የተባባሰው ዩክሬን ጦርነት በጀርመናውያን ላይ ያሳደረው ፍርሀት  | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 22.03.2022
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የተባባሰው ዩክሬን ጦርነት በጀርመናውያን ላይ ያሳደረው ፍርሀት 

በዩክሬኑ ጦርነት ሰበብ በጀርመን ሰዉ ፍርሀት ውስጥ የመሆኑ ምልክት እየታየ ነው ።ጭንቀቱ  የበረታበት ወደፊት ሊደርስ ይችላል ብሎ ለሚያሰጋው አደጋ  ዝግጅት እስከማድረግ ደርሷል። ለወትሮው እንደልብ ይገኙ የነበሩ የምግብ ዘይት፣ፓስታ ዱቄትና እርሾን የመሳሰሉት ከምግብ መደብሮች መደርደሪያዎች  መጥፋት ከጀመሩ ቆዩ።

ዩክሬን ጦርነት በጀርመናውያን ላይ ያሳደረው ፍርሀት 

 የዩክሬን ጦርነት አውሮጳውያንን በእጅጉ ማስጋቱ ቀጥሏል። ጦርነቱ ወደ ሌሎች የአውሮጳ ሀገራት ሊስፋፋ ይችላል የሚል ስጋት ያደረባቸው፣ሊመጣ ይችላል ብለው ለሚፈሩት የከፋ ጊዜ ከወዲሁ እየተዘጋጁ ነው። አንድ ወር ሊደፍን ሁለት ቀናት የቀሩት የሩስያ ዩክሬን ጦርነት ሕይወት እያጠፋ በርካቶችን እያፈናቀለ  ልዩ ልዩ መሰረተ ልማቶችን እያወደመ ቀጥሏል። ከ3.5 ሚሊዮን በላይ የዩክሬን ዜጎችን ከሀገራቸው ያሰደደው ጦርነት በተለያየ የዓለም ክፍል ያስከተለው ተጽእኖም ቀላል አይደለም። ጦርነቱ በተለያዩ ሀገራት የነዳጅና የምግብ ዋጋ ንረትና የአንዳንድ ሸቀጦችን እጥረትም አስከትሏል። በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ ተጽእኖው እየጠነከረ በመሄድ ላይ ያለው የዩክሬን ጦርነት በአውሮጳ  ስጋቱ እንዲጨምር እያደረገ ነው። በጀርመን ሰዉ ፍርሀት ውስጥ የመሆኑ ምልክት እየታየ ነው ።ጭንቀቱ  የበረታበት ወደፊት ሊደርስ ይችላል ብሎ ለሚያሰጋው አደጋ  ዝግጅት እስከማድረግ ደርሷል። ለወትሮው እንደልብ ይገኙ የነበሩ የምግብ ዘይት፣ፓስታ ዱቄትና እርሾን የመሳሰሉት ከምግብ መደብሮች መደርደሪያዎች  መጥፋት ከጀመሩ ሳምንት አልፏል። ሰዉ ለረዥም ጊዜ ሳይበላሹ ሊቆዩ የሚችሉ የምግብ ዓይነቶችን ማከማቸት የያዘ ይመስላል። ይህ ኮቪድ 19 ጀርመን በገባበት ወቅትም የታየ ክስተት ነበር። ያኔ በተለይ የመጸዳጃ ወረቀት እጥረት የጎላ ነበር ።አሁን ደግሞ በተለይ የምግብ  ዘይት የውሀ ሽታ የሆነ ይመስላል። በርሊን የሚገኘው የዶቼቬለ ወኪል

ይልማ ኃይለ ሚካኤል እንደታዘበው በጀርመን የዩክሬን ጦርነት ያስከተለው ስጋትና ፍርሀት መነሻ የተለያየ ነው።በርሱ አስተያየት በአሁኑ ጊዜ የዩክሬን ስደተኞች በብዛት ወደ ጀርመን በመግባት ላይ መሆናቸው አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ሌሎችም ምክንያቶች አሉ ይላል ይልማ ። የኤኮኖሚ ምሁሩ ዶክተር ጸጋዬ ደግነህ ደግሞ የፍርሃቱና የስጋቱ ምንጭ ህዝቡ ስለ ዩክሬኑ ጦርነት  ይደርሰዋል ያሉት ወደ አንድ ወገን ያጋደሉ መረጃዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገምታሉ። ጀርመናውያን ለዩክሬን ድጋፋቸውን በመግለጽ ላይ ባሉበት በአሁኑ ወቅት  የዩክሬን ባለስልጣናት በጀርመን ላይ የሚያደርጉት  ተጨማሪ ጫናም የህዝቡ ፍርሀት እንዲባባስ አስተዋጽኦ አድርጓል ይላሉ።
ዶክተር ጸጋዬ እንደሚሉት የጀርመንና የዩክሬን የንግድ ትስስር በወር እስከ 2.6 ቢሊዮን ዩሮ ይደርሳል። ከ4ሺህ በላይ የጀርመን ኩባንያዎች ደግሞ ሩስያ ውስጥ ይገኛሉ። ጀርመን የተለያዩ  የኢንዱስትሪ ምርቶችን ከሩስያ የምታስገባ ሀገር ናት። ይህ ሁሉ የንግድ ግንኙነት በጦርነቱ ሲጎዳ ጀርመናውያን በሀገሪቱ ላይ ከፍተኛ የኤኮኖሚ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል እየዋለ እያደር እየተገነዘቡት የመጡ ይመስላል ብለዋል። ።አ አር ዴ የተባለው የጀርመን ቴሌቪዥን ባካሄደው የህዝብ አሰተያየት መመዘኛ  ከጠየቃቸው ጀርመናውያን 64 በመቶ  ግጭቱ የጀርመን ኤኮኖሚ

እንዲያሽቆለቁል ማድረጉ አይቀርም ብለዋል። ሌላው የጀርመናውያን ስጋት የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን መከላከያ ድርጅት ኔቶ ብሎም ጀርመን በዩክሬኑ ጦርነት ጣልጋ ሊገቡ ይችላሉ የሚለው ነው።ፎርሳ የተባለው የህዝብ አስተያየት መመዘኛ ተቋም ከጠየቃቸው 1000 ሺህ ጀርመናውያን 69 በመቶው ይህ ስጋት አላቸው። ከዩክሬን በኩል በተደጋጋሚ የሚቀርበው አቤቱታ አካል የሆነው ጥያቄ እስካሁን ከጀርመን ፖለቲከኞች በኩል እሺታ ያላገኘ ጉዳይ በመሆኑ እውን ሊሆን  አይችልም ባይ ነው ይልማ ። 
ከዩክሬን ጦርነት ጋር በተያያዘ ጀርመናውያን ሊደርስብን ይችላል ከሚሉትና ከሚያሳስባቸው ጉዳዮች አንዱ የሳይበር ጥቃት ነው። በተለይ ይህ ጥቃት ከሩስያ በኩል ሊሰነዘር ይችላል ተብሎም ይፈራል። በዚህን መሰሉ ጥቃት የኃይልና የውኃ አቅርቦት ሊቋረጥ የመቻሉ ስጋት ፍርሀት ከፈጠሩት ውስጥ ይጠቀሳል። ይህ ጉዳይ ተገቢው ትኩረት እንዲሰጠው የፌደራል የጀርመን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትርም አሳስበዋል። ይልማ ኃይለ ሚካኤል እርሱ ይሆናል ብሎ ባያስም ሊሆን የሚችል ነው ብሏል።
ዶክተር ጸጋዬም የሳይበር ጥቃት ሊፈጸም ይችላል ይሆናል ብለው ይሰጋሉ። ታዲያ አሁንም በቀጠለው በዩክሬን ጦርነት መንስኤ ፍርሃትና ጭንቀት ውስጥ ያለውን ህዝብ ምን ያረጋጋው ይሆን ይልማም ዶክተር ጸጋዮም ህዝቡን የማረጋጋት ስራውን ለፖለቲከኞች ለሃይማኖት አባቶችና ተሰሚነት ላላቸው ሰዎች ሰጥተዋል። 

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ 
 
 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች