1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የብሊንከን ጉብኝት፣የተንታኞች አስተያየት

ዓርብ፣ መጋቢት 8 2015

አንቶኒ ብሊንከን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ "መርዛማ ቅራኔዎችን እና የጎሳ መከፋፈልን ማስወገድ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ብሔር ተኮር ግጭቶችን ለማስወገድ ብቸኛው መንገድ ነው" ብለው ነበር።

https://p.dw.com/p/4Oqkw
Äthiopien USA Demeke Hasen Antony Blinken
ምስል Ethiopian Foreign Ministry

የብሊከን ጉብኝት ዓላማና ዉጤቱ፤ ትንታኔ

 

የዩናትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ኢትዮጵያን የጎበኙበት ምክንያትና የጉብኝቱ ዉጤት በፖለቲካ ተንታኞች ዘንድ የተለያየ ግን ተቀራራቢ አስተያየት እየተሰጠበት ነዉ።የአዲስ አበባዉ ወኪላችን ካነጋገራቸዉ ተንታኞች አንዱ ጉብኝቱ የኢትዮጵያ መንግስትና ሕወሓት ባደረጉት ስምምነት ዩናይትድ ስቴትስ መደሰትዋን ጠቋሚ ነዉ ይላሉ።ሌላኘዉ ተንታኝ እንደሚገምቱት ደግሞ በሰሜን ኢትዮጵያዉ ጦርነት ሰበበብ የሻከረዉ የአዲስ አበባና የዋሽግተን ግንኙነት መሻሻሉን አመልካች ነዉ።ብሊንከን  በኢትዮጵያ ጉብኝታቸዉ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች የገቡትን ቃል እንዲያከብሩ፣ ፍትሕን እንዲያሰፍኑና በሕዝብ መካከል መግባባትን እንዲፈጥሩ አደራ ብለዋል።
 የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በኢትዮጵያ ያደረጉትን የሥራ ጉብኝት ተልእኮ አጠናቀው ትናንት ወደ ሌላኛዋ ወደብ አልባ የምዕራብ አፍሪካዋ አገር ኒጀር ተጉዘዋል።
አሜሪካ እኒህን ፖለቲከኛ ወደ ኢትዮጵያ ስትልክ እንደምታውን ከጠየቅናቸው አንዱ ዶክተር ጌድዮን ጃለታ በአሜሪካ በኩል ደስታን ያስከተለ የግንኙነት መሻሻል የመታየቱ ማሳያ አድርገው ገልፀውታል።
"ግንኙነታቸው መሻሻሉን ያሳያል። ትልቅ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደዚህ ሲመጣ ያንን ያሳያል። የሰላም ስምምነቱ መፈረሙ፣ እንደገና ደግሞ ነገሮች በዚያ መቀጠላቸው፣ አሜሪካን እንዳስደሰታት ያሳያል" ።
ስማቸው እንዱጠቀስ ያልፈለጉ ሌላ የዓለም አቀፍ ሕግ እና ፓለቲካ ዐዋቂ ሰው "ባለፉት ሁለት ዓመታት ሻክሮ የቆየው ግንኙነታቸውን የማሻሻል ፍላጎት እንዳለ የሚያሳይ ነው" ብለዋል።
"ቀደም ብሎ የነበረው የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ ግንኙነት በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ሻክሮ ነበር። አሁን ግንኙነትን የማሻሻል ፍላጎት እንዳላቸው በግልጽ የሚያሳይ ነው። ሁለተኛው ነገር ግን በዩክሬን ጉዳይ ላይ ከአፍሪካ ጋር ምእራባዊያን የተለያየ አሰላለፍ ነው የነበራቸው። ይህም ማለት ወይ ከእኛ ጋር ወይም ከእነሱ [ ከራሺያ ] ጋር የሚለውን አቋማቸውን ትንሽ ወደ ማለስለስ መሄድ እንዳለባቸው የተረዱበት ፍላጎት ነው"።
አንቶኒ ብሊንከን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ "መርዛማ ቅራኔዎችን እና የጎሳ መከፋፈልን ማስወገድ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ብሔር ተኮር ግጭቶችን ለማስወገድ ብቸኛው መንገድ ነው" ብለው ነበር። ይህንን እንዲሉ ምን ምክንያት አላቸው ያልናቸው ዶክተር ጌድዮን ሲመልሱ
"አሜሪካኖች ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም መኖሩ ለአካባቢው - ለአፍሪካ ቀንድ ጥቅም እንዳለው ያውቃሉ። ስለዚህ እዚህ የሚሆነውን ነገር በአጽንዖት ነው የሚከታተሉት። ከዚህ አንፃር እንደዚህ አይነት አስተያየቶችን ይሰጣሉ" ብለዋል።
ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉት ባለሙያም ተመሳሳይ አቋም አላቸው።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በተጨማሪ በስም ባይጠቅሷቸውም ከሰላም ስምምነቱ ፈራሚ የሕወሓት ባለስልጣናትንም ጋር ማነጋገራቸውን ገልፀው ነበር። 
አቶ ጌታቸው ረዳ አዲስ አበባ ላይ ተገኝተው እንደነበርና በዚህ ውይይት ላይ መሳተፋቸውን በትዊተር ፅፈዋል።

ብሊንከን ከደመቀ ጋር
ብሊንከን ከደመቀ ጋር ምስል Ethiopian Foreign Ministry
ብሊንከን ከዐብይ ጋር
ብሊንከን ከዐብይ ጋር ምስል Fana Broadcasting Corporate S.C

ሰለሞን ሙጪ 

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ