1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተመድና የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች አጣሪዎች ልዩነት

ማክሰኞ፣ መስከረም 10 2015

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና የተባበሩት መንግሥታት ባለፈው ዓመት ባደረጉት ጣምራ ምርመራበትግራይ ክልል ውስጥ በነበረው ጦርነት በሰብዓዊነት ላይ የተፈፀመ እና የጦር ወንጀል ሊባሉ የሚችሉ የወንጀል ዓይነቶች መፈፀማቸውን የሚያመለክቱ ማስረጃዎች መገኘታቸውን አመልክተው ነበር።

https://p.dw.com/p/4H7O7
UN Menschenrechtsrat in Genf
ምስል picture-alliance/dpa/S. Di Nolfi

የተመድ ሰብአዊ መብትና አጣሪና የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ልዩነት

ሰሜን ኢትዮጵያ ዉስጥ ከዚሕ ቀደም በተደረገዉ ጦርነት ተፈፅሟል በተባለዉ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሰበብ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት የሰየመዉ አጣሪ ኮሚሽንና የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እየተወዛገቡ ነዉ።የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት አምና ታሕሳስ የሰየመዉ አጣሪ ኮሚሽን  ትንናት እንዳስታወቀዉ የጦርነቱ ተካፋዮች የጦር ወንጀል ፈፅመዋል ብሎ ያምናል።የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ግን የዓለም አቀፉ ድርጅት መርማሪዎች ያወጡት ዘገባ በስፋትም ሆነ በጥልቀት ከዚሕ ቀደም ከተደረገዉ ምርመራ ጋር አይገናኝም ባይ ነዉ።የመብት ተሟጋቾቹ ዉዝግብ   ዛሬ ሲሰማ ኢትዮጵያና ኤርትራ ድንበር ላይ ሙሉ ጦርነት መከፈቱ  ተዘግቧል።

በነበረው ግጭት የተሳተፉ ወገኖች የጦር ወንጀል ፈጽመዋል ብለው እንደሚያምኑ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ጥሰት መርማሪዎች ገለፀዋል። 
መርማሪዎቹ በትግራይ ክልል በሰብዓዊነት ላይ ከተፈጸሙ ወንጀሎች በስተጀርባ የመንግሥት እጅ አለበት ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና የተባበሩት መንግሥታት ባለፈው ዓመት ባደረጉት ጣምራ ምርመራበትግራይ ክልል ውስጥ በነበረው ጦርነት በሰብዓዊነት ላይ የተፈፀመ እና የጦር ወንጀል ሊባሉ የሚችሉ የወንጀል ዓይነቶች መፈፀማቸውን የሚያመለክቱ ማስረጃዎች መገኘታቸውን አመልክተው ነበር። 

አሁን የተባበሩት መንግሥታት የመርማሪ ኮሚሽን ቡድን አባላት ያቀረበው ዘገባ በርቀት የተከናወነ ከመሆኑ በላይ በስፋትም ሆነ በጥልቀት ከዚህ በፊት ከደረገው ምርመራ ጋር የሚገናኝ እንዳልሆነ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ተናግሯል። በመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ባለፈውዓመት የተቋቋመው እና ሦስት ገለልተኛ ናቸው የተባሉ የመብት ጥሰት መርማሪ ባለሙያዎችን ያቀፈው ኮሚሽኑ ተፈጽመዋል ያላቸው የመብት ጥሰቶች"የጦር ወንጀል እና በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ናቸው ብሎ ለማመን ተጨባጭ ምክንያቶች እንዳሉት" ተናግሯል.ባለሙያዎቹ በትግራይ አስከፊ ሁኔታ መኖሩን ገልጸው፣ መንግሥት እና አጋሮቹን ከአንድ ዓመት በላይ ለሆነ ጊዜ ኢንተርኔትና ባንክን ጨምሮ ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶችን ማገዳቸውን ነቅፈዋል። በጉዳዩ ዙሪያ የመንግሥትን ምላሽ ለማካተት ጥረት ባደርግም ለጊዜው ስልክ ባለመነሳቱ አልተሳካም። 
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ከዚህ በፊት ባወጣው መግለጫ ግን "መርማሪው ቡድን የተቋቋመበት ሂደት እና የተሰጠው ኃላፊነት ግልፅነት የጎደለው፣ ተገቢ ያልሆነ የፖለቲካ ቅኝት ያለው እና ከዚህ ቀደም የተባበሩት መንግስታት የሰብዐዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ጽ/ቤት እና የኢትዮጵያ የሰብዐዊ መብቶች ኮሚሽን በጥምረት ያደረጉትን የሰብዐዊ መብት ጥሰት ምርመራ እንዲሁም የዚህም የጥምር ምርመራ ቡድን ምክረ ሃሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ በተገቢው መልኩ ታሳቢ ያደረገ እንዳሆነ" ጠቅሶ ይሁንና "የተቋቋመው ኮሚሽን ሃላፊነቱን ሲወጣ የመንግስትን መሠረታዊ አቋም ባገናዘበ እንዲሁም የዓለም አቀፍ የሰብዐዊ መብት ስርዐት የብሄራዊ የህግ ስርዐቱ ደጋፊ እና ሟሟያ ሆኖ መታየት እንዳለበት አፅኖት የሚሰጠው የአሟይነት መርህ ባከበረ፣ ተገቢነት ከሌላቸው የፖለቲካ ፍላጎቶች ነፃ በሆነ መንገድ የሚንቀሳቀስ ከሆነ ከኮሚሽኑ ጋር የመተባበርን ጉዳይ መልሶ የማጤን እድል እንደሚኖር" ተናግሮ መርማሪዎቹም ለምርመራ ባይሆንም ለጉብኝት ዲስ አበባ መጥተው ነበር። 

ሰለሞን ሙጬ 

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ