1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሲቪክ ድርጅቶች ስለ የሽግግር ፍትሕ ረቂቅ ፖሊሲ

ሰኞ፣ መጋቢት 2 2016

በአሁኑ ወቅት በርካታ የአገሪቱ ክፍሎች በማያባራ ግጭት ውስጥ መሆናቸውን የጠቀሱት ድርጅቶቹ መንግሥት ሕግና ሥርዓት የማስከበር ግዴታውን በአግባቡ ካልተወጣ በስተቀር የሽግግር ፍትሕን ተግባራዊ ለማድረግ በጣም አዳጋች እንደሚሆን አመላክተዋል፡፡ቀውሱ ለሽግግር ፍትሕ አፈጻጸምም እንቅፋት እንዳይሆኑ፣ መንግሥት የሕግ የበላይነትን እንዲያረጋግጥ ጠይቀዋል።

https://p.dw.com/p/4dODo
ስለ ሽግግር ፍትህ ረቂቅ ፖሊሊ በአዲስ አበባ የተካሄደ ምክክር
ስለ ሽግግር ፍትህ ረቂቅ ፖሊሊ በአዲስ አበባ የተካሄደ ምክክር ምስል Solomon Muche/DW

የሲቪክ ድርጅቶች ስለ የሽግግር ፍትሕ ረቂቅ ፖሊሲ

በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ወቅት በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና የጦር ወንጀል ተሳትፎ ነበራቸው የተባሉ የኤርትራ ወታደሮች ፣ በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ በሚቋቋመው ልዩ ፍርድ ቤት ጉዳያቸው ሊታይ እና ተጠያቂነትም ሊረጋገጥ ይገባል ሲሉ ስምንት የመብት ጉዳይ ላይ የሚሰሩ ሲቪክ ድርጅቶች ጠየቁ። የመብት ድርጅቶቹ የኤርትራ ወታደሮች በእነዚህ ወንጀሎች ተሳትፎ እንደነበራቸው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ማረጋገጣቸውን ጠቅሰው "የኤርትራ ወታደሮች ጉዳይ በሌሉበትም ቢሆን በሚቋቋመው ልዩ ፍርድ ቤት ሊታይ እና ተጠያቂነታቸውም ሊረጋገጥ፣ በእውነት አፈላላጊ ኮሚሽኑ አማካኝነትም በነዚሁ የውጭ ኃይሎች የተፈፀሙ ከባድ ወንጀሎች ይፋ ሊደረጉ፣ እውነቱ ሊታወቅ እና ሊሰነድ ይገባል።" ብለዋል።

በጦርነቱ የተሳተፉ የኤርትራ ወታደሮች ጉዳይ

ሰሜን ኢትዮጵያን በብርቱ ጎድቶ ባለፈው ጦርነት በውጭ ኃይሎች የተፈጸሙ ከባድ ወንጀሎች ይፋ ሊደረጉ፣ እውነቱ ሊታወቅና ሊሰነድ ይገባል ያሉት በመብት ዙሪያ የሚሠሩት ስምንት ድርጅቶች ይፀድቃል ተብሎ የሚጠበቀው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የሚያቋቁመው ልዩ ፍርድ ቤት ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ የጦር ወንጀሎችን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ወንጀሎችንና ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመዳኘት ዕውቀትና ልምድ ያላቸው የውጭ አገር ባለሙያዎች በዳኝነት ቢመደቡ ለፍትሕ ሒደቱ ቅቡልነት፣ ለውሳኔዎች ጥራት፣ ለዕውቀት ሽግግርና በዘርፉ ለሥነ ሕግ ዕድገት ተመራጭ እንደሚሆን አመልክተዋል።የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አርቃቂ ባለሙያዎች ምን እየሠሩ ይኾን ?

ባለ ስምንት ገጽ ጥያቄውን ለፍትሕ ሚኒስቴር ካስገቡት ድርጅቶች መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃይለማርያም።

"የሌላ ሀገር መንግሥት በአንድ ሀገር ውስጥ ገብቶ ያውም በዓለም አቀፍ ወንጀል የሚያስጠይቁ የጦር ወንጀሎች ፣ በሰው ስብዕና ላይ ያነጣጠሩ ወንጀሎች እስከተፈፀመ ድረስ በተቻለ መጠን የዚህ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው መብታቸው የተጣሰባቸው አካላት ፍትሕ ማጣት ስለሌለባቸው እነዚህ ሰዎች ፍትሕ እንዲያገኙ መደረግ አለበት"

ረቂቅ ፖሊሲው በቂ ውይይት እንዲደረግበት መጠየቁ

የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ሰነዱ ለሕዝብ ይፋ ተደርጎ ውይይትና ትችት እንዳልቀረበበት፣ ረቂቅ ፖሊሲውን በሚመለከት ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና ለጋሾች ጋር ከተደረጉ አጫጭር ውይይቶች በስተቀር በቂ ውይይት አለመደሩጉን የገለፁት ስምንቱ ሲቪክ ድርጅቶች ረቂቅ ፖሊሲው ከመፅደቁ በፊት፣ ለሕዝብ ይፋ ተደርጎ ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን፣ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ጨምሮ በሌሎችም ሰፊ ውይይት እንዲደረግበት ጠይቀዋል።

ስለ ሽግግር ፍትህ ረቂቅ ፖሊሲ የተካሄደ የምክክር መርሀ ግብር
ስለ ሽግግር ፍትህ ረቂቅ ፖሊሲ የተካሄደ የምክክር መርሀ ግብር ምስል Solomon Muche/DW

 

የፀጥታ ችግር የፖሊሲውን ግብ እንዳይጎዳ ሥጋት መፍጠሩ

 

በአሁኑ ወቅት በርካታ የአገሪቱ ክፍሎች በማያባራ ግጭት ውስጥ መሆናቸውን የጠቀሱት ድርጅቶቹ መንግሥት ሕግና ሥርዓት የማስከበር ግዴታውን በአግባቡ ካልተወጣ በስተቀር፣ የሽግግር ፍትሕን ተግባራዊ ለማድረግ በጣም አዳጋች እንደሚሆን አመላክተዋል፡፡ቀውሱ ለሽግግር ፍትሕ አፈጻጸምም እንቅፋት እንዳይሆኑ፣ መንግሥት የሕግ የበላይነትን እንዲያረጋግጥ ጠይቀዋል።ኢትዮጵያ ለሽግግር ፍትህ ዝግጁ ነች?

"በኦሮሚያ ዜጎች በታጠቁ ኃይሎች ሲታገቱ፣ ሲገደሉና ደብዛቸው ሲጠፋ መንግሥት በተጨባጭ በቂ ዕርምጃ ሲወስድ አለመታየቱ፣ በአማራ ክልል በበርካታ ቦታዎች ታጣቂ ኃይሎች በሚፈጽሙት የሽምቅ ጥቃት፣ በግልፍተኝነት በሲቪሉ ሕዝብ ላይ ጅምላ የበቀል ዕርምጃ የወሰዱ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ በተጨባጭ ተጠያቂ ሲደረጉ አልተሰሙም" በማለትም ወቅሰዋል።

ጥያቄውን ያቀረብነው የተሳካ፣ ትክክለኛና ተዓማኒ ፖሊሲ ከመሻት ነው

የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ በቅርቡ ፖሊሲ ሆኖ ይፀድቃል ተባለበአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ብዙ ተጠርጣሪ ዜጎች መታሰራቸውንና  የሚታሰሩበት ቦታ "ሐሩርና ንዳድ የበዛበት ወታደራዊ ማሠልጠኛ" ዜጎች ጉዳዩን የሕግ ማስከበር ሳይሆን የበቀል እርምጃ አድርገው እንዲያዩት የሚጋብዝ በመሆኑ እርምት እንዲደረግ የሲቪክ ድርጅቶቹ  ጠይቀዋል። በረቂቅ የፖሊሲ ሰነዱ ላይ ምክክር መደረጉን በአወንታ የተመለከቱት ድርጅቶቹ ጥያቄያቸው የተሳካ፣ ትክክለኛ ማህበረሰቡ እምነት የሚጥልበት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ እንዲሆን ከማሰብ የቀረበ መሆኑን ገልፀዋል።

ሰሎሞን ሙጬ

ኂሩት መለሰ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር