የቀጠለው የቡሩንዲ ቀውስ | አፍሪቃ | DW | 14.05.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የቀጠለው የቡሩንዲ ቀውስ

በቡሩንዲ አንዳንድ የጦር ኃይሉ አባላት እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ግንቦት 13፣ ቀን 2015 ዓ.ም. ፕሬዚደንት ፒየር ንኩሩንዚዛን ከስልጣን ለማፈናቀል ሙከራ ካደረጉ ትናንት ልክ አንድ ዓመት አለፈ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:05

የቡሩንዲ ቀውስ

የመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ የተካሄደው ፕሬዚደንት ንኩሩንዚዛ ሕገ መንግሥቱን በመጣስ ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን እንደገና ለመወዳደር እቅዳቸውን ካሳወቁ እና በሰበቡም በሀገሪቱ ብርቱ ተቃውሞ ከተነሳ በኋላ ነው። ይሁን እንጂ፣ የፕሬዚደንት ንኩሩንዚዛ ታማኝ ወታደሮች እንደሚታወሰው መፈንቅለ መንግሥት ሙከራውን አክሽፈውታል።
የመፈንቅለ መንግሥቱን ሙከራ በተከተለው አንድ ዓመት በመላ ቡሩንዲ፣ በተለይ በመዲናይቱ ቡጁምቡራ ሁከት እና ግጭቱ ቀጥሎዋል፣ መንግሥትም ተቃዋሚ በሚላቸው ላይ የጭቆና ርምጃውን በማጠናከር የመብት ጥሰቱን ማስፋፋቱን በፕሪቶርያ፣ ደቡብ አፍሪቃ የሚገኘው ዓለም አቀፍ የፀጥታ ጥናት ተቋም የፖለቲካ ተንታን ዮላንድ ቡካ አመልክተዋል።

Burundi Proteste gegen Präsident Nkurunziza

ተቃውሞ በቡጁምቡራ

« የመፈንቅለ መንግሥቱን ሙከራ ካስከተላቸው መዘዞች እና የመንግሥት ምላሽ መካከል ዋነኛው ነፃ የመገናኛ ብዙኃን መዘጋት ሲሆን፣ በሰበቡም በመላይቱ ሀገር ሕዝቡ ለመንግሥቱ የማይመች፣ ማለትም፣ ትችት አዘል ዜና እንዳያገኝ አድርጎታል። » የቡሩንዲ መንግሥት በጋዜጠኞች እና ተችት በሚያቀርቡ ወገኖች ላይ መውሰድ የቀጠለው የኃይል ርምጃ የፕሬዚደንት ንኩሩንዚዛን ፖለቲካ የሚቃወሙ በርካታ ዜጎች ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ አስገድዶዋል። መሰደድ ከተገደዱት የቡሩንዲ ዜጎች መካከል አንዲት ለደህንነቷ በመስጋት ስሟ እንዲገለጽ ያልፈለገች ጋዜጠኛ በምህፃሩ «ኤርፔአ» ወይም «ራድዮ ፒውብሊክ አፍሪኬን» በመባል ለሚታወቀው ነፃው ራድዮ ጣቢያ ትሰራ ነበር። ይኸው የራድዮ ጣቢያም ነበር ስለመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ የመጀመሪያውን ዜና ያሰራጨው። ዜናው እንደተላለፈ ብዙም ሳይቆይ ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች የራድዮ ጣቢያውን በእሳት አጋይተው እንዳወደሙት እና በዚያን ወቅት ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገር ለቃ ለመሸሽ ማሰቧን ጋዜጠኛዋ ታስታውሳለች።

« ከዚህ ክስተት በኋላ ሂደቶች መፋጠን ነበረባቸው። በአንድ ምሽት ነበር እንዴት ሀገር ለቅቄ መውጣት እንደምችል ያቀድኩት። ስለእቅዴ የሚያውቁት ሶስት የቤተሰቤ አባላት ብቻ ነበሩ። የቤት ሰራተኞቼ እንዳይጠረጥሩ በሚልም ከቤት አንድ ትንሽ ቦርሳ ብቻ ይዤ ነበር የወጣሁት። »

ሕጋዊ ባልሆነው የፕሬዚደንቱ ድጋሚ መመረጥ ሰበብ ውዝግብ ከተፈጠረ ወዲህ ከ250,000 የሚበልጥ የቡሩንዲ ዜጋ ሀገሩን ለቆ መሰደድ ተገዶዋል። ውዝግቡ ከተቀሰቀሰ አንስቶ ፕሬዚደንት ንኩሩንዚዛ ተቀናቃኞቻቸውን መፈናፈኛ እንዳሳጡዋቸው ይገኛሉ። የከሸፈውን መፈንቅለ መንግሥት ጠንስሰዋል በሚል ክስ ከቀረበባቸው 28 ሰዎች መካከል 21 ሰዎች ከጥቂት ቀናት በፊት ለሁለተኛ ጊዜ በከፍተኛው ፍርድ ቤት ፊት ቀርበው ዕድሜ ይፍታህ ተፈርዶባቸዋል፣ ፍርድ ቤቱ በተከሳሾች ላይ መጀመሪያ የተሰጠው ብይን ቀለል ያለ ሆኖ ያገኘው ዓቃቤ ሕግ ያቀረበለትን የይግባኝ ማመልከቻ ከተመለከተ በኋላ ነበር ይህንን ብይን ያስተላለፈው። አምስቱ ተከሳሾች እስከ ሁለት ዓመት እስራት ሲበየንባቸው፣ ሌሎች ሁለት በነፃ ተለቀዋል። የእስራት ቅጣት ከተፈረደባቸው መካከል ከፍተኛ የቀድሞ የጦር መኮንኖችም የሚገኙባቸው ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ 3,4 ሚልዮን ዩሮ መቀጫ እንዲከፍሉም በይኖባቸዋል። ይኸው ገንዘብ በመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ ወቅት ሰለባ ለሆኑ ሰዎች ቤተሰቦች እንዲሰጥ ፍርድ ቤቱ ወስኖዋል።

Onesime Nduwimana

ኦኔሲም ንዱዊማና

የቡሩንዲ መንግሥት የመፈንቅለ መንግሥቱን ሙከራ አሲረዋል በተባሉት ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ከነርሱ ጋር ግንኙነት ነበራቸው በተባሉ የተቃዋሚ ቡድኖች አባላትም ላይ ጭምር ከባድ ርምጃ በመውሰድ ላይ መሆኑን ነው የፕሪቶርያ ዓለም አቀፍ የፀጥታ ጥናት ተቋም የፖለቲካ ተንታኝ ዮላንድ ቡካ የሚያስረዱት። እንደ ዮላንድ ቡካ አስተያየት፣ ፕሬዚደንት ንኩሩንዚዛ ውዝግቡን ለማብቃት ከተቀናቃኞቻቸው ጋር ገላጋይ ሀሳብ ለመድረስ ዝግጁነቱ ተጓድሏቸው ይገኛሉ።

« የምሥራቅ አፍሪቃ ማህበረሰብ በቡሩንዲ መንግሥት ተቃዋሚዎች እና በገዢው ፓርቲ መካከል ውይይት እንዲካሄድ ያደረገውን ጥረት ስናስብ፣ ሁኔታው ፈታኝ መሆኑን እንመለከታለን። ይህ አሁን የተላለፈው ብይን መንግሥት በአንፃሩ ቆመዋል ብሎ ከሚያስባቸው ሰዎች ጋር ለመወያየት ፈቃደኛ አለመሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። »

ፕሬዚደንት ንኩሩንዚዛ ከማን ጋር እንደሚደራደሩ ራሳቸው መወሰን ስለሚፈልጉ፣ እስከዛሬ ድረስ በመንግሥት እና በተቃዋሚዎች መካከል ድርድር ሊካሄድ አልቻለም።

ይህ በዚህ እንዳለ፣ ፕሬዚደንት ፒየር ንኩሩንዚዛ ራሳቸውን እርቀ ሰላም አራማጅ አድርገው ማቅረብ ይዘዋል። ባለፈው ሰኞ በትዊተር በጻፉዋቸው መልዕክቶች በአሁኑ ጊዜ የሚታዩ ችግሮች ያለፈውን አስከፊ ታሪክ ሊያስረሱ እንደማይገባ አሳስበዋል። ፕሬዚደንቱ እንደጻፉት፣ የአሁኑን ቀውስ የቀሰቀሱት ለእርቀ ሰላም አስፈላጊ የሆነውን ሀቁን ለማፈን የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው። እንደሚታወሰው፣ ቡሩንዲ ውስጥ ከ40 ዓመት በላይ በፊት የቱትሲ ጎሳ አባላት በሁቱ ጎሳ ላይ ዘግናኝ ጭፍጨፋ ፈፅመዋል። በሁቱ እና በቱትሲ ጎሳዎች መካከል በተካሄደ ውዝግብ ከ300,000 የሚበልጥ ሰው ሕይወቱን አጥቶዋል። ምንም እንኳን ታዛቢዎች ሀገሪቱ አሁን የምትገኝበትን ቀውስ እንደ ፖለቲካዊ እንጂ እንደ ጎሳ ውዝግብ ባያዩትም፣ የፕሬዚደንቱ የሰሞኑ ትዊተር መልዕክት አዲስ ግጭት ሊነሳ ይችላል የሚል ዛቻ ያዘለ አድርገው ተመልክተውታል።
የቀድሞው የፕሬዚደንት ንኩሩንዚዛ ቃል አቀባይ የነበሩት ፣ አሁን የተቃዋሚውን ቡድን አባል የሆኑት ኦኔሲም ንዱዊማና ፕሬዚደንቱ ለእረቀ ሰላም የሚያቀርቡትን ጥሪ የምር አድርገው እንደማይመለከቱት አስታውቀዋል። ኦኒኔሲም እንንደሚሉት፣ ራሳቸው የሁቱ ተወላጅ የሆኑት ንኩሩንዚዛ በእውነት ለሁቱ ጎሳ አሳቢ ከሆኑ ፣ የተለያዩት ጎሳዎች እጎአ በ2000 ዓም በአሩሻ ታንዛንያ የደረሱትን ዓይነት ገላጋይ ሀሳብ መቀበል ባልገደዳቸው ነበር።

Leonidas Hatungimana

ሌዎኒዳ ሀቱንጊማናም

ረጅሙን የርስበርስ ጦርነት ፍፃሜ ባስገኘው ውል ላይ ተቀናቃኞቹ ወገኖች ከደረሱት ስምምነት መካከል ፕሬዚደንቱ ሁለት የስልጣን ዘመን ብቻ እንዲያገለግል የሚልም ስለሚገኝበት ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን በመወዳደራቸው እና በመመረጣቸው ስምምነቱን እንደጣሱ ነው ኦኔሲም ያስታወቁት።

« በዚህም ንኩሩንዚዛ ሕገ መንግሥቱን የጣሱት ራሳቸው በመሆናቸው ከሳቸው የበለጠ ሌላ የመፈንቅለ መንግሥት አራማጅ የለም። እና የቡሩንዲ ዜጎች በአሩሻ የደረሱት ገላጋይ ሀሳብ በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ነው። ስለዚህ ሕግ የጣሱት ንኩሩንዚዛ እና ተከታዮቻቸው ስለሆኑ፣ እኛ ነን ካላንዳች ድርድር ከስልጣን ውረዱ ብለን መጠየቅ የነበረብን። »
ሁኔታዎች ይህን በመሰሉበት በዚሁ ጊዜ ሀገሪቱን ከምትገንበት የቀውስ ሁኔታ ለማውጣት ፕሬዚደንቱ ምን አማራጭ አላቸው በሚል የሚጠይቁ ብዙዎች ሲሆኑ፣ ሌላው የቀድሞ የፕሬዚደንት ንኩሩንዚዛ ቃል አቀባይ ሌዎኒዳ ሀቱንጊማናም የፕሬዚደንቱ ተፅዕኖ ምን ያህል ነው በሚል ማጠያየቃቸው አልቀረም።

« ሁለት ዓበይት ችግሮች አሉ። የመጀመሪያው ችግር ራሳቸው ናቸው። አሁን ወደኋላ ልመለስ ካሉ የሚጠብቃቸው እስር ቤት ነው። ሁለተኛው ችግር ደግሞ በአሁኑ ጊዜ ሊቆጣጠሩት የማይችሉት አንድ ቡድን በዙርያቸው አቋቁመዋል። የዚሁ ቡድን አባላት የፕሬዚደንቱ ወዳጆችም ጠላቶችም ናቸው። »

በሌላ አነጋገር፣ ንኩሩንዚዛ ለራሳቸው ሲሉ አሁን መከተል በያዙት ፖሊሲ ከመቀጠል አልፈው ሌላ መንገድ ሊከተሉ አይችሉም። በዚህም የተነሳ ከተቃዋሚዎች ጋር ድርድሩ ወደፊት መራመድ ተስኖታል። ታዛቢዎች እንደሚሉትም፣ ከአንድ ዓመትም በኋላ ቡሩንዲ የምትገኝበት ቀውስ የሚያበቃበት ሁኔታ ይበልጡን እየራቀ ነው።

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic