሳትፎ

ቅዳሜ፣ መጋቢት 21 2016

በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በዓለም ወቅታዊ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የናረውን የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ ለመቋቋም አርሶ አደሮች ፊታቸውን ወደ ተፈጥሮ ማዳበሪያ (ፍግ) በማዞር የወጪ ቅነሳ ስልቱን እንዲያግዙ እየተጠየቁ ነው፡፡

https://p.dw.com/p/4eHDL
Äthiopien Landwirte
በአርሶ አደሮች የተዘጋጀ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ምስል Seyoum Getu/DW

የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ከውጭ የሚገባውን ምን ያህል ያግዛል?

የተፈጥሮ አፈር ማዳበሪያ ትኩረት የሚሻበት ምክኒያት

ገበሬው በአከባቢው ባለው ተረፈ ምርት በመጠቀም ማምረት የምችለው  የተፈጥሮ አፈር ማዳበሪያ ከውጪ በከፍተኛ ወጪ የሚገባውን የአፈር ማዳበሪያን ወጭ ለመቀነስ አይነተኛ ሚና እንዳለው ይነገርለታል፡፡

በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በዓለም ወቅታዊ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የናረውን የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ ለመቋቋም አርሶ አደሮች ፊታቸውን ወደ ተፈጥሮ ማዳበሪያ (ፍግ) በማዞር የወጪ ቅነሳ ስልቱን እንዲያግዙ እየተጠየቁ ነው፡፡በአማራ ክልል የንግድ ሥራ ድባቴ ተጭኖታል፤ ግብርና ሌላ ሥጋት ተጋርጦበታል

በጅማ ዞን ጎማ ወረዳ በዝግጅቱ ላይ ያለውን የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት መነሻ በማድረግ የተፈጥሮ አፈር ማዳበሪያው ኢኮኖሚያዊ እና የተፈጥሮ ጥበቃ ሚናውን ቃኝተናል፡፡

የተፈጥሮ አፈር ማዳበሪያ አዘገጃጀት

የጅማ ዞን ጎማ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊና የግብርና ባለሙያው መሃመድ ሰፋ ከድር በወረዳው ከአጋሮ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ ቀበሌ በተፈጥሮ አፈር ማዳበሪያ (ፍግ) ዝግጅት ላይ ተጠምደዋል፡፡ የተፈጥሮ ማዳበሪያን በማዘጋጀቱ ረገድ ጉልህ ሚና ያለው “ቨርም” የተሰኘውን የተለያዩ ተረፈ ምርቶችን ወደ አፈር ማዳበሪያነት የሚቀይረው ትል በብዛት በዚህ ማዕከል ውስጥ ይባዛል፡፡ መሰል ጥረቱም ከተጀመረ ገና አንድ ዓመት እንኳ አልሆነም የሚሉት ባለሙያው የጥረቱ ውጥንም እየናረ የመጣውን ከውጪ የሚገባውን የአፈር ማዳበሪያ ለማገዝ፤ በረጅም ጥረት ከተቻለም ለመተካት ነው ይላሉ፡፡ “የአፈር ማዳበሪየውን እንደአማራጭ እንዲጠቀሙ ነው ዋናው ውጥን፡፡ በዋናነት ግን በዚህ ማዕከል የተፈጥሮ የአፈር ማዳበሪያ (ኮምፖስት) ማዘጋጀት ሳይሆን ትሉን በማባዛት ወደ ገበሬዎች በመበተን በትሉ ገበሬዎች የአፈር ማዳበሪያውን በቤታቸው እንዲያዘጋጁ ማድረግ ነው ዓላማችን” ብለዋል፡፡

በጅማ ዞን የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት
የጅማ ዞን ጎማ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊና የግብርና ባለሙያው መሃመድ ሰፋ ከድር በወረዳው ከአጋሮ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ ቀበሌ በተፈጥሮ አፈር ማዳበሪያ (ፍግ) ዝግጅት ላይ ተጠምደዋል፡፡ምስል Seyoum Getu/DW

የ“ቨርም” ማዕከላት ሚናአፈር ፣ ምርታማነት እና የማዳበሪያ አጠቃቀም

በዚህ የ“ቨርም” ማዕከል የተለያዩ ተረፈ ምርቶች ዘመናዊ በሆነ መንገድ በትሎቹ እንዲደቁ ይደረጋል፡፡ ቨርም የተባለው ትልም ለመኖር ሲል የሚመገበውን የሚሰጠውን ተረፈ ምርት ወደ ደቃቅ አፈርነት ይቀይረዋል፡፡ ይህን የተፈጥሮ አፈር ማዳበሪያ መጠቀም ከወጪ ቅነሳም በላይ ጥቅም እንዳለውም አቶ መሃመድ ሰፋ ያስረዳሉ፡፡ “አንደኛ ጥቅሙ ከተፈጥሮ ጋር ተስማሚ በመሆኑ የአከባቢ ብክለት አይፈጥርም ወይም የአፈር ለምነትን አይቀንስም፡፡ ሌላው ጥቅሙ ገበሬ በቤቱ ይህን እንደአማራጭ ማምረት ከቻለ ለሰው ሰራሹ አፈር ማዳበሪያ የሚያወጣውን ወጪ በእጅጉ ይቀንስለታል” ብለዋል፡፡ ሌላው የተፈጥሮ ማዳበሪያ ጥቅሙ አንዴ ለጥቅም የሚውለው የተፈጥሮ አፈር ማዳበሪያ እንደ ሰው ሰራሹ የአፈር ማዳበሪያ በያመቱ ለመጠቀም የሚያስገድድ ሳይሆን አንዴ ጥቅም ላይ የሚውለው ለሶስት ተከታታይ ዓመታት ለምርት ጥቅም እንደሚውልም ተነግሮለታል፡፡ አቶ ሰፋም በወረዳቸው የተለያዩ “የቨርም” ማዕከላት ብኖሩም ከዚህ ማዕከል ብቻ የተፈጥሮ አፈር ማዳበሪያ ለማምረት የሚረዳውን ይህን ትል ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ በሁለት ዙር ከ1 ሺህ 350 ኩንታል በላይ በማባዛት ለአርሶ አደሮች ማከፋፈል  መቻሉን አስረድተዋል፡፡

በተፈጥሮ ማዳበሪያ እንክብካቤ የሚደረግለት የቡና ማሳ
የተፈጥሮ ማዳበሪያ ጥቅሙ አንዴ ለጥቅም የሚውለው የተፈጥሮ አፈር ማዳበሪያ እንደ ሰው ሰራሹ የአፈር ማዳበሪያ በያመቱ ለመጠቀም የሚያስገድድ ሳይሆን አንዴ ጥቅም ላይ የሚውለው ለሶስት ተከታታይ ዓመታት ለምርት ጥቅም እንደሚውልም ተነግሮለታል፡፡ ምስል Seyoum Getu/DW

የተፈጥሮ አፈር ማዳበሪያ የአፈር አሲዳማነትን ለመቀነስ

በኦሮሚያ ግብርና ቢሮ የአፈር ለምነትና ማሻሻል ዳሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ እሸቱ ለገሰ ለተፈጥሮ አፈር ማዳበሪያ የአማራጭነት ሃሳብ መንግስት ትኩረት የተሰጠበት ያሉትን ምክኒያት ስያስረዱ፤ “የተፈጥሮ ማዳበሪያ አንደኛ የአፈር ንትረ ነገር ይዞ የመቆየት አቅም አለው፡፡ ይህ የአፈር እርጥበታማነት እንዲጠበቅ ይረዳል፡፡ አሁን አሁን በአስጊ ሁኔታ እየተስፋፋ ያለውን የአፈር አሲዳማነትንም ለመቀነስ ጉልህ ሚና ይኖረዋል፡፡ ለዚህም ነው ትኩረትም የተሰጠው” ብለዋል፡፡የማዳበሪያ መዘዝ በሐዲያ

የተፈጥሮ አፈር ማዳበሪያ ከውጪ የሚገባውን ማዳበሪያ ይተካ ይሆን?

ይህ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅቱ ላይ ዋና ዓላማ ተደርጎ ለጊዜው የሚሰራበትም ከውጪ የሚገባውን ሰው ሰራሽ የአፈር ማዳበሪያን ለመተካት ሳይሆን ብያንስ ፍጆታውን ለመቀነስ እንደሆነም አቶ እሸቱ አስረግጠው አስረድተዋል፡፡ “ሰው ሰራሽ የአፈር ማዳበሪያ እጥረት እያጋጠመን መሆኑ ይታወቃል፡፡ አሁን እሱን ለመተካት ሳይሆን ጎን ለጎን መጠቀም ነው ፍላጎታችን፡፡ አጠቃላይ በተፈጥሮ ማዳበሪያው ይህን እንተካ ብንል አይቻልም፡፡ የግብዓት እጥረት የአዘገጃጀት ጥራት ጉድለትም ሊያጋጥመን ስለሚችል ሁለቱንም ጎን ለጎን መጠቀሙ የተሸለ ነው ብለን ይዘናል” ነው ያሉት፡፡

በተፈጥሮ ማዳበሪያ እንክብካቤ የሚደረግለት የቡና ችግኝ ማሳ
የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅቱ ላይ ዋና ዓላማ ተደርጎ ለጊዜው የሚሰራበትም ከውጪ የሚገባውን ሰው ሰራሽ የአፈር ማዳበሪያን ለመተካት ሳይሆን ብያንስ ፍጆታውን ለመቀነስ እንደሆነም አቶ እሸቱ አስረግጠው አስረድተዋል፡፡ምስል Seyoum Getu/DW

ኢትዮጵያ ከውጪ ለምታስገባው የአፈር ማዳበሪያ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ፈሰስ ለማድረግ እንደምትገደድ ይታወቃል፡፡ ያም ሆኖ ባለፈው ዓመት በግዢ እና ስርጭት ሂደቱ ላይ ባጋጠመው ሰፊ ክፍተት ህገወጥነትም ተንሰራፎ ከፍተኛ የአፈር ማዳበሪያ እጥረት ገበሬውን በማጋጠሙ ምርታማነትም ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደሩ አይዘነጋም፡፡

ስዩም ጌቱ

ታምራት ዲንሳ