1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርትኢትዮጵያ

ትምህርት ለመማር እየተማፀኑ ያሉ ተማሪዎች

ልደት አበበ
ዓርብ፣ መጋቢት 13 2016

የዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት እንግዶቻችን በ2016 ዓ/ም በባህርዳር ዩኒቨርስቲ ገብተው እንዲማሩ የተመደቡ አዲስ ገቢ ተማሪዎች ናቸው። ይሁንና እስካሁን ትምህርት አለመጀመራቸው እንዳሳሰባቸው በመግለፅ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ። እስካሁን ከሚለከታቸው አካላት ያገኙት ምላሽ ግን በትዕግስት ጠብቁ የሚል ነው።

https://p.dw.com/p/4dwRz
የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ህንፃ
የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲምስል Matyas/Pond5 Images/IMAGO

ትምህርት ለመማር እየተማፀኑ ያሉ ተማሪዎች

 በዚህ የወጣቶችን ጉዳይ በሚያስተናግደው እና ለወጣቶች መድረክ በሚሰጠው የዶይቸ ቬለ ክፍለ ጊዜ ቅሬታቸውን እንድናስተናግድ የጠየቁን ተማሪዎች በ2015 ዓመተ ምህረት የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተናን ተፈትነው ካለፉ 3 በመቶ ያህል ተማሪዎች መካከል ሲሆኑ ነገር ግን እስካሁን ትምህርት አልጀመሩም።  ይህም የተመደቡበት ባህርዳር ዩኒቨርስቲ ተማሪዎቹን እስካሁን ጠርቶ ማስተማር ባለመቻሉ ነው።  ለደህንነቱ ሲባል ስሙን በራዲዮ እንዳንገልፅ የጠየቀን አንድ ወጣት «ከረዥም ወራት ጥበቃ በኋላ ጥር 21 ትምህርት እንድንጀምር ጥሪ ደርሶን ነበር ። ግን ባላወቅነው ምክንያት ሶስት ቀን ሲቀረው ተራዘመ» ይላል።  በዚህም ምክንያት የተወሰኑ ተማሪዎች ቅሬታቸውን ለማሰማት ወደ ትምህርት ሚኒስቴር እና የተመደቡበት ባህር ዳር ዩኒቨርስቲ አቅንተው ነበር። ግን እስካሁን መፍትኼ ሳያገኙ ቀርተዋል።  « ትምህርት ሚኒስቴርን ስንጠይቅ እንድንበትናችሁ ዩኒቨርሲቲው ፍቃደኛ መሆን አለበት አለ። ከዛ የሆኑ ተማሪዎችን አስተባብረን ወደ ባህርዳር ዩኒቨርስቲ እንዲሄዱ አደረግን። » የሚለው ወጣት ተማሪዎቹ እንወያይበታለን ከሚል ምላሽ በስተቀር አጥጋሚ ምላሽ እንዳልሰጣቸው ይናገራል።

የትምህርት ሚኒስቴር ምላሽ

ፍሬ የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ካለፉ ወይም ከ 50 በመቶ በላይ ውጤት ካስመዘገቡ 27 ሺ 267 ተማሪዎች መካከል ሌላኛዋ መማር ያልቻለች ወጣት ናት። ፍሬ ትክክለኛ ስሟ አይደለም። እሷም ለደህንነቷ ሲባል ትክክለኛ ስሟን እንዳንገልፅ ጠይቃናለች። ወጣቷ ቅሬታቸውን ለማሰማት ወደ ትምህርት ሚኒስቴር ተወክለው ከሄዱት ተማሪዎች መካከል ስትሆን ያገኙትን ምላሽ እንዲህ ስትል ገልፃልናለች።  « ከአንድም ሁለቴ ወደ ትምህርት ሚኒስቴር ሄደን ነበር። ከዛ እስካሁን እንደታገዛችሁት ታገሱ ነው ያሉን። በሁለተኛ ጊዜ ስንሄድ ደግሞ በትኑን ነው ያልናቸው። » የምትለው ፍሬ ዩንቨርስቲው እና የክልሉ መንግሥት ደብዳቤን ትምህርት ሚኒስቴር እንደሚሻ እንደተነገራቸው ትናገራለች።

ትምህርት ሚኒስቴር
ትምህርት ሚኒስቴር የዩንቨርስቲውን እና የአማራ ክልል መንግሥት ደብዳቤን እንደሚሻ እንደተነገራቸው ተማሪዎቹ ይናገራሉ ምስል Alemnew Mekonnen/DW

የባህርዳሩ ልዑክ

ኤርምያስ ደግሞ ተማሪዎችን ወክለው ወደ ባህር ዳር ከሄዱት አዲስ ተማሪዎች አንዱ ነው።  ያነጋገርነው ረቡዕ ዕለት ሲሆን ከዩኒቨርስቲው አገኘን የሚለው ምላሽ ተከታዩ ነው። « ቅሬታችንን አስገቡ ተብለን ቅሬታችንን አስገባን። ከእነሱ ምላሽ እየጠበቅን ነበር። ለዛሬ ምላሽ ተብለን ነበር። ዛሬ ደግሞ ሐሙስ እና ዓርብ ስብሰባ ስላለ ስብሰባው ላይ ነው ውሳኔ የሚሰጣችሁ ብለውን ዓርብን እየጠበቅን ነው።» ኤርሚያስ እንደሚለው ባህርዳር ዩኒቨርስቲ ገብተው መማር ሲኖርባቸው ትምህርት ያልጀመሩ ተማሪዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ናቸው። « የመጀመሪያ ዓመት እና የሪሚዲያል ተማሪዎች በድምሩ ወደ 5000 ገደማ ነን » በማለት የሪሚዲያል ተማሪዎችም እስካሁን ትምህርት እንዳልጀመሩ ይናገራል። 
ባህርዳር አቅራቢያ ነዋሪ የሆነው ኤርሚያስ ባህርዳር ዩኒቨርስቲ እስካሁን ያልጠራቸው ከፀጥታው ሁኔታ ጋር በተያያዘ እንደሆነ ርግጠኛ ነው። ግቢ ካሉ ተማሪዎችም ሰማሁ የሚለው ይህንን የሚያረጋግጥ ነው።  «የፀጥታ መደፍረሱ በግቢው ውስጥ ሁለት ጊዜ  ተስተውሏል። » ይላል።  « አንድ ጥር ላይ ነበር። ከዛ ደግሞ ዘንዘልማ ጋር ፍንዳታ ነበር። ዘንዘልማ ካምፓስ ተዘግቶ እንዳለ ነው። ሁለተኛ ደግሞ የጤና ተማሪዎች ጋር ተኩስ ተነስቶ ነበር። እነሱም ወደ ተለያዩ ቦታዎች እና ዋና ካምፓሱ ተበትነው ነበር። » ይላል።

የባህር ዳር ዩንቨርስቲስ « በትዕግስት ጠብቁ»

ተማሪዎቹን እስካሁን ያልተቀበለበትን ምክንያት የባህር ዳር ዩኒቨርስቲን ጠይቀን ነበር። በክልሉ በተራዘመው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት ስማቸው ተገልፆም ይሁን በድምፅ መረጃ ከመስጠት የተቆጠቡ አንድ የዩኒቨርስቲው ከፍተኛ ኃላፊ ተማሪዎቹ በትዕግስት እንዲጠብቁ ያሳስባሉ።  ይህ ምላሽ ግን ለተማሪዎቹ አጥጋቢ አይደለም። « ይህ ሰባት ወር ለጠበቀ ሰው ይህ መፍትሔ ሊሆን አይችልም» ይላል ስሙን መጥቀስ የማይፈልገው ወጣት።
በፀጥታው ችግር ምክንያት ሁለት የዩኒቨርስቲው ካምፓሶች መዘጋታቸውን ያረጋገጡልን የዩኒቨርስቲው ከፍተኛ ኃላፊ ምንም እንኳን የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች ጥሪ ደርሷቸው የነበረ ቢሆንም በሁለቱ ጊቢ ያሉ ተማሪዎች « በሰዓቱ ባሉ ታጣቂ ኃይሎች»  ተማሪዎቹ ግቢዎቹን እንዲለቁ መገደዳቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።  በመሆኑም ተማሪዎቹ ወደ ዋናው ግቢ በመሸጋገራቸው እና ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች በአሁኑ ወቅት በቂ ቦታ እንደሌለ ገልጸውልናል።  በተጨማሪም መንግሥት የፀጥታውን ሁኔታ ካረጋገጠ ዩኒቨርስቲው አሁንም ተማሪዎችን ተቀብሎ የማስተማር አቅም እንዳለው የሚናገሩት ኃላፊው ዩኒቨርሲቲው  ትምህርት ሚኒስቴር ተማሪዎችን በትኑልን ሊል እንደማይችልም ነው የሚያስረዱት ።  

 እቤት ተቀምጦ መጠባበቅ «ከፍተኛ የሥነ ልቦና ጫና አሳድሮብናል »

ከሶስት ሳምንት በፊት በባህር ዳር ከተማ ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ መካሄዱን የሚያውቁት አዲስ ገቢ ተማሪዎች የፀጥታ ሁኔታው ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ እንዳልሆነ እያወቁም እንኳን ጊቢ ገብተው መማር ይሻሉ። ምክንያቱን ሲገልጹም  እቤት ተቀምጦ መጠባበቅ «ከፍተኛ የሥነ ልቦና ጫና አሳድሮብናል » ነው ። « እንግዲህ በ2015 ተፈትነን እና 3% ከሚባሉት ተማሪዎች መካከል ሆነን ነው እቤት የተቀመጥን። ሰፈር ወይም እቤት ተቀምጠን ሥነ ልቦናዊ ጫና አለው። አምና ለምንድን ነው የለፋሁት የሚል ተፅዕኖ ይፈጥራል» ይላል ስሙን መግለፅ ያልፈለገው ተማሪ።  ይህም ድባቴ ውስጥ እንደከተታቸው ይናገራል። ወጣቱ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያው ምርጫው አልነበረም። እሱ እንደሚለው እሱ ይማርበት ከነበረው ትምህርት ቤት 12 ተማሪዎች ያለፉ ሲሆን ሁሉም ተማሪዎች የደረሳቸው ባህርዳር ነው። « እንግዲህ 3% በሚያልፍበት ጊዜ እንኳን ምርጫችን አልታየም። ይህ በጣም የሚያሳዝን ነው» በማለት ያማርራል። 

የአማራ ክልል ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎች ሥጋትና አቤቱታ

ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቀው ትምህርት ሚኒስቴር የተማሪዎቹን ቅሬታ በተመለከተ መፍትሄ ከማመላከት ወደ ዩኒቨርስቲው ነው የመራን።  ይህ ዝግጅት እስከተጠናከረበት እስካለፈው ረቡዕ ድረስ በትዕግስት ይጠብቁ ከሚል ምላሽ በስተቀር ድረስ በተማሪዎቹ እጣ ፈንታ ላይ አልተወሰነም።

ልደት አበበ 

ታምራት ዲንሳ