1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሁለቱወገኖች የስልጣን ሽኩቻ ወዴት ያመራ ይሁን?

እሑድ፣ ግንቦት 4 2016

በትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደርና በህወሐት መካከል ያለው የስላጣን ሽኩቻ ተካሮ አንዱ በአንዱ ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻው በግላጭ እየተካሄደ ከመሆኑም አልፎ ጎራ ለይተው እስከመገዳደል እንዳይደረስና የተገኘው አንጻራዊ ሰላም እንዳይደፈርስ ብዙዎቹ የክልሉ ነዋሪዎች ስጋታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።

https://p.dw.com/p/4fhUs
የትግራይ ክልል ጊዚያዊ መስተዳደር ፕረዚደንት አቶ ጌታቸው ረዳ
የትግራይ ክልል ጊዚያዊ መስተዳደር ፕረዚደንት አቶ ጌታቸው ረዳምስል DW/Y. Geberegeziabeher

የስልጣን ሽኩቻ

በፌደራል መንግስትና በትግራይ ሃይሎች መካከል ሲካሄድ የነበረ ደም አፋሳሽ ውግያ ሚልዮኖችን ለሞት፣ ለስደትና መፈናቀል ከዳረገ በኋላ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት አንጻራዊ ሰላም ቢገኝም በትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደርና በህወሀት አመራሮች መካከል እየተካረረ ያለው የስልጣን ሽኩቻ የተፈጠረውን ሰላም እንዳያደፈርሰው ብዙዎችን አስግቷል።

የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ገና ከምስረታው የመንግስትና የፓርቲ ስራዎች ተለያይተው  መሰራት አለባቸው የሚል አቋም የተወሰደ ቢሆንም፤ በህወሐት በኩል ግን ጊዚያዊ መንግስቱ መዋቅሩ እስከቀበሌ ድረስ ዘርግቶ በስምምነቱ መሰረት መተግበር ያለባቸውን ስራዎች እንዳያከናውን እንቅፋት እየሆነ እንደሆነ በስፋት ይነገራል።

ሕወሐት ጊዚያዊ አስተዳደሩን ለመቆጣጠር ያስችለኛል ያለውን "የጋራ ኮሞቴ" በሚል ሰበብ፤ ኮሚቴ አዋቅሮ ከስልጣንና ሃላፊነቱ ውጭ የጊዚያዊ አስተዳደሩን ለመዘወር ይንቀሳቀሳል፤ የጊዚያዊ አስተዳደሩ የሥራ ሃላፊዎችን የብልጽግና "ባንዳዎች" የሚልና ሌሎች ፍረጃዎችን በመጠቀም የስም ማጥፋት ዘመቻ ያደርጋል፤ ጊዚያዊ የመማክርት ጉባኤ እንዳይመሰረት አሁንም "የብልጽግና" መዋቅር ሊጭንብን ነው በሚል የመማክርት ጉባኤውእስከአሁን እንዳይመሰረት አድርጓል የሚሉና ሌሎች ወቀሳዎች ይሰነዘሩበታል።

በጊዚያዊ አስተዳደሩ በኩልም ግልጽ የሆነ የስራ ፍኖተ ካርታ አለመኖር፤ መንግስትና ፓርቲ መለያየት አለባቸው ብሎ ሲያበቃ በተግባር አለመፈጸም፤ የእርዳታ እህልን ጨምሮ በቢልዮን የሚቆጠር ገንዘብና ንብረት የዘረፉና ያዘረፉ ባለስልጣናት፤ እንዲሁም የተለያዩ ፖለቲከኞችና ሙስናን ያጋለጡ ግለሰቦች የሚገድሉ በዘፈቀደ የሚያስሩ ባለስልጣናትን አጣርቶ ለፍርድ አለማቅረብ፤ የጸጥታና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን አለመፍታት የሚሉና ሌሎች በርካታ ትችቶች እየተሰነዘሩበት ይገኛል።

በትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደርና በህወሐት መካከል ያለውየስላጣን ሽኩቻ ተካሮ አንዱ በአንዱ ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻው በግላጭ እየተካሄደ ከመሆኑም አልፎ ጎራ ለይተው እስከመገዳደል እንዳይደረስና የተገኘው አንጻራዊ ሰላም እንዳይደፈርስ ብዙዎቹ የክልሉ ነዋሪዎች ስጋታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ። የሁለቱወገኖች የስልጣን ሽኩቻ ወዴት ያመራ ይሁን የዛሬ የእንወያይ ዝግጅታችን ትኩረት ነው።

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር