1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሴቶችን ቀን እያሰብን ለሴቶች ምን ተደርጓል?

ማክሰኞ፣ መጋቢት 3 2016

የተመድ በጎርጎሪዮሳዊው 2030 ዓ,ም ሊያሳካ ካቀዳቸው ዘላቂ የልማት ግቦች አንዱ የሴቶችን መብቶች በማክበር ኑሯቸው ማሻሻልን ይመለከታል። ሆኖም የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉተሬሽ እንደተናገሩት ከ340 ሚሊየን በላይ አዋቂና አዳጊ ሴቶች እጅግ በከፋ ድህነት ኑሯቸውን ይገፋሉ። «የሴቶችን ቀን እያሰብን በተግባር ለሴቶች ምን ተደርጓል?»

https://p.dw.com/p/4dQYa
ፎቶ ከማኅደር፤ የፍትህ ተምሳሌት
በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ዘርፈ ብዙ ጥቃቶች የሁሉንም ወገን ትኩረት እንደሚሹ ነው የአፍሪቃ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማማት ያስተላለፉት መልእክት አጽንኦት የሰጠው። ፎቶ ከማኅደር፤ የፍትህ ተምሳሌትምስል Ute Grabowsky/photothek/picture alliance

የሴቶችን ቀን እያሰብን ለሴቶች ምን ተደርጓል?

 

«ውድ እህቶች፤ የጊዜ ዑደት በየዓመቱ፤ በዓለም አቀፍ እና በተለይም ደግሞ በአፍሪቃ የጋራ ትውስታ ውስጥ ሊቀማ የማይገባውን የሴቶችን መብት ለማስመለስ ያለውን ውጣ ውረድ ለማስተካከል ተምሳሌታዊ ወደሆነው ማርች ስምንት ይመልሰናል። የሴቶች ቀን የመታሰቡ ዋና አላማ ይህ ነው። ለመሆኑ በጊዜ ሂደት ይህን ወሳኝ ግብ ለማሳካት የማያቋርጥ እንድገት አሳይተናል? ከትናንቱስ ዛሬ ወደ ግባችን ቀርበን ይሆን? ይህን እጠራጠራለሁ።»

ባለፈው ሳምንት ዓርብ ዕለት የታሰበውን የዓለም የሴቶች ቀን ምክንያት በማድረግ የአፍሪቃ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማማት በጽሑፍ ያስተላለፉት፤ መልዕክት ነው።  የዘንድሮው የዓለም የሴቶች ቀን መሪ ቃል «በሴቶች ላይ መሥራት እድገትን ያፋጥናል» የሚል ነው። 

የሴቶች መብቶች ስኬትና ጥያቄ

የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ በዘንድሮው የዓለም የሴቶች ቀን መልእክታቸው በመላው ዓለም የሚገኙ አዋቂ እና አዳጊ ሴቶች ለእኩልነት ባደረጉት ትግል ለስኬቶቻቸው አድናቆታቸውን ገልጸዋል። ሴቶች ፍትህና እኩልነት የሰፈነባትን ዓለም ለመፍጠር በጾታቸው ምክንያት ያሉ መሰናክሎችን በመናድ፤ ዘልማዳዊ አመለካከቶችንም በመበታተን ቀላል የማይባል እርምጃዎችን ወስደዋል ያሉት ጉተሬሽ አሁንም ግን እጅግ ብዙ እንቅፋቶች መኖራቸውን አጽንኦት ሰጥተዋል። ዛሬም በቢሊየኖች የሚቆጠሩ አዋቂ እና አዳጊ ሴቶች መገለል፤ ኢፍትሃዊነትና ተጽዕኖዎች እየደረሱባቸው መሆኑንም አመልክተዋል። ከዚህ ላይ ደግሞ ሰብአዊነታቸውን ዝቅ ለሚያደርግ ዘርፈ ብዙ ጥቃት መጋለጣቸውንም አመልክተዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ ምንም እንኳን ስኬቶች መኖራቸውን ቢያበረታቱም አሁንም የሴቶችን ሰብአዊ መብቶች በአግባቡ ለማስከበር የሚደረገው ጥረት ከባድ ጫና እያጋጠመው መሆኑን ዘርዝረዋል። የአፍሪቃ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት በመልእክታቸው የሴቶችን መብት ለማስከበር የታሰበውን ያህል እስከ ዛሬ ማሳካት የመቻሉ ነገር እንዳጠራጠራቸው ያመለከቱበትን ምንክንያት ሲገልጹ የታወቀና እና የተለመደ እንደሆነ ገልጸዋል። በክፍለ ዓለም አፍሪቃ በተለያዩ አካባቢዎች ምን እየተካሄደ እንደሆነ በመጠየቅም፤ በግጭት ጦርነቶች መካከል አዋቂና አዳጊ ሴቶች የጥቃት ሰለባዎች መሆናቸው መቀጠሉን አመልክተዋል። እናቶች፤ ሚስቶች እህቶች እና ሴት ልጆች አብዛኛውን ጊዜ የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንዳያገኙ እንደሚደረጉ፤ ከዚያም አልፎ በገዛ አካላቸው ላይ እንኳ መብት እንደሌላቸው ገልጸዋል። ከዚህ ማሳያዎች አንዱ የሆነው የሴት ልጅ ግርዛትን በተመለከተ የተመ የሕጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ በዕለቱ ያወጣው መረጃ ከ230 ሚሊየን በላይ ሴቶች በስነተዋልዶ ጤናቸው ላይ ከፍተኛ ችግር ለሚያስከትለው የሴት ልጅ ግርዛት መዳረጋቸውን አመልክቷል። እንደ ዘገባው ባለፉት ስምንት ዓመታት ብቻ 30 ሚሊየን የሚሆኑት አሰቃቂ የሚባለው የግርዛት አይነት ተፈጽሞባቸዋል። ምንም እንኳን ይህ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት እንዲቆም የሚደረገው ጥረት በአንዳንድ ሃገራት ለውጥ ቢያመጣም በአብዛኛው ግን አሁንም ድርጊቱ እየተፈጸመ እንደሆነም ገልጿል። የሴት ልጅ ግርዛት በብዛት ከሚፈጸምባቸው ሃገራትም ኢትዮጵያ፣ናይጀሪያ እና ሱዳን ዋናዎቹ ሲሆኑ ቡርኪናፋሶ ትርጉም ያለው ለውጥ ከታየባቸው ሃገራት ቀዳሚዋ እንደሆነች ነው ጥናቱ ያሳየው።

ፎቶ ከማኅደር፤ የዩኒሴፍ አርማ
የተመ የሕጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ በዕለቱ ያወጣው መረጃ ከ230 ሚሊየን በላይ ሴቶች በስነተዋልዶ ጤናቸው ላይ ከፍተኛ ችግር ለሚያስከትለው የሴት ልጅ ግርዛት መዳረጋቸውን አመልክቷል። ፎቶ ከማኅደር፤ የዩኒሴፍ አርማ ምስል Denis Balibouse/REUTERS

ስለሴቶች እኩልነት የሚነገረውና እውነታው

ሴቶች የመማር ሆነ የተማሩትም በሙያቸው የሥራና ኃላፊነት ዕድሉን ቢያገኙ በተሰማሩበት ውጤታማ እንደሚሆኑ ብዙዎች ያምናሉ ይናገራሉ። እንዲያም ሆኖ ግን አሁንም ሴቶች ለሚገኙበት ማኅበረሰብ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዳያደርጉ ሁኔታዎች አልተመቻቹላቸውም የሚሉ ጥቂት አይደሉም። ከዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ሴቶች በትላልቅ የመንግሥት ኃላፊነት ቦታዎች ላይ መመደባቸው አንድ ሰሞን በምሳሌነት ይጠቀስ ነበር። የተሾሙት ሴት ባለሥልጣናት ምን ያህል የሚጠየቀስ አስተዋጽኦ አበረከቱ? አሁንስ የት ደረሱ? በዚህ ረገድ የሚወራው እና እውነታው እንዴት ይመዘናል? በሚል ካነጋገርናቸው አንዷ ጋዜጠኛ ጽጌ አይናለም የሴቶችን መብት በተመለከተ ካስተዋለችው በመነሳት ኢትዮጵያ ውስጥ «ይሰጣል፤ ይነፈጋልም» ትላለች። 

ሴቶች የሚገባቸውን እንዲያገኙ መደረጉ እንደችሮታ በሚታይበት ማኅበረሰብ ውስጥ በርካታ መሰናክሎች ታልፈው ዕድሎቹ ሲመቻቹ አቅሙ እያላቸው የማይጠቀሙበት መኖራቸውም ሌላቸው አሳሳቢ ጉዳይ እንደሆነም ነው ጋዜጠኛዋ የምትናገረው። ስለሴቶች መብት ሲታሰብ የአካል ጉዳተኛ ሴቶች ጉዳያቸው እንዴት ይታይ ይሆን ያልናት ዐይነ ስውርነት እንቅፋት ሳይሆንባት በኮሌጅ መምህርትነት በማገልገል ላይ የምትገኘው ለወየሁ አየለ፤ ከጾታ ጋር በተያያዘ ያለው ተጽዕኖ ያው መሆኑን በማመልከት ሥራው ያለው ጭንቅላት ላይ ነው ትላለች። በተለያዩ ጊዜያት ሴቶች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት አስተማሪ ሊባል የሚችል ተመጣጣኝ ቅጣት ስለማይወሰንበት ጥቃቱም ጥፋቱም መደጋገሙን ስለሴቶች መብት መከበር የሚሟገቱ ወገኖች ይገልጻሉ። በግጭት ጦርነት አካባቢዎች ለጾታዊ ጥቃት በተለይም ተገድዶ ለመደፈር የተዳረጉ እህቶች እና እናቶች ፍትህ እንደሚያስፈልጋቸው በየጊዜው እየተጠየቀ ነው።

በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል የአድቮኬሲ እና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዋ ሃና ላሌ ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ድርጅቶች እና ተቋማት አማካኝነት የሴቶችን መብቶች ለማስከበር የሚደረጉ ጥረቶች ቢኖሩም በቂ እንዳልሆኑ አስተውላለች። በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል የሚሠራው የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ላይ በማተኮር ነው። የሴቶችን መብቶች አንስተው በሚሟገቱበት ሂደት በተለይም የጾታ ጥቃቶችን የሚመለከቱ መረጃዎች ጋር በተያያዘ ጫና እንደሚደርስባቸው ነው የምትገልጸው። 

በይፋ የማይነገረው ሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ተምሳሌታዊ መግለጫ
በይፋ የማይነገረው ሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ተምሳሌታዊ መግለጫምስል picture-alliance/Pacific Press/E. McGregor

ትኩረት የሚሻው ዘርፈ ብዙ ጥቃት 

በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ዘርፈ ብዙ ጥቃቶች የሁሉንም ወገን ትኩረት እንደሚሹ ነው የአፍሪቃ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማማት ያስተላለፉት መልእክት አጽንኦት የሰጠው። በተለይም በይፋ የማይነገረው ቢነገርም ተገቢው ፍትህ የተነፈገው በገጠርም ሆነ በከተማ እንዲሁም በግጭት አካባቢዎች የሚፈጸመው አስገድዶ የመድፈር ወንጀል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት። እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን አደባባይ አውጥተው ለሚሞግቱ እና የጥቃት ሰለባዎች ፍትህም ሆነ ተገቢውን የሕግ ከለላ እንዲያገኙ ጥረት ለሚያደርጉ በርካታ ሴቶችም አድናቆታቸውን ገልጸዋል። 

የዘንድሮው የሴቶች ቀን መሪ ቃልም «በሴቶች ላይ መሥራት እድገትን ያፋጥናል» የሚል እንደመሆኑ በማጀትም ሆነ በአደባባይ ሚናቸውን በጣምራ ለማከናወናቸው ለምሳሌነት የሚጠቀሱትም ጥቂት አይደሉም። ሴቶችን በየደረጃው ለየዘርፉ ብቁ ለማድረግ ወጣቶች ሴቶች ላይ መሥራት ይገባል ባይ ናት ጋዜጠኛ ጽጌ። እሷ እንደምትለውም ሥራው ከቤተሰብ ይጀምራል።

ስለሴቶች መብቶች መከበር የሚነገርባቸው መድረኮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ መጥተዋል። ዛሬም ግን ለጾታዊ ጥቃት የተጋለጡ ቁጥራቸው እየጨመረ እንጂ ሲቀንስ አይታይም። በኅብረተሰቡ ውስጥ እናት፣ እህት ብሎም ልጅ የሆኑት ሴቶች ተገቢው ሰብአዊ መብቶቻቸው ተከብረው፤ ባላቸው የትምህርት ደረጃና እውቀት የበኩላቸውን ለማኅበረሰቡ እንዲያበረክቱ እንቅፋቶችን የማስወገዱ ጥረት ግን የሌሎችን ብቻ ሳይሆን የእራሳቸው የሴቶችንም ጠንካራ ተሳትፎ ይጠይቃል።

 ሸዋዬ ለገሠ 

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር