የተሰናከለው ስብሰባ
ሰኞ፣ መስከረም 6 2017የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ባለስልጣናት በሽረ ከተማ ትላንት እያካሄዱት የነበረ ህዝባዊ ስብሰባ በተፈጠረ ረብሻ ምክንያት ተቋረጠ። የግዚያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ ጨምሮ በርካታ የክልሉ ባለስልጣናት በመድረኩ ታድመው የነበረ ሲሆን፥ በአዳራሹ ውስጥ በየጎራው ከፍተኛ የተቃውሞ እና ድጋፍ ድምፅ መስተጋባት መጀመሩ ተከትሎ ህዝባዊ መድረኩ እንደተቋረጠ ተገልጿል። የትግራይ ኮምኒኬሽን ቢሮ ረብሻው ሆን ተብሎና ታቅዶ የተፈፀመ ብሎታል።
በህወሓት ውስጥ ባሉ ሁለት ቡድኖች መካከል ያለውአለመግባባት እየተካረረበሚገኝበት በአሁኑ ወቅት፥ የእዚህ መካረር ማሳያ ነው የተባለለት የትላንቱ የሽረ ክስተት በበርካቶች ዘንድ መነጋገርያ ሆንዋል። ትላንት እሁድ ጠዋት ሊካሄድ ታቅዶ የተጀመረው አቶ ጌታቸው ረዳ ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የታደሙበት ህዝባዊ ስብሰባ መጀመሩ ከተነገረ ደቂቃዎች በኃላ በተፈጠረ ረብሻ ተቋርጧል። ከሽረ ከተማ ያነጋገርናቸው እና በህዝባዊ መድረኩ ለመሳተፍ ታድመው ከነበሩት ውስጥ የሆኑ አስተያየት ሰጪዎች እንደገለፁልን፥ መድረኩ የተቋረጠው አስቀድመው ተደራጅተው በገቡ ባልዋቸው በአብዛኛው ሴቶችና አዛውንቶች ጩኸትና ስድብ ነው ያሉ ሲሆን፥ በሌላ በኩል ደግሞ ህዝባዊ መድረኩ እንዲቀጥል የሚጠይቁ በርካታ ወጣቶች በመሰብሰብያ አደራሹ ድምፃቸው ሲያሰሙ፣ የግዚያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝደንት በስም እየጠሩ ድጋፋቸው ሲገልፁ መስተዋሉ ነግረውናል። በተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት ደግሞ የታቀደው ህዝባዊ መድረክ በተጀመረ በደቂቃዎች ውስጥ ተቋርጦ፣ ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ ጨምሮ ሌላች የመድረኩ ተሳታፊዎች ከአደራሹ መውጣታቸው ተነግሯል።
ከሽረ ያነጋገርነው በቦታው የነበረ ወጣት "የግዚያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝደንትን 'ባንዳ፣ ሌባ' የሚሉ ነበሩ። በሌላ በኩል ደግሞ በአብዛኛው ወጣቶች የሆኑ 'ጌታቸው ጀግና' እያሉ ድጋፍ የሚሰጡም ነበሩ። በዚህ መሃል ከፍተኛ ድምፅ ጩኸት ነው የተፈጠረው። መደማመጥ ጠፋ። በአጠቃላይ ሰው ለሁለት ነው የተከፈለው" ሲል የታዘበው ነግሮናል።
በዚሁ ጉዳይ ዙርያ ትላንት እሁድ መግለጫ ያወጣው የትግራይ ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ፅሕፈት ቤት ታቅዶ የነበረው መድረክ "አስቀድሞ መመርያ ተሰጥቷቸው የገቡ የተወሰኑ ሰዎች" መድረኩን ሆን ብለው እንዳወኩት የገለፀ ሲሆን፥ በቀጣይ የህዝቡ ፍላጎት በተለይም ድጋፍ የገለፁ ወጣቶች ታሳቢ በማድረግ በአጭር ግዜ ውስጥ ዳግም ህዝባዊ ውይይቱ እንደሚደረግ አስታውቋል።
ይህ ሁኔታ በመፈጠሩ መድረኩ መቋረጡ፣ ያለን ጥያቄ ለአስተዳደሩ እንዳናቀርብ አግዶናል በማለት ወጣቶቹ ቅሬታቸው ገልፀዋል።
ከዚህ ቀደም የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕረዚደንትአቶ ጌታቸው ረዳየሚታደሙባቸው ህዝባዊ ስብሰባዎች እና የጎዳና ትእይንቶች በትግራይ ክልል ዓብይዓዲ፣ ዓዲግራት፣ ማይጨው እና ሌሎች ከተሞች ተካሂደው የነበረ ሲሆን በአንፃሩ ተመሳሳይ መድረኮች የተደናቀፉበት አጋጣሚም በአንዳንድ አካባቢዎች ተስተውሏል። አስቀድመው ተካሂደው በነበሩ መድረኮች በአንዱ የህወሓት ክንፍ ላይ ከፍተኛ ትችት ሲሰነዘርም ተስተውሎ ነበር።
ስለሁኔታው ከሽረ እንዳስላሰ ፖሊስ ፅሕፈት ቤት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ሚልዮን ሃይለስላሴ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ፀሐይ ጫኔ